ስም ማጥፋት

0
78

ሴጅ ጆርናልስ ገጽ “የስም ማጥፋት“ የሚለው ቃል በ20ኛው ክፍለ ዘመን በአሜሪካ ቢመጣም፣ የዚህ ተግባር ምሳሌዎች በጥንት ዘመን ይገኙ ነበር ይላል። በታሪክ የሮም ነገሥታት፣ የካቶሊክ ጳጳሳት፣ የፈረንሳይ ነገሥታት፣ የሶቪየት ፖለቲከኞች፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና የንግድ ሰዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ ሙከራ ሰለባ መሆናቸውን ያወሳል።

“የስም ማጥፋት ዘመቻ ማለት የአንድን ሰው  ስምና ክብር ሆን ብሎ ክፉኛ በመጉዳት የስኬት እድሉ አነስተኛ እንዲሆን የማድረግ ሙከራ ነው። ይህ ተግባር የሚፈጸመው በግለሰቦች ላይ እንጂ በቡድኖች ላይ አይደለም” በማለት ትርጉም ይሰጠዋል።

የስም ማጥፋት ዘመቻ በስነ ልቦናዊ አጠራሩ ካራክተር አሳስኔሽን ወይም የባህሪ ግድያ በመባልም ይታወቃል። ለዘመናት በፖለቲካ ውስጥ ተፎካካሪን ለማስወገድ ሲያገለግል ቆይቷል።

የባህሪ ግድያ በታሪክ የሰው ልጅ ሥልጣኔን ያህል ዕድሜ ያለው ጥንታዊ ስልት ነው። ዋና ዓላማው የተቃዋሚን ስምና ክብር በሕዝብ ፊት በማጉደፍ፣ ኃይሉንና ተጽዕኖውን ማዳከም ወይም ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ነው። ዘዴዎቹና መንገዶቹ ግን ከዘመን ዘመን ሲለዋወጡ ቆይተዋል። በጥንታዊት ሮም ሪፐብሊክ የስም ማጥፋት ዘመቻ የፖለቲካው ዋነኛ መሣሪያ ነበር። በፖለቲከኞች፣ በነገሥታት እና በጦር ጄነራሎች መካከል የተለመደ ስልት ነበር።

በሕዝብ ፊት በሚደረጉ ንግግሮች  ታላላቅ ተናጋሪዎች፣ ተቃዋሚዎቻቸውን በሕዝብ ፊት  በሙስና፣ በፈሪነት፣ በሥነ ምግባር ብልሹነት እና ሀገር በመክዳት ይከሱ ነበር። በሐሜትና ወሬም ስለ አንድ ፖለቲከኛ የግል ሕይወት የሐሰት ወሬዎችን በከተማው ውስጥ መንዛት የተለመደ ነበር።

በግድግዳ ላይ የሚጻፉ ጽሑፎች (ግራፊቲዎች) እና ተቃዋሚን የሚያንቋሽሹ ግጥሞች ይሰራጩ ነበር። የማስታወስ እቀባ የሚባልም ስልትም ነበር። ይህ በጣም ከባድ ርምጃ ነበር። አንድ ንጉሥ ወይም ፖለቲከኛ ከሥልጣን ሲወገድ ወይም ሲሞት፣ የጠላቶቹ ወገኖች ስሙ ከታሪክ እንዲሰረዝ ያደርጉ ነበር። ሐውልቶቹ ይፈርሳሉ፣ ስሙ ከሕዝብ መዝገቦች ላይ ይሰረዛል፣ ምስሉ ከሳንቲሞች ላይ ይፋቃል። ይህም ሰውየው በታሪክ ውስጥ እንዳልነበረ ለማስመሰል የሚደረግ ሙከራ ነው። በየትኛውም መንገድ ስሙ እንዲነሳ አይፈቀድም።

በመካከለኛው የስልጣኔ ዘመን  የፖለቲካ እና የሃይማኖት ኃይል የተቆራኘ ስለነበር፣ የስም ማጥፋት ዘመቻ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መልክ ነበረው ሲሉ የታሪክ መዛግብት ያስታውሳሉ።

የክህደት ክስ ማቅረብ ዋነኛው የማጥቂያ መሣሪያ ነበር። አንድን የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ተቀናቃኝ “ከሃዲ” ወይም “መናፍቅ” ብሎ መወንጀል፣ ከቤተክርስቲያን እንዲገለል፣ ሥልጣኑን እንዲያጣ አልፎ ተርፎም እንዲገደል ሊያደርግ የሚችል ተግባር ይፈጸም ነበር።

አንድን ሰው ከሰይጣን ጋር ተቆራኝቷል፣ አስማት ይጠቀማል ወይም ጠንቋይ ነው ብሎ መወንጀል በጣም የተለመደና ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ስልት ነበር።

የሥነ ምግባር ብልሹነት ሌላው ማጥቂያ ዘዴ ነበር። ነገሥታትንና ጳጳሳትን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተቃዋሚዎቻቸው በዝሙት፣ በስግብግብነት እና በሌሎች የሥነ ምግባር ጉድለቶች ይከሰሱ ነበር። ታሪካቸው እንዳይጠገን ሆኖ ይሰበራል።

ከህዳሴው እስከ ዘመናዊው ዘመን መጀመሪያ ባሉት ጊዜያት የሕትመት መሣሪያ መፈጠር የስም ማጥፋት ዘመቻን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋገረው። መረጃ በፍጥነትና በስፋት መሰራጨት ጀመረ።

በሺዎች የሚቆጠሩ በራሪ ጽሑፎች እየታተሙ ይሰራጩ ነበር። እነዚህ ጽሑፎች ብዙ ጊዜ ስም ሳይጠቀስ  የሚጻፉ ሲሆኑ፤ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን በከባድ ውንጀላዎች ያጠቁ ነበር።

ፖለቲካዊ የካርቱን ስዕሎች ተቃዋሚን በአስቂኝና በአዋራጅ መንገድ የሚያሳዩ ስዕሎች እየተለመዱ መጡ። የአንድን መሪ አካላዊ ገጽታ በማጋነን ወይም አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ በማሳየት ክብሩን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

በፕሮቴስታንት እና በካቶሊክ መካከል በነበረው የሃይማኖት ግጭት ወቅት ሁለቱም ወገኖች ይህንን ስልት በስፋት ተጠቅመውበታል። ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተክርስቲያን፤ ጳጳሱ ደግሞ በፕሮቴስታንቶች በስፋት ስማቸው ይጠፋ ነበር።

በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመናት የጋዜጦች፣ የመጽሔቶች፣ በኋላም የሬዲዮና የቴሌቪዥን መስፋፋት የስም ማጥፋት ዘመቻን የመንግሥታትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ መሣሪያ አደረገው።

የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማድረግ አንደኛው ዘዴ ነበር። በአምባገነናዊ ሥርዓቶች (ለምሳሌ በናዚ ጀርመን እና በሶቪየት ኅብረት) የስም ማጥፋት ዘመቻ የመንግሥት ፖሊሲ ሆነ። ናዚዎች አይሁዶችን የኅብረተሰብ ጠላት፣ ጥገኛ እና ዘር አርካሽ በማለት በስፋት በመወንጀል የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም ሕዝቡን አዘጋጅተዋል። በሶቪየት ኅብረት ደግሞ ስታሊን የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን የሕዝብ ጠላት እና ሰላዮች በማለት አስሯል፤ ገድሏል።

የፖለቲካ ዘመቻዎች ማድረግም እንዲሁ ጥቅም ላይ ከዋሉት ዘዴዎች መካከል ይጠቀሳል። የዲሞክራሲን መርህ በዋናነት የሚያራምዱ ሃገሮችም ቢሆን፣ በምርጫ ወቅት ተቀናቃኝን በግል ሕይወቱ፣ በገንዘብ አያያዙ ወይም በሀገር ወዳድነቱ ላይ ጥያቄ በማንሳት ስሙን ማጥፋት የተለመደ ሆነ።

“ኮሚኒስት” ብሎ መፈረጅም ለመጠቂያነት ውሏል። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በአሜሪካ ውስጥ አንድን ሰው “ኮሚኒስት” ነው ብሎ መወንጀል የአንድን ሰው የሥራና የማኅበራዊ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በቂ ነበር።

የስም ማጥፋት ዘመቻ ዓላማ በታሪክ ውስጥ ብዙም አልተለወጠም። የተለወጠው ቴክኖሎጂው፣ ፍጥነቱና የሚደርስበት የኅብረተሰብ ክፍል ስፋት ነው። ከሮማውያን የንግግር መድረክ እስከ ዛሬው የማኅበራዊ ሚዲያ ድረስ፣ የሰው ልጅ ተቀናቃኙን ለማሸነፍ ከተጠቀመባቸው በጣም ኃይለኛና አጥፊ መሣሪያዎች አንዱ ሆኖ ቀጥሏል።

ስም ማጥፋት የበርካታ ኃያላን ግለሰቦችን ውድቀት በማስከተል ዛሬ ላይ ስለ እነሱ ያለንን አመለካከት በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።  የሮም ንጉሥ  የነበረውን ካሊጉላን የታሪክ ድርሳናት እንደ ጨካኝ፣ ምህረት የለሽና እብሪተኛ አድርገው ይገልጹታል።

በእርግጥ እንደዚያ እንዳልነበር የሚተርኩ ድርሳናት አሉ። የባህሪው አስከፊ ገጽታዎች ምናልባትም የህይወት ታሪኩን በወገንተኝነት በጻፉ ተቃዋሚዎቹ ሆን ተብሎ የተጋነኑ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ ምንጮች አሉ። ጠላቶች ስሙን በሚገዙት ሕዝብ ዘንድ ለማስጠላት የፈጠራ ክፉ ስም ሰጥተውታል። የስም ማጥፋት ዘመቻ በተወሰኑ መንገዶች ታሪክን የቀረጸ ሲሆን የበርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ስም አጉድፏል።

ሀፍ ፖስት ድረገጽ “አንተ ንቁ፣ ስኬታማ ግለሰብ፣ የተወደድክ መሪ፣ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ተወዳጅ፣ ማራኪ ወይም የእነዚህ ሁሉ ገጽታዎች ባለቤት ከሆንክ፣ በሆነ ወቅት የስም ማጥፋት ዘመቻ ዒላማ መሆንህ አይቀርም” ይላል።

የስም ማጥፋት ቅናት ካደረባቸው፣ ከተቆጡ፣ ከተንኮለኞች፣ ከምቀኞች ሊመጣ የሚችል  ዘመቻ ነው።  የስም ማጥፋት   በአንድ ሰው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በጣም ከባድ፣ ጥልቅ እና ዘርፈ ብዙ ነው። ይህ ጥቃት የአንድን ሰው ስም ከማጥፋት አልፎ፣ ማንነቱን፣ ስነ-ልቦናውንና መላ ሕይወቱን የሚያናጋ ከባድ ዓይነት ውጤት  ሊያመጣ ይችላል።

በስነ-ልቦና እና በስሜት ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት አንጻር ከተመለክትነው ከፍተኛ ውጥረት እና ጭንቀት  ያመጣል። የስም ጥፋት ተጠቂው በየጊዜው በጥቃት ስር እንዳለ፣ ሰዎች እንደሚጠሉትና እንደሚያሙት ስለሚሰማው የማያቋርጥ ውጥረትና ጭንቀት ውስጥ ይገባል።

ይህ ደግሞ ወደ ድብርት ስሜት ሊከተው ይችላል። የተስፋ መቁረጥ፣ የሀዘን፣ ዋጋ ቢስነት እና የብቸኝነት ስሜት ተጠቂውን ሊሰማው ይችላል።

ከዚህ ቀጥሎ በራስ መተማመኑን ያጣል። ፍርሀት እና ጥርጣሬ ስሙ የሚጠፋ ሰው ሊገጥመው የሚችል ችግር ነው። ተጠቂው በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ሁሉ መጠራጠር ይጀምራል። ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ ሳይቀሩ በእሱ ላይ እንደተነሱበት ሊሰማው ይችላል። ይህም ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ያበላሻል።

በዚህ ምክንያት የማህበራዊ መገለል ስሜት ያድርበታል። ሰዎች ከእሱ ሲርቁና ሲያገሉት፣ ብቸኛና ማንም እንደማይረዳው ሆኖ ይሰማዋል። በተስፋ ማጣት ስሜት ራሱን በማጥፋት ሐሳብ ውስጥ ሰለባ ይሆናል።

የስም ማጥፋት ማኅበራዊ ጉዳትም አለው። ይህ ጉዳት የተጠቂውን ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ያበላሽበታል። ጓደኞች፣ የሥራ ባልደረቦች እና የቤተሰብ አባላት ሳይቀሩ በወሬው ተጽዕኖ ሥር ወድቀው ወይም ከችግሩ ለመራቅ ሲሉ ከተጠቂው ሊርቁ ይችላሉ።

ስምና ክብር መጉደፍም ሌላው ማህበራዊ ጉዳት ነው። ይህ ችግር አድጎ ከማኅበረሰቡ መገለልን ያመጣል። የሙያ እና የገንዘብ ጉዳት የስም ጥፋትን ተከትሎ ከሚመጡት ዋና ጉዳዮች ሌላው ነው። የስም ማጥፋት ዘመቻ የአንድን ሰው የሥራ ሕይወትና የገቢ ምንጭ በቀጥታ ያጠቃል። ይህን ተከትሎ የሙያ ሕይወት መበላሸት ሊገጥመው ይችላል። የገቢ ምንጭ ሲቋረጥ፣ ተጠቂውና ቤተሰቡ ለከፋ የገንዘብ ችግር ሊዳረጉ ይችላሉ።

ስም ማጥፋት አካላዊ ጉዳትም አለው። የእንቅልፍ እጦት፣ሥር የሰደደ ራስ ምታት፣ የሆድ ህመም፣ የደም ግፊት መጨመር፣ የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም እና ሌሎችም ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።

የባህሪ ግድያ በቃላት የሚፈጸም ቢሆንም፣ ጉዳቱ ግን  ከአካላዊ ጥቃት እኩል፣ አንዳንዴም ከዚያ የከፋ ነው። የአንድን ሰው ሰብዕና፣ ሕልም፣ ግንኙነት እና የወደፊት ተስፋ የሚሰብር አጥፊ መሣሪያ ነው። አንዴ ከተፈጸመ በኋላ የሚተወው ጠባሳ በቀላሉ የሚድን አይደለም። ቀስ በቀስ እንደሚገድል መርዝ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

የስም ማጥፋት ለማንኛውም ሰው በስራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ ወይም  በቤተሰብ ውስጥም ሊከሰት ይችላል።  ራስን ለመጠበቅ እና  ህይወትን በፈጠራ ባህሪ ላለመጉዳት መደረግ ያለባቸውን ነጥቦች ማስተር ካፒታል ገጽ አስፍሯል።

የመጀመሪያው ምላሽ አለመስጠት ነው። ምላሽ መስጠት ብዙውን ጊዜ ሁኔታውን ሊያባብሰው ይችላል። ለሚያጠቃን ሰው የሚፈልገውን ትኩረት ሊሰጠው ይችላል፣ እንዲሁም ራስን ጥፋተኛ ወይም ተከላካይ ሊያስመስል ይችላል። ከዚህ ይልቅ እየሆነ ስላለው ነገር እና ስለ እሱ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ ለማሰብ የተወሰነ ጊዜ መውሰድ ተገቢ ነው ይላል ገጹ።

ሁለተኛው እርምጃ ከምናምናቸው ሰዎች ድጋፍ መፈለግ ነው። ይህ ጓደኛ፣ የቤተሰብ አባል፣ ወይም የባለሙያ አማካሪ ሊሆን ይችላል። ከሚያምኑት ሰው ጋር መነጋገር ስሜትዎን ለማስተካከል እና እየሆነ ያለውን ነገር ለመረዳት ያግዛል።

ሦስተኛው እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ መመዝገብ  ነው። ይህ ከሁኔታው ጋር የተያያዙ ማናቸውንም ንግግሮች፣ ኢሜይሎች፣ ወይም የማህበራዊ ሚዲያ ልጥፎችን ያካትታል። ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከወሰኑ ይህ ሰነድ እንደ ማስረጃ ሊያገለግል ይችላል። ሁኔታው በህይወትዎ ላይ እንዴት ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ መዝግቦ መያዝም ጠቃሚ ነው።

አራተኛው ሁኔታው ስራዎን፣ ዝናዎን፣ ወይም የግል ደህንነትዎን በሚነካበት ደረጃ ላይ ከደረሰ፣ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግዎ ይችላል። ይህ የስም ማጥፋት ክስ መመስረትን ወይም የእግድ ትእዛዝ መፈለግን ሊያካትት ይችላል።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here