የፋይዳ ፋይዳዎች

0
78

ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ አካላዊ /ባዮሜትሪክ/ እና የሥነ ሕዝብ /ዲሞግራፊክ/ መረጃን ከነዋሪዎች በመሰብሰብ አንድን ሰው በልዩ ሁኔታ በመለየት (ትክክለኛ መረጃ በመስጠት)፣ ለሁሉም አገልግሎት ሰጪዎች ማንነትን በማረጋገጥ እና በኤሌክትሮኒክ መልኩ ደንበኞቻቸውን ማወቅ የሚያስችል ታዓማኒነት ያለው የዲጂታል ማንነት ምዝገባ ሥርዓት ነው።

አቶ ኦላና አበበ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ከፍተኛ አማካሪ ናቸው፤ እርሳቸው እንዳብራሩት ፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያን ከሌሎች ልዩ የሚያደርጉት መገለጫዎች  አሉት፡፡ አንድ ሰው አንድ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሲሆን ዜጎች የፋይዳ ቁጥር የሚባለውን ባለ 12 እና 16 አሀዝ /ዲጂት/ መለያ ቁጥር በካርድ፣ በወረቀት ወይም በስልክ በማሳየት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት ነው፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ በልዩ ፋይዳ ቁጥሩ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ጋር ለማስተዋወቅ እና ከክልል ክልል ለማስተሳሰር ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ባሕር ዳር ላይ ያለውን ሥርዓት አዳማ፣ አዋሳ፣ መቀሌ … ካለው ሥርዓት የሚያስተሳስር ወጥ የሆነ የግንኙነት መረብን ይፈጥራል፤ ይህ መሆኑ ማንኛውንም አገልግሎት በየትኛውም ቦታ ለማግኘት እና ሌሎች ተግባራትንም ለማግኘት ይጠቅማል፡፡

ግላዊ መረጃን ምሥጢራዊ አድርጐ የሚጠብቅ መሆኑን ያነሱት ከፍተኛ አማካሪው፤ አስተማማኝነቱም ከሌሎች መታወቂያዎች ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፤ በዚህም እንደ ሀገር የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ በመሆኑ ዲጂታል መታወቂያም አዋጁን የጠበቀ፣ ያከበረ እና በዚያ አግባብ የሚመራ ሥርዓት እንደሆነ አክለዋል፡፡

አቶ ኦላና እንዳሉት ሰዎች ሲመዘገቡ የሰጡት ማስረጃ ባለቤትነቱ የተመዝጋቢው ነው፤ እያንዳንዱን መረጃ ማየት ሲፈለግም የመታወቂያው ባለቤት ተጠይቆ በፈቃዱ የሚያጋራው እንጂ ባለሙያ ምዝገባውን ካካሄደ በኋላ የመዘገበውን መረጃ የሚያይበት ሥርዓት አይደለም፡፡

ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያውን በዜግነት ኢትዮጵያዊ ሆነም አልሆነም በሀገሪቱ ነዋሪ እስከሆነ ድረስ የመኖሪያ ወይም የሥራ ፈቃዱን በማየት አገልግሎቱ ይፈቅድለታል፤ ከዕድሜ አኳያም ከተወለዱ ጀምሮ የምዝገባ ሥርዓቱ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዜሮ እስከ አምስት ዓመት ያሉ ሕፃናት በሥነ ሕዝብ /ዲሞግራፊ/ መረጃ ብቻ የምዝገባ አገልግሎት ያገኛሉ፤ ከአምስት ዓመት በላይ ያሉ ልጆች ደግሞ በሥነ ሕዝብ እና አካል ላይ ያሉ መረጃዎችን /ባዮሜትሪክ/ በመውስድ ይሰጣቸዋል፡፡

ከፍተኛ አማካሪው እንዳሉት  በተለያዩ ጊዜያት ሕዝብን ተጠቃሚ እና ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፤ በግብርናው፣ በጤናው፣ በትምህርቱ… የሚከናወኑ ተግባራት በዲጂታል ሥርዓት ካልታገዙ ሥኬታማ የመሆን ዕድላቸው ጠባብ ነው፡፡ ይህን አገልግሎት በማሳለጥ ከሕግ አኳያ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ደግሞ በየተቋማቱ የመልካም አስተዳደር  አገልግሎት ለማግኘት የሚገጥመውን እንግልት እና ምልልስ ማስቀረት ይገባል፤ ለዚህም የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት መሠረት ይሆናል፡፡

እንደ ሀገር ወደ ዲጂታሉ ዓለም ለመግባት አራት አስቻይ ነጥቦች ላይ መሥራት ይገባል፤ እነዚህም ኢነርጂ (መብራት፣ ኀይል)፣ ዳታ (ኮሙኑኬሽን)፣ የክፍያ አፈፃፀም /ዲጅታል ፔይመንት/ እና አሁን በሀገሪቱ እየተተገበረ የሚገኘው ፋይዳ / ድጂታል መታወቂያ ናቸው፡፡  እነዚህን ማከናወን ካልተቻለ ወደ ዲጂታሉ ዓለም ለመግባት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡

ሀገር ካላት ሀብት ዋናው ሕዝብ ነው፤ በመሆኑም እንደ ሀገር ያለውን ሀብት መዝግቦ እና አውቆ አገልግሎት መስጠት ይገባል፡፡ የፋይዳ መታወቂያ ደግሞ አንድ ሰው አንድ መሆኑ የሚረጋገጥበት ሥርዓት በመሆኑ ጥቅሙ የጎላ ነው፤ ለማሳያም ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ አጀንዳ አንዱ ምስሶ /ፒላር/ ሲሆን የተጀመረውን ተግባር (የኢኮኖሚ ማሻሻያ) ለማሳካት የሚያስችል መርሀ ግብር ነው፡፡ ይህን ብቻ በማሳካትም ሰባት በመቶ ዓመታዊ ጥቅል ገቢ /ጂ ዲ ፒ/ እንደ ሀገር ማግኘት የሚያስችል ሥርዓት ነው፡፡

የፋይዳ መታወቂያ ሥርዓት በአንድ ሀገር ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፤ ሀገራዊ ልማትን በአግባቡ ለማቀድ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ ወንጀልን ለመከላከል፣ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን ለመፍታት እና አካታችነትን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሥርዓቱ አካላዊ መረጃ ላይ ተመሥርቶ የሚሰጥ እና አንድ ሰው አንድ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ያሉት አቶ ኦላና፤ አንድ ሰው ሁለትና ከዚያ በላይ በተለያዬ ሥም መታወቂያውን ማውጣት እንደማይችልም አረጋግጠዋል፡፡

የፋይዳ ሥርዓት ሰው ተኮር ሆኖ ሰዎችን ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለውን እንግልት ለመፍታት የተዘጋጀ መርሀ ግብር በመሆኑ  በተለይ ማንነታቸውን በሕጋዊ መንገድ በማረጋገጥ መሠረታዊ የዜግነት መብቶቻቸውን ለማግኘት ያስችላል፤ ማንነትን ለማረጋገጥ ያስፈልግ የነበረውን የሰነዶች ማገላበጥ በማስቀረት ለፈጣን አገልግሎት ምቹ ነው፡፡ የተቋማትን የተንዛዛ አገልግሎት ቀልጣፋ ያደርጋል፤ የተሳሳተ የማንነት መረጃ ይዘው የሚቀርቡ የአገልግሎት ተጠቃሚዎችን መረጃ ለማጣራት ቀላል ስለሚሆን መጭበርበርን ይከላከላል፤ ዜጎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲፈልጉ ማንነትን ለማረጋገጥ ቀላል ይሆናል፤ በመረጃ እጥረት ምክንያት ያልተገባ የአገልግሎት አሰጣጥ አይኖርም፤ በሀሰተኛ የማንነት መረጃ የትክክለኛ ዜጎችን ሀብት፣ ንብረት… መውሰድን ያስቀራል፡፡ የወረቀት ላይ አሠራርን በማስቀረት የሰው ኀይል ብክነትን ይቀንሳል፡፡

ልጆች ሀገር ተረካቢዎች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ኦላና በትልልቅ ተቋማት ሲያገለግሉ ወይም ትምህርት ላይ እያሉ የውጭ የትምህርት ዕድል ካገኙ የሥም እና የትውልድ ቀን ሥህተት እንዳይፈጠር ፋይዳ መታወቂያ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም አገልግሎትን በማሳለጥ ከገቢዎች፣ ከመሬት ነክ ጉዳዮች /ካርታ እና ፕላን/፣ ከገንዘብ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ማጭበርበሮችን ያስቀራል፡፡

ፋይዳ በርካታ አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ጠቀሜታዎች እንዳሉት የጠቆሙት ዋና አማካሪው፤ በቀጣይ ዜጎች  ወደ ተቋማት ሳይሄዱ ከቤታቸው ወይም ባሉበት ቦታ ሆነው ሳይንገላቱ በስልክ አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  ስለሆነም  ሁሉም ሰው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

እኛም ዘገባችንን የፋይዳ  ብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓትን ቀድመው ከተገበሩ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችውን የኢስቶኒያን ተሞክሮ በማጋራት መቋጨት ወደናል። ጂቢጂ ዶት ኮም (gbg.com) እንደዘገበው የኢስቶኒያ ዜጎች ዲጂታል መታወቂያቸውን በመጠቀም ከ99 በመቶ በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀጥታ /ኦንላይን/ ማግኘት ችለዋል። በዚህም ኢ አይ ዲ (EID) ተብሎ በሚጠራው የኢስቶኒያ ዲጂታል መታወቂያ አማካኝነት የሀገሪቱ ዜጎች ከ600 በላይ አገልግሎቶችን እንደሚያገኙ መረጃው አክሏል። ለአብነትም ዜጎች በቤታቸው  ወይም ባሉበት ቦታ ሁሉ ሆነው በኦንላይን ምርጫ መሳተፍ፣ የግብር ክፍያን መፈጸም፣ የጤና አገልግሎትን ማግኘት  እና  የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ማድረግ ዲጂታል  መታወቂያ  ካስገኘላቸው ዋና ዋናዎናቹ  አበርክቶዎች መካከል ናቸው፡፡ ቢሮክራሲን (የተንዛዛ አሠራርን) የሚያስቀር በመሆኑም  ኢስቶኒያውያን በዓመት በአማካይ አምስት የሥራ ቀናት መቆጠብ እንዳስቻላቸውም መረጃው ያመላክታል።

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here