በኢትዮጵያ ሊግ አንድ የመሳተፍ እጣ ፋንታው ያለየለት ኮምቦልቻ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ህልውናው አሳሳቢ ነው።
በ2016 ዓ/ም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ሊግ አንድ የወረደው ኮምቦልቻ ከተማ በ2017 ላለመወዳደር የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጠው ለፌዴሬሽኑ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ አንድ አመት ሳይወዳደር አሳልፏል።በዚህ የአንድ አመት የእፎይታ ጊዜ ከተማ አስተዳደር ክለቡን ለማጠናከር ምን ሰራ? ስንል ለኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ አስቻለው ብርሃኑ ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር።
ሀላፊው እንደነገሩን በ2017 በደራሽና በተለያዩ ስራዎች ተጠምደው መቆየታቸውን ገልጸው በተለይም በመላው አማራ ጨዋታዎች ውጤታማ ሆኖ ለማጠናቀቅ ከእግር ኳስ ክለቡ ይልቅ ለውስጥ ውድድሮች ቅድሚያ በመስጠታቸው መላው አማራን በበላይነት ማጠናቀቅ እንደቻሉ ተናግረዋል።እንዲያም ሆኖ ኮምቦልቻ ከተማእግር ኳስ ክለብ ከነበረብን የበጀት ችግር አንጻር በተያዘው በጀት አመት ሊስተካከሉ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ በሚል ተስፋ ወደ 2018 መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።
በያዝነው አዲስ አመት ኮምቦልቻ ከተማ እግር ኳስ ክለብን በሊግ አንድ ለማወዳደር ፍላጎት ያለው ከተማ አስተዳደሩ በመንግስት በኩል የሚጠበቀው አመታዊ በጀት እንዳልተለቀቀላቸው አቶ አስቻለው ነግረውናል።
ይህ በጀት እንደ አማራ ክልል ለሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ባለመለቀቁ ምክንያት ሁሉም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ባሉበት መቆማቸውን አስተያየት ሰጥተዋል። በዚህም ምክንያት ገና በጀት ቢለቀቅ እንኳን ክለቡን ለማስቀጠል ጊዜው እየረፈደ ነው ብለዋል።ለምሳሌ የ2018 የሊግ አንድ ውድድር በጥቅምት ወር መጨረሻ የሚከናወን በመሆኑ የተጫዋቾች ምልመላ፣ ግዥ እና የአሰልጣኝ ቅጥር ለመፈጸም ጊዜው እየረፈደ ነው ብለዋል።
ከአመታት በፊት መቀመጫውን ኮምቦልቻ ከተማ አድርጎ በብሄራዊ ሊግ ይወዳደር የነበረው ጥቁር አባይ ትራንስፖርት ድርጅት በተመሳሳይ ችግሮች መፍረሱ ይታወሳል። እንደ ስጋት የኮምቦልቻ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የጥቁር አባይ ትራንስፖርት ድርጅቱ አይነት እጣ ፋንታ እንዳይገጥመው ጥንቃቄ ካልተደረገ ነገሮች አስቸጋሪ መሆናቸውን ከዚህ በፊት ከፈረሱ ክለቦች ታሪክ መማር ይገባል።
በነገራችን ላይ በአማራ ክልል በርካታ ክለቦች ባለቤት በማጣትና ጠያቂ አጥተው ፈርሰዋል።ከጥቁር አባይ ትራንስፖርት ድርጅት በተጨማሪ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲና ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ከነ ሙሉ ድምቀታቸው ደብዛቸው ጠፍቷል።የኮምቦልቻ ከተማ በዚያ ደረጃ ስጋት ባያሳድርም የበጀት ጉዳይ ለክለቦች መፍረስ ዋነኛ ችግር መሆኑ ግን እየታየ ነው።
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ምዘገባ ደብዳቤ ልከናል ያሉት የኮምቦልቻ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አስቻለው ብርሃኑ በዚህ አመት እኛ በቻልነው መጠን ክለቡን ወደ ተሳትፎ ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን ይበሉ እንጂ በጀት በተጨባጭ ባልተመደበበት ሁኔታ ክለቡን የማሳተፉ ጉዳይ ምንም ማረጋገጫ አልተገኘም።
በኢትዮጵያ ሊግ አንድ የመሳተፉ እጣ ፋንታው ያልየለት ኮምቦልቻ ከተማ ያለምንም ስጋት እንዲቀጥል ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ሊሰራ ይገባል።ጠንካራ ደጋፊ ማህበር እና የኢንዱስትሪ ከተማ በሆነችው ኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ጋር ክለቡን የማስተሳሰር አማራጭም መታሰብ ይኖርበታል።
(መልሰው ጥበቡ)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም