ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? አዲሱ የትምህርት ዘመን እንዴት ነው? በያዝነው ዓመት ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደምትተጉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ልጆች በዚህ ጽሑፍ ድንቅ ተፈጥሯዊ ሀብታችን የሆነውን የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ እናስተዋውቃችኋለን::የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በድሮው አጠራር አላጥሽ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ጎንደር ዞን፣ ቋራ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ከ1930ቹ ጀምሮ ከደን በዘለለ ጥብቅ ደን በመሆን በኅብረተሰቡ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡
በርካታ ጥናቶች ከተካሄዱ በኋላ የአካባቢው ማኅበረሰብ ፓርክ ይሁንልን ተደጋጋሚ ጥያቄ ታክሎበት በደንብ ቁጥር 38/1998 ብሔራዊ ፓርክ ሆኖ ታውጇል:: በሰሜን-ምዕራብ አካባቢ የሚገኘውን የሀገሪቱን ወካይ ቆላማ ስርዓተ-ምህዳርና በውስጡ በያዛቸው ብዝሀ-ህይወት ለመጠበቅ ታስቦ የተከለለ ፓርክ ነው፡፡
አልጣሽ 13 ነጥብ አንድ ዝቅተኛ እና 41 ነጥብ አንድ ከፍተኛ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሙቀት መጠን ያስተናግዳል፡፡ በተለያዩ ወቅቶች የተለያየ እይታ ያለው ብሔራዊ ፓርክ ነው፡፡
በስተሰሜን እና ምሥራቅ የቋራ ወረዳ ሰባት ቀበሌዎች፣ በስተደቡብ የቤንሻጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልል (ብጃሚስ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ) ወይም አይማ ወንዝ እና በስተምዕራብ ሱዳን (ዲንደር ፓርክ) ያዋስኑታል፡፡
በዚህም ብሔራዊ ፓርክ በብዝሀ-ሕይወት ሀብቱ በሀገሪቱ ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙት ውስጥ ሲሆን ከእፅዋት ዝርያዎች 14 የቁጥቋጦ አይነቶች፣ 57 ታላቅ እፅዋቶች (የዛፍ አይነቶች)፣ ከ10 በላይ የሳር ዝርያዎች፣ 32 አጥቢ እንስሳት (በአፍሪካ ብቻ የሚገኝ የተባለለት እና በመጥፋት ላይ ያለ ባለ ጥቁር ጋማ የአንበሳ ዝርያን እና ዝሆንን ጨምሮ)፣ ስምንት አይነት ተሳቢ እና ተራማጅ እንስሳት ዝርያ፣ 16 የአይጥ ዝርያዎች፣ ሰጎንን ጨምሮ 240 የአእዋፍ ዝርያዎች እንዲሁም ከ16 በላይ የአሳ ዝርያዎች ይገኙበታል::የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ቆላማው አካባቢ በአረንጓዴ የደን ሽፋን ምክንያት የሰሃራ በረሃማነት መስፋፋትን ከሚከላከል ስነ-ምህዳር አካል ዋነኛ በመሆኑ አረንጓዴው መቀነት (Green Belt) ወይም አረንጓዴው ዘብ (Green Guard) የሚል ስያሜ ተስጥቶታል፡፡ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአልጣሽ ብሄራዊ ፓርክ የካርበን ልቀት ከመከላከል አንፃር ሀገሪቱ ካሏት ጥብቅ ቦታዎች እና ፓርኮች ሁሉ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ እ.አ.አ በ2012 የዓለም አቀፍ አካባቢ ጥበቃ ተቋም ጥናት መሠረት የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ 20,132,576 ቶን ካርበን አምቆ በመያዝ የዓለም አየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል እንፃር የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑን ያስርዳል፡፡
ምንጭ፡- የጣና_ሃይቅና_ሌሎች_ውሃማ_አካላት_ልማትና_ጥበቃ_ኤጀንሲ
ተረት
አታላዩ
በአንድ የገጠር መንደር ይኖር የነበረ አንድ አታላይ ሰው ነበር፡፡ በዚህ ድርጊቱ የተማረሩ የአከባቢው ሰዎች ሁሉም ተሰባስበው እሱን እንዴት ከመንደሩ ማባረር እንዳለባቸው መወያየት ጀመሩ፡፡
ሁሉም ሀሳብ እየሰጡ በአንድ ነገር መስማማት ስላቃታቸው ለምን እሱን ጠርተን አንጠይቀውም ብለው አስጠሩት፡፡ ይሄ አታላይ ሰውም ተጠርቶ መጣ። ሽማግሌዎቹ “አንተ ሰው ምን ብናረግህ ይሻላል? ሁሉንም አስቸገርክ፤ ስለዚህ ሁላችንም ከዚህች መንደር ልናባርርህ ተስማምተናል እና መጥፎ ነገር ውስጥ ሳናስገባህ ከዚህ ለቀህ ሂድ” አሉት። አታላዩም ሰው “እባካችሁ እኔው እራሴ ለቅቄ እሄዳለሁ፤ ከመሄዴ በፊት ግን አንድ ነገር ብቻ ላስቸግራችሁ?” ብሎ ጠየቀ። ሽማግሌዎቹ እና የሰፈሩ ሰዎችም ብር ሊጠይቀን ነው ብለው ማጉረምረም ጀመሩ። አታላዩ ሰውም “አንዴ ስሙኝ እኔ ብር አልጠይቅም፤ ቤቴን አቃጥላችሁ አመዱን በስልቻ ሞልታችሁ እንድትሰጡኝ ብቻ ነዉ የምፈልገው” አላቸው:: ሁሉም በደስታ ተስማምተው ቤቱንም አቃጥለው አመዱን በሦስት ስልቻ ሞልተው ሰጡት። አታላዩ ሰውዬም የሰጡትን ይዞ ጉዞ ጀመረ። ብዙ ከተጓዘ ቡኋላ ስለመሸበት አንድ ቤት አግኝቶ “የመሸበት እንግዳ ነኝ አሳድሩኝ?” አላቸው። እነሱም እሺ ብለው አስገቡት፤ እሱም ሦስቱን ስልቻ ደጃፍ አስቀምጦ ገባ። እኩለ ሌሊት ተነስቶ ከጤፍ ጎተራ ዉስጥ ትንሽ ጤፍ ሰርቆ በስልቻው አጠገብ ነስንሶ ተመልሶ ተኛ፡፡ ሲነጋ ጠዋት ተነስቶ ስልቻው አጠገብ ሲደርስ ጩኸቱን ለቀቀው፤ የመንደሩ ሰዎችም ተደናግጠው ሁሉም ተሰበሰቡ። “ምን ሆነሃል?” ብለውም ጠየቁት።
እርሱም “ሦስት ስልቻ ጤፍ ይዤ መጥቼ ነበር፤ ሆኖም ጤፉን በሙሉ ወስደው በአመድ ለወጡብኝ፡፡” ሲላቸው እነርሱም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ቢሉት ስልቻዉን ሲያነሳ ከስሩ ጤፍ አዩ፡፡ የአከባቢውም ሰዎች ተመካክረው ስማቸውን እንዳያጠፋ በመፍራት ሦስት ስልቻ ጤፍ ሰጥተውት ጤፉን ይዞ ወደ ቀድሞው መንደሩ ተመለሰ፡፡ የመንደሩ ሰዎች “እንዴት ተመለስክ ጤፉንስ እንዴትአገኘህ?” ብለው ጠየቁት፤ እርሱም “አመድ በጤፍ የሚቀይሩ ሰዎች አሉ እኔም ይሄንን ጉድ ልነግራችሁ ነው ተመልሼ የመጣሁት” ብሎ አታለላቸው። እነሱም ቤታቸውን አቃጥለው አመዱን በአህያቸው ጭነው ወደዛ ቦታ ሲሄዱ፤ እሱ ደግሞ ላሞቻቸውን ሰብስቦ ሽጦ ለመጥፋት ወደ ገበያ ይዞ እየሄደ እያለ መሽቶበት ማደሪያ ሲያጣ ጫካ ውስጥ በጅቦች ተበላ፡፡ እነዛ የመንደሩ ሰዎች “አመድ ይዘው ገበያ ወጡ ”ተብለው ሁሉም ሳቀባቸው፡፡ ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ!
ሞክሩ
1.ድሃ ያለው፤ ሀብታም ግን የሌለው ምንድን ነው?
- ሦስቱ ሰዎች ምሥጢር ሊጠብቁ የሚችሉት እንዴት ነው?
- ምሥጢር ማለት ምንድን ነው?
መልስ
- ምንም
- ከሦስቱ ሁለቱ ሲሞቱ
- ለሌላ ሰው አትንገር ብለህ የምትነግረው ነገር
ነገር በምሳሌ
ሆዴ አታጣላኝ ከዘመዴ
ሁሉንም ቻል አድርገው ማለት ነው፡፡
መስሎ ከመታየት ሆኖ መገኘት ሳይሆኑ ከመምሰል የተፈለገውን ለመሆን ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡
ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ
ነገሮችን በጥልቀት መረዳት ተገቢ ነው
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም