የገጠር ሠርግ ትዝታዬ

0
87

በትዝታ ፈረስ ሽምጥ እየጋለብሁ ልጅነቴን ካሳለፍሁባት፣ ትውስታዬን ካኖርሁባት ከደጋማዋ ጽዮን ማርያም ሰናፍጭ ከምትባል መንደር ደርሻለሁ። ጽዮን ማርያም ከደብረ ማርቆስ ከተማ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ፈጠን ብሎ ለተጓዘ ሰው በግምት እስከ ሦስት ሰዓት ከሚወስድ የእግር ጉዞ በኋላ የምትገኝ ቦታ ናት።

ሰናፍጭ በምትባለው የገጠር መንደር በልጅነቴ አታሞ (ከበሮ) በተመታበት ቤት ቀርቼ አላውቅም። አያሌ ኮረዶች እና ጎረምሶች በጋብቻ ሲጣመሩ ቆሜ አጨብጭቤ ድሬአለሁ። አሁን ሳስታውስ በክብር እንደተጠራ ሽማግሌ ሠርግ በሚሠረግበት ቤት ከእሮው (ከዋዜማው) ጀምሮ ቀድሜ ነበር የምገኘው። ታዲያ የልጅነቴ ትዝታ ዛሬ ላይ የጎጃምን የሠርግ ሥርዓት መለስ ብዬ እንዳይ ቀሰቀሰኝ።

ሠርግ የወጣቶች የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ፣ ለወላጆች ደግሞ የልጆችን አዱኛ ማያ መነፅር ነው። በጎጃምም የልጁን አዱኛ ለማየት ያሰበ ወላጅ በተለይም የወንድ ልጅ አባት እና እናት ስለልጃቸው የጋብቻ ሁኔታ ቁጭ ብለው ይመክራሉ። ልጃቸው ለአዱኛ መድረሱን፣ ከማን ዘር ተጋቡ መኾን እንዳለባቸው፣ የሠርግ ወጭን የሚሸፍን ምርት ስለመኖሩ በዝርዝር ከተወያዩ በኋላ ልጃቸውን ለመዳር ይወስናሉ።

የወንድ ወላጆች ወደ ሴቷ ወላጆች ሽማግሌዎችን ይልካሉ፣ ሽማግሌዎቹ ከሴት ወላጆች ቤት ሲደርሱ እንዴት አደራችሁ፣ እንዴት ዋላችሁ ብለው ከደጅ ይቀመጣሉ። የሴት ወላጆችም ምንድን ነው ነገሩ? ሲሉ ይጠይቃሉ። ሽማግሌዎችም ስለጋብቻ ጥየቃው ያስረዳሉ፤ የሴት ወላጆችም ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ እንምክርበት ብለው ሽማግሌዎችን ይመልሳሉ። ወላጆችም ቁጭ ብለው ስለመጣው ተጋቡ ዘር፣ የጠንካራ ገበሬ ቤተሰብ ስለመኾኑ፣ ስለልጁ ቁምነገረኛነት፣ ስለመደገስ አቅማቸው ይመክራሉ፤ ይወስናሉ።

ሽማግሌዎች ስለጋብቻው መልስ ለማግኘት ሁለት ጊዜም፣ ሦስት ጊዜም እልፍ ሲልም እስከ አራት ጊዜ ሊመላለሱ ይችላሉ። በጎጃም ባሕል የሴት ወላጆች በአንድ ጊዜ እሺ፣ አበጀ ብለው የሽማግሌዎችን ጥያቄ መቀበል እንደነውር ስለሚቆጠር የሽማግሌዎች መመላለስ የግድ ነው። ከብዙ መመላለስ በኋላ ሽማግሌዎቹ ከሴት ወላጆች እሺ! ይሁን የሚለውን መልስ ለወንድ ወላጆች ያበስራሉ። የልጆቹ ወላጆችም ተገናኝተው ሠርጉ መቼ እንደሚኾን ቀን ይቆረጥለታል፣ “ቀጣር” ይባላል። የሠርጉ ዝግጅት በሁለቱም ወገን ያኔ ይጀመራል።

በገጠራማው የጎጃም አካባቢ ሠርግ ለወላጆች ብቻ “ራሳቸው ይወጡት” ተብሎ የሚተው አይደለም። ይልቁንም የቅርቡም የሩቁም ዘመድ ወሬውን እንደሰማ አንድ እንስራ ጠላ፣ ሁለት እንስራ ጠላ (ግማሽ አቆልቋይ) ወይም አንድ አቆልቋይ (አራት እንስራ ጠላ ከመቶ እንጀራ ጋር) እይዛለሁ እያለ ለባለጉዳዩ ይናገራል። ባለጉዳዩም ሠርጉ ስንት አቆልቋይ እንደሚወስድ ገምቶ እና ተረፍረፍ አድርጎ ይደግሳል።

መድረሱ አይቀርምና፤ የሠርጉ ቀን ይደርሳል። የእሮው ‘ለት (በዋዜማ) ዘመድ አዝማዱ ይሰባሰባል። ሁነኛ ሰው ተመርጦ በጠዋት የመንደሩን ነዋሪዎች በየቤታቸው እያንኳኳ “አያ እገሌ ልጄን መርቁልኝ” ብሏል እያለ ይጠራል።

ቤተ ዘመዱ በጠዋቱ በአንድ በኩል ዳሱን ይጥላል (ይሠራል)፤ በሌላ በኩል የሙሽራውን ጫጉላ ያዘጋጃል። ዳሱ እና ጫጉላው እንደተሠራ ፊሪዳ (የበሬ እርድ) ይጣላል። ፊሪዳው ላይ የሚገኙ የቅርብ ዘመድ እና ከመንደሩ የተመረጡ ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው። ለፊሪዳ የተባለው አቆልቋይ ይቀርባል፣ ቅቤው ተሰልሶ በቁርጥ ስጋ (ጉማ) ይበላል። ቁርጥ ስጋ በአካባቢው “ጉማ” ተብሎ ነው የሚጠራው። ተሰቅሎ የኖረው አታሞውም (ከበሮ) ይወርድና ስብ (ጮማ) ተቀብቶ ጥሩ ድምፅ እንዲያወጣ በፀሐይ ይሞቃል።

ለእሮው (ዋዜማው) አቆልቋይ የያዙ ሰዎች ስጋ ይሰጣቸውና ወጥ ይሠራሉ፣ የተጠሩትን የመንደሩን ነዋሪዎች ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ። ፀሐይ ዘቅዘቅ ስትል ወደ አስር ሰዓት ገደማ ጥሪ የተደረገላቸው የመንደሩ ነዋሪዎች ወደ ሠርጉ ቤት ይመጣሉ። አስተናጋጆች እየተቀበሉ በየአቆልቋያቸው ያስቀምጧቸዋል። ጠላው ይቀርባል፣ እንጀራው ይበላል፣ ይመረቃል፣ ከዚያማ አሼሼ ገዳሜ (ዘፈን) ይጀመራል።

የመንደሩ ሰው ፀሐይ የሞቀውን፣ በስብ የጠገበውን አታሞ እየመታ ሌሊቱን ሙሉ ሲደነክር (ሲጨፈር) ያድራል። የላብ መተኪያ በሚል አሳላፊ ሌሊቱን ሙሉ ወገቡን አስሮ ጠላ ሲቀዳ፣ ደካሪው ሲጠጣ ነው የሚያድረው።

ጠዋት የሠርጉ ‘ለታ የመንደሩ ወጣቶች፣ ልጃገረዶች እና ልጆች ይሰባሰባሉ። ፈረስ ይዘጋጃል፣ አንድ አስር እንጀራ በድቁስ (በአዋዜ) ተቀብቶ፣ በጽዋ ድፍድፍ ተይዞ ሙሽራው ወይም ሙሽሪት በፈረሱ ላይ ተቀምጦ/ጣ የሆም አበባዬ የሆም እየተባለ እየተዘፈነ ጉዞ ይጀመራል።

ወዴት? በብዛት ወንዝ አካባቢ የሚበቅል ሆማ የሚባል ለምለም ዛፍ አለ። እኔም በአደግሁባት ጽዮን ማርያም ይሄ ዛፍ ነበረ። እናም ሙሽራው/ዋን ሆማ ወደ አለበት ዛፍ ይዘን ሄደን ሦስት ጊዜ እንዞራለን። ከዚያ በጽዋ ያለውን ድፍድፍ ሙሽራው/ዋ ወርውሮ/ራ በሆማው ዛፍ ይሰበራል። ጽዋው እንደተሰበረ ወዲያውኑ በአዋዜ የተቀባውን እንጀራ ሙሽራው/ዋ እንደቀመሰ/ች ከተሸከመችው ልጃገረድ አናት ላይ እንዳለ እንሻማዋለን።

በእጃችን ጨብጠን የያዝነውን እንጀራ እየበላን እና “የሆም አበባዬ የሆም…” እያልን እየዘፈን ወደ ቤት እንመለሳለን።

ከቤት እንደተመለስን ከገብስ የተዘጋጀ ገንፎ (ስልቅ ይባላል) እየተገነፋ ይጠብቀናል። ሙሽራውን/ዋን ከቤት አስገብተን ትንሽ እንደክራለን (እንጨፍራለን)። ትዝ የሚለኝና ያኔ የማይገባኝ ነገር የሙሽራው/ዋ እናት ይዘነው የመጣነውን የሆማ ቅጠል በወንፊት ላይ አድርጋ፣ ከአናቷ ላይ አስቀምጣ የምትደክረው (የምትጨፍረው) ነው። አሁን ለምን ብዪ ሽማግሌ ስጠይቅ “ጋብቻው የለመለመ ይሁን” ብላ እናት ስትመኝ ነው አሉኝ።

በገንፎ ላይ የሚታደሙት ሆማ ቆረጣ የሄዱት ህፃና ልጆች፣ ልጃገረዶች እና ወጣቶች ብቻ ናቸው። ከዳሱ ቁጭ እንልና የስልቁን ገንፎ ቅቤው እየተንጠፈጠፈ ጥግብ እስክንል እንበላለን። ጠገብ ስንል ገንፎውን እያድቦለቦልን (ክብ እያደረግን) እንወራወራለን፣ እንመታታለን። ያኔ እናቶች እንደጠገብን ስለሚረዱ የተርፈውን ገንፎ ቶሎ ብለው ያነሱታል።

ስምንት፣ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ሠርገኛ (አጃቢ) ይገባል (ይሰባሰባል)። ሙሽራው ዝግጅት ያደርጋል። እንደ ከተማው ሦስት፣ አራት ሚዜ አያስፈልገውም የገጠር ሙሽራ። አንድ “አሳሳች” የሚባል በአካል ከሙሽራው ጋር የሚቀራረብ እና የቅርብ ጓደኛ ከአጠገቡ ይኾናል። ለሠርገኛ የተዘጋጀው አቆልቋይ ይቀርባል፣ ይበላል፣ ይጠጣል።

ከተበላ፣ ከተጠጣ በኋላ ሙሽራው ከፈረስ ላይ ወጥቶ ሰላሳ፣ አርባ የሚኾን ሠርገኛ እየተከተለ ወደ ሙሽራዋ ቤት ይሄዳሉ። የሙሽራዋ ሀገር ሁለት፣ ሦስት ሰዓት በእግር ሊያስጉዝ ይችላል። ሠርገኛው ሙሽራውን ይዞ ከሙሽሪት ቤት እንደደረሰ ከቤቱ በቅርብ ርቀት ሰብሰብ ብሎ ቁጭ ይላል።

ሙሽራው መምጣቱ በሙሽሪት ቤት እንደተሰማ ሽማግሌዎች ይላኩና ሙሽራውን ወደ ዳስ እንዲገባ ይጋብዙታል። “አናስገባም ሠርገኛ” የሚባለው ባሕላዊ ትንቅንቅ ይጀመራል። ሠርገኛ ፈንቅሎ ገብቶ ሙሽራዋን ይዞ ይወጣና ከዳስ ይቀመጣሉ። ለሙሽራ የተዘጋጀው አቆልቋይ (ሌማት) ቀርቦ ይበላል። ለሙሽራ የሚቀርበው ሌማት በጥሩ ባለሙያ የተዘጋጀ የተመረጠ ጠላ እና ጣፍጦ የተሠራ የዶሮ ወጥ ነው።

(ደመወዝ የቆዬ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here