የዘመን ስሌታችን

0
15

ኢትዮጵያና ግብፅ የታሪክ እና የባህል እንዲሁም የሀይማኖት ትስስር ያላቸው በመሆኑ ተመሳሳይ የዘመን አቆጣጠር እንደነበራቸው ይነገራል። ሁለቱም የፀሐይ ኡደትን የተከተለ የአቆጣጠር ስርአት ይከተሉ ነበር። በነሀሴ መጨረሻ ላይ ከአባይ መጥለቅለቅ ጋር ሶጢስ የተባለው ኮከብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመውጣቱ ጋር  ሲገጣጠም የአዲስ ዓመት መጀመሪያ መሆኑን ያሳይ ነበር። በዚሁ ከዓለም ኢትዮጵያን ልዩ ወደ ሚያደርገው የዘመን አቆጣጠር እና ስለ ጳጉሜ ምስጢር እናልፋለን።

ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መነሻ መሆኗን የሰው ልጅ ፍልሰት ጥናቶች፣ የቅሪተ-አካል ጥናቶች እና ሌሎች የሳይንሳዊ ማስረጃዎች ያረጋገጡት ሀቅ ነው። ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች ቤተ መዘክር ሲል ኮንት ሮዚኒ ይገልፃታል። ከ80 በላይ ቋንቋ፣ ባህል እና ማንነት ያለው ሕዝቧ በአብሮነት፣ በአንድነት እና በመቻቻል የሚኖሩባት ታላቅ ምድር ናት:: አንጋፋዎቹ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች በፍቅር እና በወንድማማችነት ለዘመናት አብረው በመኖር ለዓለማችን ጥሩ ምሳሌ ሆነዋል::

ኢትዮጵያ ከሌላው የዓለማችን በተለየ መልኩ የአስራ ሶስት ወር የፀሐይ ብርሃን የማይጠፋባት ሀገር መሆኗ ግርምትን ይፈጥራል:: ይህም የሆነበት ሚስጢሩ ኢትዮጵያ የራሷ ብቻ የሆነ የጊዜ አቆጣጠር ቀመር ያላት መሆኑ ነው። የጊዜ አቆጣጠር ቀመሯ በቀን፣ በሳምንት፣ በወር እና በዓመት የተከፋፈለ መሆን ከሌሎች የዘመን ስሌት አይነቶች ያመሳስለዋል::

የሃገራችን ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌሎች ለምን ተለየ? ብለን ብንጠይቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባሕረ ሐሳብ በሚል መጽሐፋቸው ላይ “ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ዘመን መነሻ አድርገው ይጠቀማሉ፤ ታላቁ እስክንድርም የገነነበት ዘመን መቁጠሪያቸው ሆኖ ነበር” የሚል ምክንያት ይሰጣሉ። የእኛ ካህናትም ዘመነ እስክንድር በሚል ይጠቀሙበት እንደነበር መፃህፍት ይመሰክራሉ::

ሶርያውያን የዘመን አቆጣጠራቸውን የሚለኩት በፀሐይ ቆጥረው ለዓመቱ 365 ቀን ከ6 አካፍለው ዕለትን በመስጠት ከሮማውያን በተዋሱት ጊዜ የዓመቱን መጀመሪያ አዲስ ዓመት ይሉታል:: በኋላ የሰማዕታት መታሰቢያ እንዲሆን በ460 ዓመተ እግዚእ የተባለውን የዘመን መለወጫ ወደ መስከረም 1 ቀን ለወጡት ይባላል::

የሀገራችን ሊህቃንም አዲስ ዓመታችን መስከረም አንድ ቀን እንዲሆን የወሰኑት ይኸንን በመከተል እንደሆነ ያስረዳናል:: የዓመቱን መጀመሪያ መስከረም ማድረግን ከሶርያውያንም ሆነ ከግብጾች ብናገኘውም ጀማሪው በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ይገዛ የነበረው ዩልዮስ ቄሣር ስለነበር የዩልዮስ ባሕረ ሐሳብ ተብሎ ይጠራል::

ዩልዮስ ቄሣር በ46 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ባወጣው የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት መሠረት ዓመቱን 365 ዕለት ከ6 ሰዓት አድርጎ ለአራት ወራት 30 ቀናት መድቦ ለአንዱ 28 ቀን በ4 ዓመት አንዴ ደግሞ 29 ቀናት በመስጠት ለቀሩት ሰባት ወራት 31 ቀናት መድቦላቸው በ12 ቦታ ከፋፍሏቸዋል::

ለክርስትያኑ የዘመን ስሌት መነሻ ለመስጠት ሁለት ሙከራዎች የተደረጉ መሆኑን ፕሮፌሰር ስርግው ይጠቁማሉ። የመጀመሪያው ሙከራ በ213 ዓ.ም የነበረው የአፍሪካው ጁሊያን ያሰላው ሲሆን ከዓለም መፈጠር እስከ ክርስቶስ መወለድ ያለውን ጊዜ 5 ሺህ 500 ዓመታት እንደሆነ አስልቶታል። ይህ ስሌት የመፅሀፍ ቅዱስን የፍጥረት መቅደም መከተል መሰረት ያደረገ መሆኑ ግልፅ ነው። ሁለተኛው ሙከራ ነአፓንዶር እና አኒያኖስ የተደረገው ሲሆን ከዓለም መፈጠር እስከ ክርስቶስ መወለድ ያለው ጊዜ 5 ሺህ 492 እስከ 5 ሺህ 493 ዓመታት አድርገው ያሳዩበት አቆጣጠር ነው። ይህ በሁለቱ አቆጣጠሮች መካከል የ7 ወይም የ8 ዓመታት ልዩነት መኖሩን ይጠቁማል።

አውሮፓውያኑ የሚጠቀሙበትም ይህን አቆጣጠር መነሻ አድርገው ነው:: የእኛ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን እንዴት እንደተለየ አሥራት ገብረ ማርያም የዘመን አቆጣጠር በሚለው መጽሐፋቸው ሲገልጹ “ዲዮናስዮስ የተባለው የሮም መነኩሴ ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ዘመን በስሌት ለመድረስ የተከተለው መንገድ ነው” በማለት  ገልጿል::

የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ልዩነት መነሻው የዚህ ክስተት መሆኑን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲያረጋግጡ “ኢትዮጵያ ዘመነ ብሉይን እንዲህ አስከትላ 5 ሺህ 500 ብላ ስትቆጥር ዘመነ ሐዲስ ልዩ ሆኖ ከማንም ቁጥር አይገጥምም:: ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ከምሥራቆቹም ከምዕራቦቹም ሁል ጊዜ በሰባት ዓመትታ ጎድላለች:: ምክንያቱም ባለ ታሪኮችን ትታ ወንጌል ተርጓሚዎችን መነሻዋ ስላደረገች ነው” ይላሉ:: በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ እና የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ልዩነት ሊኖረው እንደቻለ ለማወቅ ይቻላል።

ወደ ሃገራችን የዘመን እና ወራት አቆጣጠር ስንመለስ ኢትዮጵያ የአስራ ሶስት ወር ፀጋ ባለቤት መሆኗ ከሌሎች ልዩ ያደርጋታል:: ወራቱም ከጳጉሜ በስተቀር የራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ስም በመያዝ መስከረም፣ ጥቅምት፣ ህዳር፣ ታህሣሥ፣ ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚያዝያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ፣ ሃምሌ፣ ነሃሴ እና ጳጉሜ በመባል ይጠራሉ::

ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋትን የዘመን አቆጣጠር ስንመለከት እያንዳንዱ ዓመት ወንጌላዊያንን መሠረት በማድረግ ባራት አዝማናት መከፈሉ አንዱ ሲሆን ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ፣  ዘመነ ዮሐንስ በመባል ይታወቃሉ። ከመስከረም እስከ ነሐሴ ያሉ ወራት በ30 ቀናት የተከፈሉ ኢትዮጵያዊ ስያሜዎች አሏቸው፤ ጳጉሜ ወር ግን በየዓመቱ 5 ቀናትን ስትይዝ በየአራት ዓመት አንዴ ስድስት ቀን እና በየስድስት መቶ ዓመት አንዴ ደግሞ ሰባት ቀናት ትሆናለች::

ጳጉሜ “ሄፓጉሜኔ” ከሚል የግሪክ ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜው ደግሞ ጭማሪ ማለት እንደሆነ ይታመናል:: በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ ጳጉሜ ስድስት ቀን ትሆናለች:: አውሮፓዊያን ጳጉሜን በየወሩ ሠላሳ አንድ ቀን በማድረግ ተጨማሪ ሲያደርጓት ኢትዮጵያ ደግሞ በየዓመቱ ተጨማሪ ወር አድርጋ ሰይማታለች:: ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማውን የክረምት ወቅት የምናልፍባት ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ ድልድይም ናት::

አስራ ሦስተኛዋ ወር ጳጉሜ በነሃሴ እና በመስከረም መካከል የምትገኝ እንዲሁም በኢትዮጵያ የወራት አቆጣጠር የመጨረሻ ወር ናት:: ኢትዮጵዊያን የጳጉሜ ወርን የምሕረት እና ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ የተስፋ ወር አድርገው ይጠሯታል:: እንዲያውም ጳጉሜ ከሌሎች ወራትም ቢሆን ለየት የሚያደርጋት ትንሽ ቀናት ያሏት፣ ወርሃዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት የሌላት ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ወርም ጭምር ናት:: ስያሜዋንም ስንመለከት ከሌሎች የኢትዮጵያ ወራት በተለየ መልኩ ኢትዮጵያዊ ስያሜ አይደለም:: በዚህ ሂደትም በሁለት ዘመናት መካከል የምትገኝ እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ የምታገለግል ወር ናት ጳጉሜ::

የዻጉሜን ወር ኢትዮዽያዊ ወር ናት የተባለበት ምክንያትም ሃገራችንን ከሌሎች በዘመን አቆጣጠር ለየት ብላ እንድትታይ ያደረገች በመሆኗ ነው። ሰራተኞች የዻጉሜን ቀናት ደሞዝ አይጠይቁም፣ አከራዮችም ኪራይ አይጠይቁባትም።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here