ድጋፍ ለሚገባው ማድረግ

0
42

ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? አዲሱ የትምህርት ዘመን እንዴት ነው? ልጆች በዚህ ጽሑፍ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ስለሚደረግ ድጋፍ እንነግራችኋለን::

መምህር አወቀ ጌትነት በባሕር ዳር ከተማ ዐጼ ሠርፀ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ናቸው:: መምህር አወቀ ለዐይነ ስውራን ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ:: ከድጋፎቻቸው መካከል መጻሕፍትን አንብበው በስልክ ይቀርጹላቸዋል፣ በተለያዩ የትምህርት ጉዳዮች ላይ ያስረዷቸዋል እንዲሁም ያማክሯቸዋል::

መምህር አወቀ እንደሚሉት በቀድሞውም ሆነ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዐይነ ስውራንን ያማከለ የመማሪያ መጸሐፍም ሆነ የማስተማር ሥነ ዘዴ የለም:: የብሬል (ዐይነ ስውራን ማንበቢያ) የተወሰኑ መጻሕፍት ያሉት እስከ ስድስተኛ ከፍል ብቻ ነው:: ይህን ታሳቢ በማድረግ የንባብ ፕሮግራም አውጥተው ተማሪዎቹ የትምህርት ክፍለ ጊዜያቸውን በማይሻማ መልኩ ያነቡላቸዋል:: ንባቡ በስልክ ይቀረጻል፤ ወደ አማርኛ የሚተረጎመው ይተረጎማል፤ ማብራሪያ ይሰጣል:: በዚህ ሂደት ለሁለት ሰዓታት ሁለት የተለያዩ የትምህርት ዓይቶችን ይሸፍናሉ:: ተማሪዎቹ እንደፈለጉ ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ ውይይትም ይኖራል::

ዐይነ ስውራን ተማሪዎቹ የተቀረጸውን ድምጽ ቤታቸው ሆነው ዐይናማው መጸሐፉን እንደሚያነበው እንደገና ማጥናት ይችላሉ፤ የቤት ሥራቸውን ይሠራሉ፤ ለፈተና ይዘጋጃሉ፤ ይህ የመማር ማስተማር ሂደት ውጤት አይሰጥበትም፤ እንዲሁም የቀረ ተማሪ አይቀጣበትም እንጂ ከመደበኛው ትምህርት የተለየ አይደለም ይላሉ መምህር አወቀ:: የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ቁጥርን ጨምሮ ምልከታን የሚፈልጉ ትምህርቶችን ለመስጠት አስቸጋሪ ነው::

ቁጥሮች ቀርተው ምልከታ የሚያስፈልጋቸውን በመዳሰስ በማሳየት የስተምሯቸዋል:: ለምሳሌ በስነ ሕይወት ትምህርት የቅጠል ክፍሎችን ለማስተማር ቅጠሉን በእጅ እያስዳሰሱ ምን ምን እንደሚባሉ ይነግሯቸዋል፤ ቢያደክምም ይይዙታል:: የማንበቢያ ክፍሉ ድምጽ ሲቀረጽ እንዳይበላሽ በጥንቃቄ የተዘጋጀ ነው:: ድምጹን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎች ላሉ ዐይነ ስውራን ተማሪዎችም ያጋሩታል:: ለምሳሌ በደብረ ማርቆስ፣ ሞጣ፣ ደብረ ታቦር እና ሌሎች አካባቢዎች ተልኮላቸው እንደሚጠቀሙበት መምህሩ ነግረውናል::

ተማሪ አበባ ዘላለም በዐጼ ሠርፀ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት::

የመምህር አወቀ እገዛ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ተናግራለች:: አጠቃላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ እና መማሪያ መጻሕፍቱ በተግባር ላይ የተመሠረቱ በመሆኑ አሳታፊነቱን አድንቃለች:: ሆኖም መጸሐፉ ነገሮችን ለማስረዳት ለተጠቀመባቸው ሥነ ሥዕሎች ያሉት ማብራሪያዎች ዐይነ ስውራንን ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም ትላለች፤ ስለሆነም መምህር አወቀ ከንባቡ ባሻገር ስዕላዊ መግለጫ በደንብ ስለሚሰጥ ትምህርቶቹን ከአይናማዎች እኩል ለመረዳት እንዳገዛት ነግራናለች:: ልጆች በትምህርት ቤታችሁ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ካሉ ማገዝ እንዳለባችሁ ከዚህ ጽሑፍ ተምራችኋል አይደል?::

 

ተረት

ፈረስ አበራለሁ

አንድ  ጊዜ  የንጉሡ  ሁለት  ባለሟሎች ባጠፉት ጥፋት  ዙፋን  ችሎት  እንዲቀርቡ ይታዘዛሉ፡፡ ከዚያም ያጠፉት ጥፋት ፍርዱ እንደሚከተለው ተነገራቸው፡፡

ንጉሡ፤ ተደላድለው ዙፋናቸው ላይ ከተቀመጡ በኋላ፡- “ያጠፋችሁት ጥፋት ፍፁም ምህረት የማይደረግለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለታችሁም  በሞት እንድትቀጡ ተወስኗል፡፡ ይግባኝ ማለት ወይም የመሰላችሁን አስተያየት መስጠት ትችላላችሁ” አለ፡፡

ከሁለቱ ፍርደኞች አንደኛው ንጉሱ ከልብ የሚወድዱት ፈረስ እንዳላቸው ስለሚያውቅ፤

“ንጉሥ ሆይ! አንድ ዓመት ይሰጠኝ እና የሚወድዱት ፈረስዎን በአየር ላይ እንደ ወፍ መብረር ላስተምረው፡፡ ይህንን ካደረግሁኝ ነብሴን ይምሩልኝ ከሆነ ማስተማሬን ልቀጥል” አለና ተማጠነ፡፡

ንጉሡ፤ በአንድ ወገን የሚወድዱት ፈረሳቸው መብረር መቻል፣ በሌላ በኩል የጥፋተኛውን ፍርድ መሻር፣ በጣም ካማለላቸው በኋላ፣ በአለም ላይ የሚበር ፈረስ ያለው ንጉስ እሳቸው ብቻ መሆናቸውን አሰቡና ልባቸውን ሞቅ አላቸው፡፡ በመጨረሻም፤ “ይሁን፤ ፈረሴን በአየር ላይ መብረር አስተምርልኝ! አንድ ዓመት ሰጥቼሀለሁ” አሉት፡፡

ይህን ወስነው እንደሄዱ ሁለቱ ሰዎች መወያየት ጀመሩ፡፡ ሁለተኛው ፍርደኛ “ስማ፤ አብደሃል እንዴ? ፈረስ በአየር ላይ በምንም አይነት እንደማይበር ታውቃለህ፡፡

በምን ተአምር ፈረሱን በአየር መብረር ልታስተምረው ነው? አንድ አመት እሩቅ መሰለህ? የማይቀረውን ነገር ቀኑን ማስተላለፍስ ለምን ይጠቅምሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ አንደኛው ፍርደኛም፤ “ይህንን ያደረግሁት በአራት መንገድ ነፃ እወጣለሁ የሚል ተስፋ ታይቶኝ ነው” አለና መለሰ፡፡ “አራት መንገድ? ለመሆኑ ንጉሡን የሚያሳምን አንድስ መንገድ ይገኛል? ስማ፤ ንጉሱ የሚለቅቁህ ፈረሳቸውን ለማብረር ከቻልክ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ምን ምን መንገድ ታይቶህ ነው?”

አንደኛው ፍርደኛም እንዲህ ሲል መለሰ፡- “አንደኛ፤ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ንጉሱ እራሳቸው ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛ፤ እኔ እራሴ ልሞት እችላለሁ፡፡ ሦስተኛ፤ ፈረሱ ሊሞት ይችላል፡፡ አራተኛ፤ ማን ያውቃል፤ ምናልባት ፈረሱን በአየር ላይ መብረር ላስተምረው እችል ይሆናል” አለ ይባላል::

 

ይሞክሩ

በዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ማን ይባላል?

በአፍሪካ ትልቁ ግድብ ማን ይባላል?

በሥርዓተ ፀሐይ ትንሿ ፕላኔት ምን ትባላለች?

 

መልስ

ዓባይ

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ

ፕሉቶ

 

ነገር በምሳሌ

የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው-

እያለው እንደሌለው የሚቸገር፤

 

ሰው በሀገሩ ወይራ ነው-

ያለሀገሩ ግን ጉሎ ነው ሰው የበለጠ ክብር የሚኖረው በሀገሩ ውስጥ ነው::

 

በጋ ታካች ክረምት ቧጋች-

ማንኛውም ተግባር መከናወን ያለበት በጊዜው ነው::

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here