የብርሐን ተስፋን የገለጠዉ ምስጢር

0
63

በዓለም 286 ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ይገኛሉ:: ከእነዚህ ውስጥ ስምምነት ተደርጎባቸው ሀገራት በፍትሐዊ መንገድ በጋራ እየተጠቀሙባቸው የሚገኙት 250ዎቹ መሆናቸውን ዩ ኤን ዋተር (www.unwater.org) የተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል::

ትኩረቱን በሰዎች እና ፕላኔቶች ላይ አድርጎ የሚሠራው ግሪድ አሬንዳል (www.grida.no) የመረጃ አውታር በበኩሉ በአፍሪካ 63 ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እንደሚገኙ አስቀምጧል:: እነዚህ ወንዞች የአህጉሪቱን 64 በመቶ የመሬት ክፍል የሚሸፍኑም ናቸው:: ከእነዚህ አፍሪካዊ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መካከል መፍለቂያውን ኢትዮጵያ አድርጎ 11 ሀገራትን የሚያቋርጠው የዓባይ (ናይል) ወንዝ ይገኝበታል:: ግብጽ እና ሱዳን ደግሞ ውኃውን ለዘመናት በብቸኝነት ሲጠቀሙበት ቆተዋል:: እነዚህ ሀገራት ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ለማንኛውም ልማት መጠቀም እንደማትችል ሀገሪቱን ያገለሉትን ያለፉ ዘመናት ስምምነቶችን ተከትለው ለመከልከል ጥረት ሲያደርጉ ይደመጣሉ:: ለዚህም አስረጂው ኢትዮጵያ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተፋሰሱን ሀገራት በማይጎዳ መልኩ በዓባይ ወንዝ ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመሥራት ግንባታው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ጉዳዩን እስከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ወስዳ እየተከራከረች መገኘቷ ነው::

ኢትዮጵያ ግን ከዓባይ ወንዝ ጋር በተገናኘ የሚደርስባትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና እውነትን መሠረት አድርጋ በአግባቡ በመመከት፣ የፋይናንስ ክልከላውንም በራሷ አቅም ለመሸፈን የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅማ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ አሳክታለች:: ጳጉሜን 04 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ የመጠናቀቁ ብሥራት ለመላው ዓለም ተሰምቷል::

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የተለያዩ ሀገራት መሪዎችም ግድቡ የኢትዮጵያውያንን የመቻል አቅም ያሳየ፣ በሁሉም ዘርፍ አሸናፊነቷን ያረጋገጠ፣ አፍሪካን በመሠረተ ልማት እና በኃይል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን አረጋግጠዋል::

 

የሕዳሴ መልኮች

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተለያዩ ዘመናት በነበሩ ነገሥታት እና መሪዎች ቅብብሎሽ ለሕዝብ ተስፋ ምላሽ የሰጠ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ነው:: ግድቡ ከዓለም 10ኛ እና ከአፍሪካ ደግሞ በቀዳሚነት ተቀምጧል::

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪ ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳው የግድቡ ስፋት አንድ ሺህ 680 ካሬ ኪሎ ሜትር ነው:: ይህም 187 ሺህ 400 ሄክታር መሬትን ያካልላል::  ከፍታው ደግሞ  145 ሜትር፣ ውፍረቱ 130 ሜትር፣  ርዝመቱ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር፣ ውኃው የሚተኛበት የግድቡ የቦታ ስፋት 246 ኪሎ ሜትር ይደርሳል:: ይህም (ግድቡ የፈጠረው ሰው ሠራሽ ሃይቅ – ንጋት ሃይቅ) ከባሕር ዳር እስከ ደብረ ማርቆስ ያለውን የመንገድ ርቀት (254 ኪ.ሜ) ያህል እንደማለት ነው::

ግድቡ የሚይዘው የውኃ መጠን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው:: የውኃ መጠኑ በሊትር ሲሰላም 74 ትሪሊዮን ሊትር እንደማለት ነው::

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከነበረው ጣና ኃይቅ ሦስት እጥፍ የሚልቀውን ንጋት ሃይቅን ፈጥሯል:: የኃይቁ ከፍተኛ ጥልቀት 150 ሜትር ሲደርስ፣ ከ70 በላይ ደሴቶች እንዲፈጠርም ምክንያት ሆኗል::

ሕዳሴ በ13 ተርባይኖች አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል:: ይህም ለኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት (አንድ ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ እንደሚያስገኝ ልብ ይሏል)፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለዓሳ ምርት (ከ10 ሺህ ቶን በላይ) እና ለቱሪዝም ልማት ትልቅ አቅም እንደሚሆን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያረጋግጣል::

ሕዳሴ በሕዝብ ዕይታ

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ የአማራ ክልል ሕዝብ የደስታ መግለጫ የድጋፍ ሰልፍ መስከረም 06 ቀን 2018 ዓ.ም አድርጓል:: ግድቡ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎችን አልፎ መጠናቀቁ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ከድጋፍ ሰልፈኞች መካከል በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘላለም ጌታሁን ተናግረዋል:: አስተያየት ሰጪው “ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ውስጣዊ ችግሮች ሊኖሩብን ይችላል፤ ይህ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ያጋጠመ ሳይሆን ከጥንትም የነበረ ነው፤ ውስጣዊ ችግሮቻችን ግን የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፋንታ ከሚወስኑ ጉዳዮች በተቃራኒ መንገድ እንድንቆም አድርጎን አያውቅም:: ይህ ኢትዮጵያውያንን ከሌላው የዓለም ሀገራት ለየት የሚያደርገን ነው፤ የሕዳሴ ግድብም ለዚህ አንደኛው ማረጋገጫ ነው” በማለት ሐሳባቸውን አጋርተውናል::

ኢትዮጵያውያን በአንድነት  ችግራቸውን ውስጥ ለውስጥ እየፈቱ እና አንድነትን እያጠናከሩ ሕብረ ብሔራዊነትን ዕውን የሚያደርገውን የሕዳሴ ግድብ ከዳር ማድረሳቸውን አቶ ዘላለም ተናግረዋል:: ይህ አካሄድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት በተቃራኒ ቆመው የነበሩ ሀገራትን አክስሯቸዋል፤ ወደፊትም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ስለማይረሳ ከመተባበር ውጪ ያሉ አማራጮችን የሚከተሉ አካላት ኪሳራቸው እንደሚቀጥል አክለዋል::

በከፍተኛ ጫና ውስጥ አልፎ የተጠናቀቀው የሕዳሴ ግድብ በቀጣይ ለሚሠሩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ስንቅ እንደሚሆንም እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል:: ሕዳሴ ከኃይል ምንጭነቱ ባሻገር የተፈጠረው ንጋት ኃይቅ ለኢኮኖሚያዊ ከፍታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያምናሉ፤ በአሳ ሐብት ተጠቃሚ ለመሆን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሥራ ዕድል እንዲበረታታ እና ቁጥሩም ከፍ እንዲል ያደርጋል ነው ያሉት::

ሕዳሴ የኢትዮጵያውያን የመገናኛ መንገድ ሆኗል ያሉት ግለሰቡ፣ አሁንም አንድነትን አጠናክሮ የነገዋን ኢትዮጵያ በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎውን ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል::

በተባበረ ክንድ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣውን የጠላት ኃይል በዓድዋ ድል ያደረገው የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት ዛሬም ሌላኛውን ዓድዋ (ዳግማዊ ዓድዋ) በክንዱ አረጋግጧል ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ በድጋፍ ሰልፉ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘሪቱ አለባቸው ናቸው:: እርሳቸውን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላይ የዳግማዊ ዓድዋን ድል የተቀዳጁት የዓባይ ወንዝ የኢትዮጵያ እናቶችን የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል ትልቅ አቅም ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸው፤ ለዚህም አቅማቸው በፈቀደው ልክ ድጋፋቸውን ሳያቋርጡ በመቀጠላቸው ነው ብለዋል::

ግድቡ በማገዶ ጭስ ዐይናቸው ለሚያለቅሱት ሴቶች መፍትሔ ከመሆኑም ባሻገር ለማገዶነት የሚጨፈጨፈውን ደን ለመከላከል ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል::

“ኢትዮጵያውያን አንድ አይነት እሳቤ ይዘን የማናሸንፈው እና የማንሻገረው መሰናክል እንደሌለ በሕዳሴ ተምረናል::  ‘ኢትዮጵያውያን ደሃ ናቸው፤ አይችሉም:: የውጭ እርዳታ ካላገኙ ግድቡን መገንባት አይችሉም’ ተብለን የተሳልንበትን መንገድ ቀድሞውኑ በምንታወቅበት አንድነታችን አሳክተን ያሳየንበት አርማችን ነው:: ይህን አንድነታችንንም በቀጣይ አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያን በልማት እና በሌሎችም ዘርፎች ተወዳዳሪ ማድረግ አለብን” በማለት የኢትዮጵያዊያንን ለጠላት አይበገሬነት አብራርተዋል::

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው “የገናና ታሪክ እና የሥልጣኔ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ረሀብተኛ፣ ተመጽዋች፣ በድህነት እና በግጭት አዙሪት ውስጥ ሆና ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዳትሆን  ከቅርብም ከሩቅም ያሉ ጠላቶች በቡድንም ሆነ በተናጠል ወግተዋታል” ብለዋል፤ አዳክመዋት ስለመቆየታቸውም አስታውሰዋል:: ይህንን የድህነት፣ የኋላቀርነት እና የግጭት አዙሪት ታሪክ ለመቀየር በየዘመናቱ የነበሩ ልጆቿ ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ቀድመው ስለመጀመራቸው ተናግረዋል:: ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደግሞ የኢትዮጵያ የቁልቁለት ጉዞ ማብቃቱን እና የብልጽግና ጉዞ ጅማሮ ማብሰሪያ መሆኑን ገልጸዋል::

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከጅማሮው ከውስጥ እና ከውጭ ብዙ ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር በማስታወስ ሁሉንም ፈተናዎች በአሸናፊነት መወጣት መቻሉን ተናግረዋል:: በአጠቃላይ ግድቡ የታሪክ እጥፋት ማሳያ፣ የኢትዮጵያዊነት የአሸናፊነት እና የአይበገሬት ማረጋገጫ ማኅተም መሆኑን አስታውቀዋል::

እንደ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባዉ የሕዳሴ ግድብ በዚህ ትውልድ  የተፈጸመ ዳግማዊ ዓድዋ ሆኖ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል:: ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከሆኑ ማሳካት የማይችሉት ነገር እንደማይኖር ፈተናዎች ተጋርጠውበት የነበረውን ግድብ በስኬት ከማጠናቀቅ በላይ ምንም ማረጋገጫ እንደሌለ አስገንዝበዋል:: ኢትዮጵያ ወደፊትም የሚያስፈልጋትን ሁሉ እያሳካች እንደምትቀጥል አስገንዝበዋል::

ኢትዮጵያ ግድቡን ያሳካችው የኢትዮጵያዊ አንድነት እና አይበገሬነት ልምምድን እንደ ሁነኛ አቅም ተጠቅማ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ርእሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ናቸው:: ይህም በተለያዩ ጊዜያት የገጠማትን ዲፕሎማሲዊ ተግዳሮቶች ተሻግራ በዜጎቿ ሐብት፣ ጉልበት እና ዕውቀት ግድቡን ገንብታ እንድታጠናቀቅ ማስቻሉን ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ያሳካችው የሕዳሴ ግድብ በተለይ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት መነሳሳትን የሚፈጥር፣ በራስ አቅም መሥራት እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነም አረጋግጠዋል::

የኢትዮጵያን መልማት እና ማደግ የማይፈልጉ ሀገራት የዘረጉትን የአይሳካላቸውም ትርክት በኢትዮጵያዊ አንድነት ዕውን በሆነው ሕዳሴ መበጣጠሱን ነው ያስታወሱት:: የቅኝ ግዛት ሙከራን ያከሸፈው ኢትዮጵያዊ ክንድ ዛሬም በልማት ከፍ ብሎ አይበገሬነቱን ዳግም የገለጠበት እንደሆነ አስታውቀዋል::

ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ክብር እና ለብሔራዊ ጥቅማቸው አመላቸውን በጉያቸው፣ ልዩነታቸውን በይደር ትተው በአንድነት የማያሳኩት ነገር እንደሌለ ግድቡ ዋነኛ ማረጋገጫ መሆኑንም ጠቁመዋል:: የኢትዮጵያውያንን የወደፊት ተስፋ የገለጠ፣ የዘመኑም ሕያው መገለጫ ነውም ብለውታል::

ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሀገር በሉዓላዊ ግዛቱ ውስጥ የማንንም ሀገር መብት እና ጥቅም ሳይነካ በነጻነት የመወሰን መብት እንዳለው ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል:: በባዕዳን ሀገራት የተጫነውን የእጅ አዙር ጫና የቀለበሰ፤ ጽናትን፣ ጥበብን፣ ጀግንነትን እና አርበኝነትን በድጋሜ ያረጋገጠ ምስጢር እንዳለውም  ጠቁመዋል::

ኢትዮጵያን ለዘመናት ባይተዋር አድርጓት የቆየውን የተፋሰሱ ሀገራት እና የቅኝ ገዢዎቻቸውን መሰሪ የስምምነት ውል እስከመርዙ የፈወሰ ነውም ብለዋል:: ታላቁ ግድብ የራሳችንን ሀብት የመጠቀም፣ የሌላውንም ሀገር ሕዝብ የመጉዳት ፍላጎት እንደሌለን የዓለም አቀፍ የግንኙነት መርህን በተግባር ያረጋገጠ ውል ያደረግንበት ነውም ብለውታል::

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋት በማገዶ እንጨት ጭስ ለሚሰቃየው የገጠሩ የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ እና ጤና መሻሻል ሁነኛ መፍትሔ እንደሚሆንም ጠቁመዋል:: በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት እየተስተጓጎለ ላለው ልማት ትልቅ አቅም ይሆናልም ነው ያሉት:: የኢንዱስትሪ እና የአገልግሎት ዘርፉ በተሟላ ሁኔታ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፤ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎችም ማኅበራዊ ዘርፎች እንዲሻሻሉ የሚያደርግ ኃይል መገንባቱን አስታውቀዋል:: ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር በኤሌክትሪክ ኃይል ለማጎልበት ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here