የኢ.ፌዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት በ1995 ለአካባቢ ደህንነት እውቅና እና ጥበቃ የሚሰጥ አዋጅ አውጥቷል:: አዋጁ በአንቀጽ 44 ንኡስ አንቀፅ (1) ሁሉም ሰዎች ንፁህ እና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው እንዲሁም በአንቀፅ 92 መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህ እና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው ጥረት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል::
የአማራ ሚዲያ ኮርፓሬሽን የሕግ ባለሙያ ወ/ሮ ፍቅር ዘውዱ አካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ በወጡ ሕግ እና አዋጆች ዙሪያ እንደገለፁት ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ የአካባቢ ብክለት አዋጅ ቁጥር 300/1995 የወጣበት ዓላማ አንዳንድ የልማት ሥራዎች አካባቢያዊ ተፅእኖ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ነው:: በአጠቃላይ አካባቢን መጠበቅ በተለይም የሰውን ጤንነትና የተፈጥሮን ሥነ ውበት ማቆየት የሁሉም ሰው ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑ ፣ ፈሳሽ ቆሻሻን ከስሩ ለመከላከል ወይም ለማስወገድ እንዲቻልና በሕጉ በተቀመጠው አግባብ መፈፀም ያልቻሉትን እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል ነው::
በዚህ አዋጅ በትርጓሜ በክፍል አንድ በተራ ቁጥር 5 ፣ 6 እና 11 ስር እንደሰፈረው፤
ፍሳሽ፦ ማለት ተጣርቶም ይሁን ሳይጣራ በቀጥታም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወደ አካባቢ የሚለቀቅ ቆሻሻ ውኃ ወይም ሌላ ቆሻሻ ፈሳሽ ወይም ጋዝ ነው::
አካባቢ፦ ማለት ደግሞ በመሬት፣ በካባቢ አየር ፣ በአየር ሁኔታ እና በአየር ንብረት ፣ በውኃ ፣ በህዋና በድምጽ ፣ በጣእም፣ በማህበራዊ ጉዳዩች እና በሥነ ውበት ሳይወሰን በተፈጥሮአዊ ሁኔታቸው ወይም በሰው አማካኝነት ተሻሽለው ወይም ተለውጠው የሚገኙ ነገሮች በሙሉና ያሉበት ቦታ ሆነው እንዲሁም በመጠናቸው ወይም ሁኔታቸው ሰውን ወይም የሌሎችን ፍጥረታት የሚነኩ በማለት ይገልጻል።
በካይ፦ ማለት ፈሳሽ ፣ ጠጣር፣ ወይም ጋዝ የሆነ ነገር በቀጥታም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ያረፈበትን የአካባቢ ክፍል የሚያበላሽ፣ በሰው ጤና ወይም ሌሎች ህያዋን ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወይም ሊያደርስ የሚችል መርዝን ፣በሽታን፣ ክርፋትን ፣ጨረርን ፣ድምፅን ፣ንዝረትን ፣ሙቀትን ወይም ሌላ ክስተትን የሚያመነጭ ነው::
በአዋጅ አንቀፅ 5 ላይ ስለ ቆሻሻ አያያዝ በግልፅ ተቀጧል:: በዚህiም ብክለትን ወይም ሌላ አካባቢያዊ ጉዳትን ሊያስከትል በሚችል ተግባር ላይ የተሰማራ ሰው የቆሻሻ መመንጨትን ለማስወገድ ወይም ወደ ተፈላጊው መጠን ለመቀነስ በባለሥልጣኑ ወይም በሚመለከተው የክልል የአካባቢ መሥሪያ ቤት ትዕዛዝ መሰረት በተገቢው ቴክኖሎጂ እና ሲቻልም ቆሻሻን መልሶ በጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችሉ ዘዴዎች መቀየር አለበት።
ማንም ሰው ተገቢውን የአካባቢ ደረጃ በመተላለፍ አካባቢን ሊበክል ወይም በሌላ ሰው በኩል እንዲበከል ማድረግ አይችልም።
የከተማ አስተዳደር የተቀናጀ የከተማ ቆሻሻ አያያዝ ሥርአትን በማውጣት የከተማ ቆሻሻ መሰብሰቡን እና መጓጓዙን እንደተገቢነቱም በጥቅም ላይ መዋሉን፣ መምከኑን ወይም ጉዳት እንዳያመጣ ተደርጎ መወገዱን ማረጋገጥ እንዳለበት ባለሙያዋ አዋጁን ጠቅሰው አስገንዝበዋል።
ባለሙያዋ እንደሚሉት ለሕዝብ መገልገያ ክፍት የሆነ ቦታን የሚያስተዳድር ማንም ሰው ምን ጊዜም በቂና ተስማሚ የመፀዳጃ ቤት፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታዎችና አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች መገልገያዎች በቦታው መዘጋቸታቸውን ማራረጋገጥ አለበት። ቆሻሻን ስናስወግድ አግባብ ካላቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በመመካከር በሳይንሳና አካባቢያዊ መርሆዎች ላይ በመመስረት የሚከተሉትን ደረጃዎች ማካተት እንዳለበት በአዋጁ በክፍል ሦስት በአንቀፅ 6 ላይ ሰፍረዋል::
ወደ ውኃ አካላትና ወደ ፍሳሽ መቀበያ መስመሮች የሚለቀቁ ፍሳሾችን መከታተል፤
ወደ አፈር የሚጨመሩ ኬሚካሎችን ወይም በአፈር ላይ ወይም ውስጥ የሚወገዱ ቁሶችን ዓይነትና መጠን የሚወስኑ የአፈር ጥራት ደረጃዎች
የአካባቢን የአየር ጥራት የሚገልፁ፣ ለማይንቀሳቀሱና ለሚንቀሳቀሱ የአየር ብክለት ምንጮች የተፈቀዱትን የልቀት መጠኖች የሚወስኑ የአየር ጥራት ደረጃዎች ፤
የአሰፋፈር ሁኔታንና የሀገሪቱን የሳይንስና የቴክኖሎጂ አቅምን በማገናዘብ የሚፈቀደውን ከፍተኛ የድምፅ መጠን የሚወስኑ የድምፅ ልቀት ደረጃዎች ፤
የሚያስከትለውን ጠንቅ ለመግታት ምንጮች ላይ የሚከረፋ ሽታ እንዳይኖር ቁጥጥር ማካሄድ
የተለያዩ የቆሻሻ ዓይነቶች አመነጫጨት ፣ አያያዝ፣ አወጋገድ ፣ አጓጓዝ ፣ የሚያገለግሉ የመጠንና አተገባበር ደረጃዎችን መወሰን::
ቆሻሻን አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት ማስወገድ፣ መያዝ እና ማጓጓዝ ካልቻልን በወንጀል ሕግ የከበደ ቅጣት የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ የሚከተሉት የሕግ ተጠያቂነት ይኖሩብናል።
አዋጁን ተላልፎ ጥፋቱን የፈፀመው የተፈጥሮ ሰው ከሆነ ከአምስት ሺህ ብር በማያንስ ከአስር ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል።
አዋጁን ተላልፎ ጥፋቱን የፈፀመው በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ሰው ከሆነ እና ጥፋቱን ማወቅ የነበረበትና ኃላፊነቱን በብቃት ያልተወጣው የሥራ ኃላፊ ከአምስት ሽህ ብር በማያንስ ከአስር ሽህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል።
ወ/ሮ ፍቅር እንደሚያብራሩት የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ 1383/2017 ደግሞ፤
ደረቅ ቆሻሻ፡- ማለት የማይፈለግ ተብሎ የተጣለ ማንኛውም ፈሳሽ ያልሆነ ወይም ነፋሽ ያልሆነ ቆሻሻ ነው። ለምሳሌ፤ የሲጋራ ቁርጥራጭ፣ የሶፍት ወረቀት፣ ፌስታል፣ የጫት ገለባ፣ የፍራፍሬ ተረፈ-ምርቶች፣ የትራንስፖርት ቲኬት፣ የሞባይል ካርድ፣ የማስቲካና ከረሜላ ሽፋኖች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ፣ የውሀ ማሸጊያዎች ፣ የእቃ መጠቅለያ… ናቸው::
ፕላስቲክ፡ ማለት በዋናነት ከፔትሮ ኬሚካል የተሠራ፣ ለስላሳ እና የማይበሰብስ የፖሊመር ይዘት ያለው ምርት ነው።
አዋጁ ሲወጣ ታሳቢ ያደረጋቸው፤
1 ቆሻሻን ከምንጩ መቀነስ፣ መልሶ መጠቀም፣ መልሶ ዑደት ማድረግ እና በአግባቡ ማስወገድ፤
የህብረተሰብ ተሳትፎን ማሳደግ
አካባቢን የበከለን ማስከፈል
የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ በአዋጁ ክፍል 3 አንቀፅ 10
ማንኛውም ሰው ለዚህ ተብሎ ከተዘጋጀ ቦታ ውጪ ደረቅ ቆሻሻን ማስወገድ አይችልም፤
ማንኛውም ሰው በከተሞች አካባቢ በሕዝብ ወይም በግል ይዞታ ላይ ደረቅ ቆሻሻን በማቃጠል ማስወገድ አይችልም፣
ከአንድ ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀም የተከለከለ ነው። ነገር ግን ባለሥልጣኑ በአንቀፅ 14 ሊፈቅድበት የሚችል አግባብ አለ:: ፕሊስቲክ ማሸጊያው በቀላለ በሌላ ምርት የማይተካ መሆኑ እና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው። ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል መሆኑንም ፕላስቲኩ ላይ መለጠፍ አለበት። የፕላስቲክ ከረጢትን ግን አይመለከትም።
ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤት ይዞታው ድንበር አንስቶ እስከ 20 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት እንዳለበትም በለሙያዋ ጠቁመዋል::ደረቅ ቆሻሻ በከተማ አስተዳደሮች በሚዘጋጁት የሕዝብ የጋራ መገልገያ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች በጊዜያዊነት መከማቸት አለበት:: ማንኛውም ሰው የሞቱ እንስሳትን ለእነዚህ አይነት ቆሻሻዎች ተብሎ በተዘጋጁ ቦታ በጊዜያዊነት ማስቀመጥ ይችላል::
የንግድ ተቋም ከይዞታው ድንበር አንስቶ ቢያንስ እስከ 50 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት አለበት፤ቆሻሻ ፈርጁ ተለይቶ ምልክት የተደረገባቸው የጉድፍ ማጠራቀሚያዎች አመቺ በሆነ ቦታ ማስቀመጥ አለበት:: ማንኛውም ሰው ለደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አገልግሎት ክፍያ የመፈጸም ግዴታ አለበት::
አዋጁን ተላልፎ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ማንኛውም ሰው የሕግ ተጠያቂነቱ በአዋጁ በአንቀፅ 25 ስር ማንኛውም ሰው የፕላስቲክ ከረጢት ከተጠቀመ ወይም ይዞ ከተገኘ ወይም ማንኛውም ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ ከተገኝ ከሁለት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ይደነግጋል::
ያመረተ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ለገበያ ያቀረበ ወይም የሸጠ፣ ለንግድ ዓላማ ያከማቸ ወይም ይዞ የተገኘ ከ50 ሺህ ብር በማያንስና ከ200 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እና ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አዋጁ ያዝዛል:: ጥፋቱን የፈፀመው የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ከሆነ ቅጣቱ በ3 እጥፍ ይጨምራል።
የህግ አንቀጽ
- የሚኒሥትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 545/2016 አንቀፅ 2 ንኡስ አንቀፅ (2) መሠረት “የአካባቢ ጥበቃ” ማለት የሰው ልጅን ጨምሮ የማንኛውም አካል ሕይወት እና እድገት የሚወስኑ የመሬት፣ የውሃ፣ የአየር፣ የአየር ንብረት ሥርዓት የመሳሰሉት ሌሎች የአካባቢ ሀብቶች፣ ክስተቶችና ሁኔታዎች መጠበቅ ነው፡፡ በዚህ ስር የወጡ አዋጆች፦
- የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መቋቋሚያ አዋጅ፣
- የአካባቢ ተጽኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር፣
- የአከባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ፣
- የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ቁጥጥር አዋጅ፣
- የደን ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም አዋጅ በቅርቡ የፀደቀው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ 1383/2017፣
- የግሪን ሀውስ ጋዝ ልቀት መጠን መቀነስን የሚመለከተው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ማፅደቂያ አዋጅ፣
- የአደገኛ ዝቃጮች ድንበር ዘለል ዝውውርንና አወጋገድን ለመቆጣጠር የወጣው የባዜል ኮንቬንሽን ማፅደቂያ አዋጅ፣
- በአጠቃላይ ከአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የሚነሳው አዋጅ ቁጥር 300/1995 ሲሆን ከጠቅላላው የአዋጁ ድንጋጌዎች መረዳት እንደሚቻለው በአካባቢ ወይም በሰው ደህንነት ወይም ጤና ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ በካይ ነገሮችን ወደ አካባቢ መልቀቅን ይከለክላል።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም