ለግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው

0
85

የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ የንግሥ በዓል መስከረም 21 ቀን በድምቀት ይከበራል። በበዓሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ይገኛሉ፤ የጎብኚዎችን ፍሰት የሚጨምርም ነው። ለዘንድሮው የንግሥ በዓልም የቅድመ ዝግት እየተደረገ ስለመኾኑ ነው የተገለጸው፡፡

የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አሥተዳዳሪ አባ ብሥራተ ገብርኤል ክፍለ ማርያም የ2018 ዓ.ም የመስቀልን እና የግሼን ደብረ ከርቤ በዓልን ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

አባ ብሥራተ ገብርኤል እንዳሉት የደብሩ አሥተዳደር ሰበካ ጉባኤ፣ ማኅበረ ካህናቱ እና የአጥቢያው ምዕመናን በተለየ ሁኔታ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠሩ ነው።

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች በድምቀት እንደሚከበር ያነሱት  አባ ብሥራተ ገብርኤል ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት  በግሸን ደብረ ከርቤ  ደግሞ የተለየ ድምቀት አለው ብለዋል።

በበዓሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገራት የሚመጡ አማኞች እና ጎብኚዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።  ለጎብኚዎቹ ምቹ መሥተንግዶ ለማቅረብ  እየሠራን ነው ብለዋል። ለንግሡ ለሚመጡ ምዕመናን ማረፊያ የሚኾን ሰፊ ቦታ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ከባለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ መንገዱን ምቹ ለማድረግ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንገዶች አሥተዳደር አማካኝነት ጥገና እንደተሠራ ተናግረዋል፡፡

ለመኪኖች መቆሚያ የሚኾኑ አራት መናኸሪያዎች መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አስያ ኢሣ የግሸን ደብረ ከርቤ እና የመስቀል በዓላት በድምቀት እና በሰላም እንዲከበሩ ከሚመለከታቸው ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ለበዓሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እንግዶች እንደሚመጡ በማንሳት የአካባው ማኅበረሰቡም በተለመደው የእንግዳ አቀባበል  ባሕሉ  እንግዶችን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሰላምና ጸጥታው አስተማማኝ እንዲኾን ሁሉም በጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here