የአማራ ክልል ፕላን ቢሮ ከ2015 እስከ 2022 ባወጣው ሪፓርት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት የሞት ምጣኔ ቢቀንስም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሕፃናት ደግሞ መከላከል በሚቻሉ የጤና ችግሮች በየዓመቱ እንደሚሞቱ አሳውቋል:: ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሕጻናት እና ጨቅላ ሕጻናት ሞት መከላከል እና መታከም በሚችሉ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት እንደሆነም ነው ሪፓርቱ የሚያመለክተው::
በባሕር ዳር ከተማ ፈለገሕይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል እና ሀሌታ የየጻናት ስፔሻሊቲ ክሊኒክ የሕጻናት ስፔሻሊስት ሃኪም ዶ/ር አስቻለው ካሴ እንደሚሉት ከአምስት ዓመት ዓመት በታች የሕጻናት ሞት ሲባል በዕድሜ ደረጃ በሦስት ተከፍሎ ይታያል:: የጨቅላ ሕፃናት፣ ከአንድ ዓመት በታች እና ከአምስት ዓመት በታች ያሉሕፃናት ሞት ተብለው ይከፈላሉ:: ይህም የሆነው የሞት ምክንያቱ በአብዛኛው የተለያየ ስለሆነ ነው::
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ እ.አ.አ ከ2005 እስከ 2019 ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ከአንድ ዓመት በታች እና ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት ሞት ቁጥር ለውጥ ቢኖረውም ከ28 ቀን በታች ያለው የጨቅላ ሕጻናት ሞት ግን አሁንም ከፍተኛ ቁጥር እየተመዘገበ ነው:: የጨቅላ ሕጻናት ሞትን በተለከተ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሱት ምክንያቶች ወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮች ናቸው:: ለምሳሌ፡- መታፈን ፣ መወለጃ ጊዜያቸው ሳይደርስ ወይም ክብደታቸው ትንሽ ሆነው መወለድ እና የጨቅላ ሕፃናት ኢንፈክሽን እንደ ሀገር አቀፍም በከፍተኛ የጨቅላ ሕፃናት ሞት በመጨመር የሚጠቀሱ ናቸው:: በሌላ በኩል በተፈጥሮ የአፈጣጠር ችግር፣ (congontal) ተቅማጥ፣ የታችኛው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን፣ የሳንባ ምች ፣ አደጋ ፣ ኩፍኝ ፣ወባ እና የምግብ እጥረት በሁሉም የዕድሜ ክልል ምክንያት ይሆናል::
በጨቅላ ሕጻናት ላይ የኢትዮጵያ ዴሞግራፊ ኸልዝ ሰርቬይ (ዲ ኤች ኤስ) እ.አ.አ 2019 ባደረገው ጥናት ከአንድ ሺህ 33ቱ ይሞታሉ:: በ2005 ከተጠናው ጥናት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ከአንድ ሺህ ጨቅላ ሕጻናት 39 እንደሚሞቱ ነበር መረጃው ያስታወሰው:: ይህም ከ19 ዓመት በኋላም የጨቅላ ሕጻናት ሞት ብዙ ለውጥ አለመኖሩን ነው ባለሙያው ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ለበኵር የገለጹት::
ከአንድ ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት የሞት ምጣኔ በ2005 ከነበረው ከአንድ ሺህ ወደ 77 ዝቅ ብሏል:: በ2019 እ.አ.አ ደግሞ ከአንድ ሺህ ወደ 47 ዝቅ በማለቱ ለውጡ የተሻለ ነው:: አጠቃላይ ከአምስት ዓመት በታች ደግሞ 2005 እ.አ.አ በተደረገ ጥናት ከአንድ ሺህ ሕጻናት 123ቱ መሞታቸው ተረጋግጧል:: ይሁን እንጅ እ.አ.አ በ2019 ከአንድ ሽህ ወደ 59 ዝቅ ብሏል:: ይህም ለውጡ ጥሩ ነበር::
በጠቅላላው ግን በሦስቱም የዕድሜ ርከኖች (ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ሞት) የሞት ምጣኔ 55 ከመቶው የጨቅላ ሕጻናት ሞት ምክንያት ነው:: ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕጻናት ዋና ዋና የሞት ምክንያቶች የሚባሉት በቁጥር ከጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ 40 ነጥብ 7 ከመቶ ፣ በተቅማጥ 13 ነጥብ 2 ከመቶ፣ በታችኛው የመተንፈሻ አካል ችግር /ሳንባ ምች/ 10 ነጥብ 3 ከመቶ ጉዳት ያደርሳሉ:: ድንገተኛ አደጋ ፣ ወባ ፣ ኩፍኝ ፣ ተቪ … የመሳሰሉት ደግሞ ሌሎች ለሕጻናት ሞት በመንስኤነት የተቀመጡ ናቸው::
በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚከከሰቱ ኢንፌክሽን የሚባሉት ምልክቶቹን ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ነው:: ቤተሰብም በግልፅ ለመንገር ይቸገራል:: ነገር ግን የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን፣ ተቅማጥ፣ ቲታነስ እና ወባ ጠቅለል ብለው የጨቅላ ሕፃናት ኢንፈክሽን ተብለው እንደሚጠሩ ባለሙያው አስገንዝበዋል:: ምክንያቱም እንደ ትልቅ ሰዎች ምክንያቱ ይሄ ነው ማለት ስለሚከብድ የጨቅላ ሕጻናት ኢንፌክሽን (ኒዮናታል ሴፕሲስ) ተብሎ ይጠራል:: ከሦስት ትልልቅ የሞት ምክንያቶችም አንዱ ነው::
ከእርግዝና ክትትል በኋላ እናቶች ጨቅላ ሕጻናቶቻቸው አልጠባ ሲሉ፣ ሙቀት ሲኖር፣ አተነፋፈሳቸው እና ፀባያቸው ሲቀያየር፣ ሲነጫነጩ፣ ሲያለቅሱ፣ ተደጋጋሚ ትውከት እና ተቅማጥ ሲከሰት፣ ዐይናቸውን እና ምላሳቸውን ጨምሮ ሁሉም አካላቸው ቢጫ ከሆነ፣ ንቃታቸው ከበፊቱ ከቀነሰ ምልከቶቹን በቶሎ ተረድቶ ወደ ህክምና ቦታ በመሔድ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል::
ዶ/ር አስቻለው እንደሚገልፁት ብዙ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍ (ኮንጀንታል ማሌሪያ) የሚባል ወባ አለ፤ እናት በዚህ የወባ አይነት ተይዛ ከሆነ በልጁ ዐይን እና መላ አካላቱ ነጭ መሆን እና ቢጫ መሆን፣ ሙቀት፣ ተደጋጋሚ ትውከት እንዲሁም ሲዳሰሱ የጣፊያ/ የጉበት ማደግ ፣በደም ማነስ ምክንያት አተነፋፈስ መቀየር /ፍጥን ፍጥን/ ያለ የአተነፋፈስ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ:: እዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ የሚገባው እንደ ትልልቅ ሕጻናት ምልክቶቹ በግልፅ የማይታዩ በመሆኑ በጤና ተቋም ነው በሽታው የሚለየው::
ሌላው የሞት ምክንያት ካለ ቀን መወለድ ነው:: ያለቀናቸው የተወለዱ ሕጻናት የሚባሉት ደግሞ በህክምናው ከ37 ሳምንት በፊት የተወለዱ ከሆነ እና ከ2 ሺህ 500 ግራም በታች ከሆኑ አነስተኛ የውልደት ክብደት ያላቸው ይባላሉ:: ክብደታቸው አነስተኛ ሆነው ሲወለዱ ለተለያየ በሽታ በተሎ እንዲጋለጡ እና እድገታቸው ላይ ሊቸገሩ ይችላሉ፤ ይሄም ኢንፌክሽን፣ የጸሐይ ብርሐን እጥረት እና ደም ማነስ ሊያመጣ ስለሚችል በየሳምንቱ እና በየወር እስከ አንድ ዓመት ክትትል ያስፈልጋቸዋል:: ይህም በሚጠበቀው መጠን እያደጉ ነው ወይ? የሚለውን ለመከታተል የሚረዳ እንደሆነ ነው ባለሙያው የጠቆሙት::
በዚህ ረገድ በርካታ ችግር አለ፤ የሪፈራል (ለተሻለ ህክምና ተቋም) የመላክ ሂደቱ ላይ ያለ ችግር ፤ ህመሙ ተለይቶ አለያም ያለቀኗ ጤና ጣቢያ የወለደች እናትን አገልግሎት ማግኘት እያለባት በሪፈራል (የተሻለ ህክምና) ለመላክ መዘግየት ምክንያት ወደ ማይመለስበት ደረጃ ይሄዳል:: ሌላው ክብደታቸው አንሶ ያለቀናቸው ሲወለዱ ሙቀት እንዲያገኙ እናቲቱ የምትሰጠው ካንጋሮኬር (kmc) ብዙ ጥቅም ያለው ቢሆንም አለመስጠቱ፣ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም ለመድረስ የመሠረተ ልማት ችግር፣ የመንገድ እና አምቡላንስ አለመኖር (በቂ አለመሆን) መንገዶች አለመመቻቸቱ፣ ከፀጥታ ጋር የተያያዘ ችግር እንዲሁም በጤና ተቋምም ያለው የህክምና መሳሪያ የተሟላ አለመሆን (በተለይ የጨቅላ ህፃናት የሚጠቀምባቸው እንደ አየር መስጫ አይነት እቃዎች) እንደ ችግር ይነሳሉ::
ታዲያ እነዚህን የሕጻናትን ሞት የሚያፋጥኑ ችግሮች ለመቀነስ ሁሉም አካል የራሱ ሚና አለው:: መፍትሔ የሚሆነው ከመንግሥት ስንጀምር መሰረተ ልማት እና አንቡላንስ እንዲሁም የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላት ፣ጤና ባለሙያው ለሙያው ትኩረት ሰጥቶ በኃላፊነት መሰልቸት እና ቸልተኝነት ሳይኖር በተጠያቂነት መሥራት አለበት:: ከዚህ በተጨማሪ ሪፈር የተባሉትን ቶሎ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከባለሙያ ጋር አብሮ መላክ ያስፈልጋል::
የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ለሕጻናት የሚሆኑ መድኃኒቶችን እና እቃዎችን ማሟላት ከመንግስት እና ባለሙያው የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ ባለሙያው ጠቁመዋል:: ምክንያቱም ይላሉ ዶ/ር አስቻለ፤ መታከም እና መዳን እየቻሉ ሆስፒታል ላይ መድኃኒት ባለመገኘቱ ውጭ ላይ ገዝቶ ለመስጠት አቅም እያጠራቸው ለህክምና ፈቃደኛ ባለመሆን የሚመለሱ ብዙ ናቸው:: ከሔዱ በኋላ ደግሞ እንደሚሞቱ ይታወቃል::
ሙያተኛው ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ማሳወቅ እና ማስተማር ይገባዋል:: እናቶች ደግሞ በእርግዝና ወቅት በቂ የሆነ ክትትል በማድረግ አጥጋቢ በሚባል መልኩ የሕፃናቱን ጤና ለመከታተል ይረዳል፣ ቀድሞ ችግሮቹን ለይቶ ቀድሞ ለተሻለ ህክምና በመላክ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ መተባበር እና ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ዶ/ር አስቻለው አስገንዝበዋል::
ጤና አዳም
ድንገተኛ የጨቅላ ሕጻናት ሞት ሲንድረም (SIDS)
ድንገተኛ የጨቅላ ሕጻናት ሞት ሲንድረም (SIDS) የጤናማ ጨቅላ ሕፃናትን ድንገተኛ ሞትን (በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት) ያመለክታል፤ በተለምዶ በእንቅልፍ ወቅት የሚከሰት በሚልም ይታወቃል። በአብዛኛው ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሕጻናት ላይ ይከሰታል።
ምልክቶች
ጨቅላ ህጻናት በአጠቃላይ ጤናማ ሆነው ሊታዩ ቢችሉም የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ፡-
- በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚስተዋሉ ለውጦች፣
- ያልተለመደ አይነት እንቅልፍ፣
- በአመጋገብ ላይ የሚታዩ ለውጦች (የምግብ ፍላጎት መቀነስ)፡፡
እንዴት መከላከል ይቻላል?
በቂ (አስተማማኝ) የእንቅልፍ ልምዶች፣
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ (ማጨስን ማስወገድ፣ መደበኛ የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ፣ ጡት ማጥባት፣ …)፣
ክትባቶች (ህፃናትን ሁሉንም የሚመከሩ ክትባቶችን ማስከተብ)፡፡
ምንጭ፡-https://www.medicoverhospitals.in/
(ሜዲከቨርሆስፒታልስ ዶት ኢን)
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም