“ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታህሣሥ የማን ሆድ ይችላል እስከዚያው ድረስ” ለተረት የታደለ፤ ለአፍ የጣፈጠ ወንዝ እንደ ዓባይ የለም:: አንዳንድ ሰው ምንም ዓይነት ተረትና ምሳሌ ባይችል ቢያንስ “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለው ተረትና ምሳሌ ከአፉ አይታጣም:: እርግጥ ነው፤ ዓባይ መንገደኛ ነው፤ ብዙ ርቆ ይሄዳል::
በእርግጥም የግዝፈቱንና የገናናነቱ እና ያህል ጥቅም ላይ አልዋለም:: ክረምት አልፎ የዓባይ ውሃ ሙላት ጎድሎ ታህሣሥ ድረስ መታገስ አቅቶት የናፍቆት ግጥም እና እንጉርጉሮ ለመግጠም የታተረ፣ እስከዚያ መታገስ ያቃተው ትውልድ ዓባይን ጥቅም ላይ ለማዋል ለምን ገደደው? ነው ጥያቄው::
አንዳንድ አባባሎች ለስንፍና፣ ለሰበብ በር ይከፍታሉ:: እነዚህን አባባሎች ላለመቻል እንደሰበብ ወስደን ላልተሳካልን ነገር እንደ ምክንያት በመቁጠር ራስን ለማሳመን እንጠቀምባቸዋለን::
ዓባይን ላለመጠቀማችን ተረቱን እንደ ምክንያት፤ ምሳሌያዊ ንግግሩን እንደአይነኬ በማየት ዓባይ መንገደኛ እንዲሆን እድል ሰጥተነው ኖረናል::
ከዚህ ሁሉ ተረት ውጭ ሁሉም የማይናገረው እና በውስጡ የያዘው ቁጭት እንዳለ ማሳያው ግን የሕዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ መጣል ነው::
የሕዳሴው ግድብ የመሰረት ድንጋይ ብስራት ለዘመናት በተረት ሸንግለን እንዲጓዝ እድል የሰጠነው እና መንገድ የከፈትንለት ዓባይ ከልባችን እንዳልነበረ በዚሁም በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ ቁጭት እንደነበረ ማሳያ ነው:: አቅሙ የፈቀደ ሁሉ ያለውን ሳይሰስት እየሰጠ እዚህ ደርሷል::
በዚህ ግድብ ግንባታ ሂደት መላ ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ገንዛባቸውን አስተባብረው በጋራ ለመቆ እንዲሁም በጋራ ለመስራት እንደምክንያት የሆነ ብሎም ግድቡ የሁሉም መሆኑን ያሳየ ተግባር ፈጽመዋል::
ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል:: ይህን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ የተቻለው ደግሞ ከቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት እና ከኢትዮጵያ ነጻ አካውንት እንዲሁም ከውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን /ከዳያስፖራዎች/ ነው:: የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በመጭው መስከረም በድምቀት ለማስመረቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው::
የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ልማት ሲሸጋገርም የተፋሰሱን ሀገራት ተጎጂ የሚያደርግ ሳይሆን ለቀጣናዊ የጋራ ልማት በረከት በጋራ ለመልማት የሚያስችል እና የሁሉንም ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ነው:: ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በአንድ የመቆምና በጋራ የመፈጸም ማሳያና የቁጭታችንም መገለጫ ነው::
በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም