የበርካታ ሀገራት ዜጎች መኖሪያቸው አድርገዋታል። ከዓለማችን ሀገራት መካከል ከሩሲያ በመቀጠል በስፋቷ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ለዛሬው ሽርሽር መዳረሻ ያደረግናት -ካናዳ።
በሰሜን አሜሪካ አህጉር የምትገኘው ካናዳ፣ በሰሜን የአርክቲክ ውቅያኖስ፣ በደቡብ የአሜሪካ ግዛት(United States) ጋር ረጅም ድንበር ትጋራለች። በምሥራቅ አትላንቲክ፣ በምዕራብ ደግሞ ፓስፊክ ውቅያኖስን ታዋስናለች።
ካናዳ 10 ክፍለ ግዛቶች(Provinces) እና ሦስት ግዛቶች(Territories) አሏት። እያንዳንዳቸው የራሳቸው አስተዳደር አላቸው።
ካናዳ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት አላት። የኢትዮጵያን ዘጠኝ እጥፍ እንደማለት ነው። በሕዝብ ብዛት ግን ከእኛ በሦስት እጥፍ ታንሳለች። እ.አ.አ የ2024 ትንበያ እንደሚያመላክተው ከ40 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖርባታል።
ካናዳ ፌዴራላዊ ፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ እና ሕገ መንግሥታዊ ንጉሣዊ የመንግሥት አስተዳደርን ትከተላለች። የእንግሊዝ ንጉሠ ነገሥት የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የመንግሥት መሪ ናቸው።
የካናዳ የፖለቲካ ሥርዓት በመድብለ ፓርቲ መዋቅር ተለይቶ የሚታወቅ ነው። ሊበራል ፓርቲ እና ወግ አጥባቂው ፓርቲ ሁለቱም የሀገሪቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።
ካናዳ በፈረንሳይ እና እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ቆይታለች። እ.አ.አ ከ1982 ወዲህ ግን ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ግዛት ነፃ መሆኗን አውጃለች። አሁንም ድረስ ግን የእንግሊዝ ንጉሣዊ አገዛዝ አካል ሆና ቀጥላለች።
ከስፋቷ አንፃር ሰው የሚኖርበት የሀገሪቷ ክፍል 10 ከመቶው ብቻ ነው። 90 ከመቶው የካናዳ መሬት በጫካ፣ በተራራ፣ በወንዝ፤ ከምንም በላይ በሐይቆች የተሸፈነ ነው። ሐይቆች ዘጠኝ ከመቶውን የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት ይይዛሉ። ዓለማችን ላይ ከሚገኙ ሐይቆች 60 ከመቶ የሚሆኑት መገኛቸው ካናዳ ናት። ሁለት ሚሊዮን ሐይቆች አሏት። ከዓለማችን የባሕር ዳርቻዎች ውስጥም 57 ከመቶዎቹ የሚገኙት በካናዳ ነው።
በስፋቷ ምክንያት ስድስት የሰዓት አቆጣጠር ዞኖችን ትጠቀማለች። እዚያው ካናዳ አንዱ ከተማ ውስጥ ሆነው ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲሆን ሌላው ከተማ ላይ አስራ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ይሆናል ማለት ነው።
የካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ ትባላለች። እ.አ.አ በ1857 ነበር ለዋና ከተማነት በንግሥት ቪክቶሪያ የተመረጠችው። በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል መገኘቷም ለመመረጧ ምክንያት መሆኑ ይገለጻል። ኦታዋ የሻዋርማ/የደሮ አሮስቶ/ ዋና መገኛም ናት። በካናዳ ከሚገኙ ብርዳማ ከተሞችም አንዷ ናት።
ቶሮንቶ ደግሞ የካናዳ ትልቋ ከተማ ናት። ከሀገር አቀፉ ኢኮኖሚ 20 ከመቶውን ታመነጫለች። ቶሮንቶ እና ግሬተር ቶሮንቶ በመባልም በሁለት ትከፈላለች። ቶሮንቶ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ፣ ግሬተር ቶሮንቶ ደግሞ ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ነዋሪዎች አሏቸው። ሲኤን ከሚባለው ታወር በመውጣት ቶሮንቶን ሙሉ በሙሉ ቁልቁል መመልከት ይቻላል። የቶሮንቶ የምድር ውስጥ ከተማ በመባል የሚገለጽ የ30 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የምድር ውስጥ መንገድም አላት። መንገድ ብቻ አይደለም፤ 1200 ሱቆች አሉት። ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የገበያ ማዕከላት፣ የችርቻሮ ሱቆች፣ … በዚህ የምድር ውስጥ መንገድ ፈልገው የሚያጡት ነገር የለም። የከተማዋን የተለያዩ ክፍሎች እና የባቡር መስመሮችንም ያገናኛል።
ሞንትሪያል የካናዳ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ናት። በሞንትሪያል ክረምቱ በጣም ይከብዳል። ብርዱን ለማቅለል ታስቦም ልክ እንደ ቶሮንቶ ሁሉ የ33 ኪሎ ሜትር የምድር ውስጥ መንገድ ተገንብቷል። ሌላኛዋ የካናዳ ከተማ ቫንኩቨር ደግሞ ዝናብ የማያጣት ናት። በተለይ ከታህሳስ እስከ ሚያዚያ ባለው ጊዜ ጫን ይላል። ከፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ የምትገኘው ቫንኩቨር ዓለማችን ላይ ለኑሮ ምቹ ከሚባሉ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ታጥታ አታውቅም። የተቃርኖ ከተማም ናት። ቢሊየነሩ እና ጎዳና ተዳዳሪው ይኖሩባታል። ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እና የተፈጥሮ ፏፏቴዎችም መገኛ ናት።
ካናዳ ተገኝቶ ኒያግራን ሳያዩ መመለስ “ወንጀል ከመፈጸም አይተናነስም” ይባልለታል። ኒያግራ በውበቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ከዓለማችን ትላልቅ ፏፏቴዎች አንዱ ነው። በአሜሪካ እና ካናዳ ድንበር ላይ ይገኛል። ለጉብኝት በመርከብ የ20 ደቂቃ የፏፏቴ መሃል ጉዞ ማድረግ ይቻላል። 14 ሚሊዮን ቱሪስቶችም በየዓመቱ ይጎበኙታል። በፏፏቴው አቅራቢያ የምትገኘው የኒያግራ ከተማም የ90 ሺህ ሰዎች መኖሪያ ናት። የምትተዳደረውም ከቱሪስቶች በሚገኝ ገቢ ነው።
በርካታ የዱር ሃብት፣ ተራራማ ስፍራዎች እና ልዩ ልዩ ውበትን የተላበሱ መልካምድሮች፣ ከተፈጥሮ ለካናዳ የተሰጡ በረከቶች ናቸው። በመሆኑም 11 የተፈጥሮ እና አንድ የባሕላዊና ተፈጥሮ ቅይጥ በድምሩ 12 የመስህብ ሃብቶችን በዩኔስኮ አስመዝግባለች። የተፈጥሮ ውበትን እና የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ ተብለው ስምንት ታላላቅ ብሔራዊ ፓርኮች በካናዳ ተቋቁመዋል።
የተፈጥሮ ሃብቶቿ ተወዳጅ ጉዞዎችን ለማድረግ፣ ለበረዶ ላይ መንሸራተት ስፖርት፣ ለብስክሌት ግልቢያ፣ የተለያዩ አዋፋትን እና የእንስሳት ዝርያዎች ለመመልከት እንዲሁም ለተፈጥሮ ማረፊያነት ያገለግላሉ። የጎብኝዎችን ቀልብ በመሳብም የቱሪዝም ገቢን ያመነጫሉ።
ካናዳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስጠሯት ነገሮች አንዱ የትምህርት ስርዓቷ ነው። እድሜያቸው ከ25 እስከ 64 ከሚሆኑት ውስጥ 57 ከመቶዎቹ ከኮሌጅ ወይንም ከዮኒቨርሲቲ የተመረቁ ናቸው። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት ያስቀምጣታል። 81 ከመቶ ዜጎቿ የሁለተኛ ደረጃ፣ 99 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ የቀለም ትምህርት ወስደዋል።
በካናዳ ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው ትምህርት በነፃ ይሰጣል። መክፈል አለብኝ ላለም የግል ትምህርት ቤቶች አሉ። ሆኖም ግን 93 ከመቶ ካናዳውያን ልጆቻቸውን በመንግሥት ትምህርት ቤት ያስተምራሉ።
ከሌሎች ሀገራት በተለዬ ካናዳ በፌደራል ደረጃ የትምህርት ሚኒስቴር የላትም። የትምህርት ፖሊሲውም፣ ካሪኩለሙም፣ በጀቱም የሚመራው በግዛቶች ነው። እናም ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላው ግዛት ሲቀይሩ የትምህርት ሥርዓቱ አብሮ ሊቀየር ይችላል። በአብዛኛዎቹ የካናዳ ግዛቶች ለምሳሌ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚጠናቀቀው 12ኛ ክፍል ላይ ነው። በኩቤክ ግዛት ግን አንድ ቀንሶ 11ኛ ክፍል ላይ ያልቃል። ግዛቶች የዚህን ያህል መብት አላቸው።
ካናዳ መጀመሪያ በፈረንሳይ ቀጥሎ በእንግሊዝ ቅኝ በመገዛቷ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ይፋ የሥራ ቋንቋዎቿ ናቸው። ይህ በትምህርት ሥርዓቱም ላይ ይንጸባረቃል። እንደየሚኖሩበት ግዛት አንዱን ቋንቋ መርጠው መማር ይችላሉ። ሆኖም በእንግሊዝኛ የሚማሩ ፈረንሳይኛ፣ በፈረንሳይኛ የሚማሩም እንግሊዝኛ ተጨማሪ የቋንቋ ትምህርት ሆኖ ይሰጣቸዋል።
ካናዳ መምህርነት የሚከበርባት ሃገር ናት። መምህር ሆኖ ለመቀጠርም፣ ለመቀጠልም ከፍተኛ ብቃት ይጠይቃል። መምህራን በየአምስት ዓመቱ የብቃት ፈተና ይሰጣቸዋል። ተገቢውን ክብር እና ጥቅማጥቅምም እንዲያገኙ ይደረጋል።
ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በካናዳ አይታወቅም። ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ውጤት ብቻውን በቂ ነው። የዚህ ጽሑፍ መጠናቀቂያም እዚህ ላይ ሆኗል፤ ቸር ይግጠመን።
ምንጭ፦ canada.ca፣ am.al.ain.com፣ statcan.gc.ca፣ ceochronicles፣ breathelife2030.org፣ gustice.gc.ca
አጭር እውነታ
ካናዳ
- ከዓለማችን ሀገራት መካከል ከሩሲያ በመቀጠል በስፋቷ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡
- ካናዳ 10 ክፍለ ግዛቶች(Provinces) እና ሦስት ግዛቶች(Territories) አሏት።
- ካናዳ ዘጠኝ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት አላት።
- ካናዳ በፈረንሳይ እና እንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ቆይታለች።
- ከስፋቷ አንፃር ሰው የሚኖርበት የሀገሪቷ ክፍል 10 ከመቶው ብቻ ነው።
- 90 ከመቶው የካናዳ መሬት በጫካ፣ በተራራ፣ በወንዝ፤ ከምንም በላይ በሐይቆች የተሸፈነ ነው።
- ሐይቆች ዘጠኝ ከመቶውን የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት ይይዛሉ።
- በስፋቷ ምክንያት ስድስት የሰዓት አቆጣጠር ዞኖችን ትጠቀማለች።
- የካናዳ ዋና ከተማ ኦታዋ ትባላለች።
- ቶሮንቶ ደግሞ የካናዳ ትልቋ ከተማ ናት።
- ካናዳን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚያስጠሯት ነገሮች አንዱ የትምህርት ስርዓቷ ነው።
- ካናዳ መምህርነት የሚከበርባት ሃገር ናት።
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም