የሩቦንዶ ደሴት ብሔራዊ ፓርክ በታንዛኒያ ቪክቶሪያ ኃይቅ ላይ ነው የሚገኘው:: ፓርኩ በአፍሪካ በስፋቱ ቀዳሚ የደሴት ላይ ፓርክ ነው:: ስፋቱም 456 ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል::
ሩቦንዶ ደሴት በ1960 ዎቹ መጀመሪያ በእንስሳት እና እፅዋት ጥብቅ ስፍራነት ተከልሎ በ1977 እ.አ.አ በብሔራዊ ፓርክ ሆኖ ህጋዊ እውቅና ተሰጥቶታል:: በደሴቱ ላይ የነበሩ በዓሳ ማስገር እና የሙዝ ተክል በማልማት ይኖሩ የነበሩ 400 የሚሆኑ ኗሪዎች ወደ አጐራባች የብስ እንዲሰፍሩ በመደረጉ አሁን ላይ ኗሪዎች የሉትም::
በ1966 እስከ 1969 እ.አ.አ ኘሮፌሰር በርናርድ ግሪዝሚክ የተሰኙ የእንስሳት ጥበቃ ማህበር ኃላፊ ከአፍሪካ ለሰርከስ ትርኢት ወደ አውሮፓ የተወሰዱ 17 ቺምፓንዚ ወይም የዝንጀሮ ዝርያዎች ወደ ፓርኩ እንዲለቀቁ አድርገዋል:: በአንድ ዓመት ውስጥ ቀጣናውን ተላምደው ቁጥራቸው ከ40 በላይ መዝለቁም በድረገጾች ተገልፆል::
ደሴቱ ላይ በሚገኘው ፓርክ በህገወጥ ንግድ ሲጓጓዙ የተያዙ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ለአብነት የሜዳ ፍየል፣ ጉሬዛ፣ ቀጭኔ፣ ዝሆን፣ አውራሪስ፣ በቀቀን ተጠልለው እንዲላመዱም ተደርጓል::
ደሴቱ በቪክቶሪያ ኃይቅ ላይ እንደመገኘቱ ከ300 በላይ ዓዕዋፍ ይገኙበታል:: የቪክቶሪያ ኃይቅ አዋሳኝ ዳርቻው የብርቅዬ ዓሳዎች መናኽሪያ መሆኑም በድረገፆች ለንባብ በቅቷል::
ሩቦንዶ በእሳተ ገሞራ ወይም ከቪክቶሪያ ኃይቅ ስር በተነሳ እሳተ ገሞራ የተፈጠሩ ሦስት ጉብታዎች ወይም ከፍ ያሉ አቀበቶች አሉት:: ኮረብታዎቹ በቀጭን ልሳነ ምድር የተያያዙ ሲሆን ከፍተኛውም የማሳ ኮረብታ ከባህር ጠለል በላይ 1486 ሜትር ተለክቷል::
ፓርኩ በእግር ተጉዘው ወይም በመጠለያ ጣቢያዎች ቆይተው ለሚጐበኙም በታንዛኒያ የብሔራዊ ፓርክ ባለስልጣን ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራቱን ይወጣል::
በጀልባ ተጓጉዞው ለሚዝናኑ እና ለሚጐበኙ ጥበቃ እና የጉብኝት ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ጥረት ያደርጋሉ- ባለሙያዎች::
ሩቦንዶ ብሔራዊ ፓርክ ለመድስ ከዳሬሰላም፣ ከዛንዚባር፣ ከአሩሻ በአውሮኘላን ተጉዞ መድረስ ይቻላል::
ለዘገባችን ዴይሊኒውስ ዶት ኮም እና ኬዩ ቢ ደብሊው ፋይቭ ሳፈሪ ድረ ገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም