የሰላምታ ቋንቋ

0
75

በቃል እና በምልክት የሚታጀብ የተግባቦት ጥበብ ነው። ከሰው ልጆች ሕልውና ጀምሮ የቀጠለ፤ ማህበረሰብ እንደ ወጉ እና ልማዱ የሚከውነው የሰላም ማብሰሪያ ነው።

በዓለም አራቱም የምድር አቅጣጫ ያሉ ሕዝቦች ልዩ ልዩ የሰላምታ ባህል አላቸው። መነሻው ባህል፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ ወይም ማህበራዊ መስተጋብር ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያዊያን ሰላምታ ሃይማኖታዊ ነው።  “ሰላምታ የእግዜር ነው፤የፈጣሪ ነው” ይባላል።

ሁለት በጥብቅ የሚፈላለጉ ባላጋራዎች እንኳን “እንደምን አደርህ፤እንዴት አደርሽ” ይባባላሉ። ሰዎች እንዴት ዋላችሁ ሲባሉ የሚያመሰግኑት ፈጣሪያቸውን ነው። ለዚህም ነው ሰላምታ አምላካዊ ነው የሚባለው። የባህል መለወጥን ተከትሎ በከተሞች አሁን አሁን “ሰላም ነው፣ ሃይ” እንላለን። ይህን ያዬ አዝማሪ እንዲህ ሲል ተቀኝቷል።

“እንዴት አደርህ ብለው እንዴት አደርህ አለኝ

እግዚአብሔር ይመስገን ሊቀር ነው መሰለኝ”

በሰላምታችን የሚከብረው ፈጣሪ ነው። ውለን ማደራችንን በማሰብ አምላካችንን እናመሰግናለን። ሰላምታ ለኢትዮጵያዊያን የምስጋና ቃል ነው። የማመስገኛ ምክንያት ነው። ሰላምታ የሚከወንባቸውን ምልክቶች ለመቃኘት ነውና የዛሬው ጽሑፍ በሀገራችን ጀምረን የመላውን ዓለም ጉልህ የሰላምታ ክዋኔዎች እንቃኛለን።

በኢትዮጵያ ቀደምቱ  ሰላምታ ከወገብ ዝቅ በማለት ጤና ይስጥልኝ ከሚል ቃል ጋር እጅ መንሳት ነው። ይህችን ሰላምታ የኮሮና ወረርሽኝ ሰሞን መልሰን መጠቀም ጀምረን ነበር። በሒደት እጃችንን ጨብጠን ማጋጨት ጀመርን፣ በምኋላ “አማን ነው” እያልን እጅ ለእጅ መጨባበጥ ጀመርን። ወደ ልማዳችን ምሽግ ተመለስን።

ጉንጭን አጥብቆ ሦስት ጊዜ መሳም በሀገራችን የተለመደ ነው። በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ደግሞ የእጅን ጀርባ መሳሳም የተለመደ ነው። ግንባር መሳምም የሚታወቅባቸው አካባቢዎች አሉ። ሰላምታ በእድሜም የተለያዬ ክዋኔ አለው። ሽማግሌዎችን  በርከክ ብሎ ጉልበታቸውን የመሳም ባህል የማክበር ምልክት ነው። ሕጻናትን ጉንጫቸውን እና ግንባራቸውን መሳም የተለመደ ባህል ነው። የርህራሄ እና ፍቅር ምልክት ነው። ቀዳማዊ አጼ ኀይለ ስላሴ በመንገድ ሲያልፉ ሕዝቡ መሬት በመሳም ሰግዶ ሰላምታ ያቀርብላቸው ነበር።

በሀገራችን አሁን ፋሽን የሆነው ደግሞ ለወንዶች ትክሻ ማጋጨት ነው። ለሴቶች “እጵ” ከሚል ድምጽ ጋር ጉልጭን ከጉንጭ ጋር ማገናኘት ነው። ይህ የከተሞች ባህል ነው። በገጠሩ ደግሞ ሴቶች ጥብቅ አድርገው ይዘው ጉንጭን በጉንጭ ሳይሆን በከንፈራቸው ይስማሉ። ወንዶችንም እንዲሁ ያደርጋሉ። ሲሲሙ ጥብቅ ያደርጋሉ።

የወንዶች ሸካራ ጺም አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል። ምራቅ የቀቡን ከመሰላቸው ደግሞ በእጃቸው ጥርግ ያደርጉናል። የአጎቴ ሚስት ሰላምታ ግን እስካሁን ይገርመኛል። በጣም በሩጫ ነው። ፊቴን ጭምቅ አድርጋ ትይዘኝና እያገላበጠች ሦስት ጊዜ “እጷ፣ እጷ፣ እጷ” ታደርገኛለች። ትንፋሽ ነበር የሚያጥረኝ። ስትለቀኝ ታስሮ እንደዋለ ዶሮ ነበር ምደናበር። ምን ያስቸኩላታል ግን? ባህል ነው። የኢትዮጵያ ሰላምታ ስል የመሐል ሃገሩን ማለቴ እንጂ በየ አካባቢው ልዩ ልዩ የሰላምታ ዘይቤ መኖሩን ረስቼው አይደለም።

ዱ ኖት ዳይ ዎንደሪንግ ድረገጽ “የሰላምታ ጥበብ ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ዳሰሳ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ሐተታ ከእጅ መጨባበጥ እስከ አፍንጫ መነካካት ያሉትን አስደናቂ ዓለም አቀፍ የሰላምታ ልማዶችን፣ ባህላዊ ጠቀሜታቸውንና ታሪካዊ አመጣጣቸውን ቃኝቷል።

ሰላምታ ለማህበራዊ ግንኙነት አስፈላጊ የሆነ ተፈጥሯዊ የሰው ልጅ ባህሪ ሆኖ፤ ግንኙነቶችን ለመገንባት ቁልፍ መሳሪያ ነው። የበርካታ ማኅበረሰቦችን እሴቶች፣ የሥልጣን ተዋረድና ልማዶችም ያሳያል። በአንዳንድ ባህሎች ውስጥ ቀላል እጅ መጨባበጥ ወይም አንገት ማጎንበስ በቂ ሊሆን ቢችልም፣ በሌሎች ደግሞ ከአፍንጫ ማሻሸት እስከ አየር ላይ መሳሳም ያሉ ውስብስብ ሥርዓቶችን ያካትታል።

ድረገጹ “ከሥነ-ሰብ እይታ አንጻር ሰላምታዎች በግለሰቦች፣ በቡድኖችና በሃገሮች መካከል መልካም ግንኙነቶችን የሚያረጋግጡ ማህበራዊ ቅባት ሆነው ያገለግላሉ” ይላል። እንደ እጅ መጨባበጥ ወይም መስገድ ያሉ  ሰላምታዎች  ለግንኙነቶች ማዕቀፍ በመስጠት፣ ለክብር፣ ለሥርዓት ወይም ለወዳጅነት ድባብ ይፈጥራሉ። ማህበራዊ ግንኙነቶችን ያዳብራሉ፣ ባህላዊ ማንነትን ያጠናክራሉ፣ ጥልቅ ምሳሌያዊ ትርጉሞችን ያስተላልፋሉ።

በመላው ዓለም የተለያዩ ባህሎች የራሳቸውን ልዩ የሰላምታ መንገዶች ፈጥረዋል። እያንዳንዳቸው በታሪካዊ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች የተቀረጹ ናቸው። እነዚህ ሰላምታዎች ብዙውን ጊዜ ሰዎች እርስ በእርስ የሚገናኙበትን መንገድ ከቀረጹ ልዩ ባህላዊ እሴቶች ወይም ታሪካዊ ክስተቶች ጋር ሊዛመዱ ይችላሉ።

ምናልባትም በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም የታወቀው ሰላምታ እጅ መጨባበጥ ነው። በምዕራቡ ዓለም የእምነትና የእኩልነት ምልክት ነው። አመጣጡ በጥንቷ ግሪክ ውስጥ ተነሳ ተብሎ ይታሰባል። በዚያም ሁለቱም ሰዎች  የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ መሆናቸውን ለማሳየት ያገለግል ነበር። እጅ መጨባበጥ በሮማውያን ዘመንም የተለመደ ነበር። ብዙውን ጊዜ በፖለቲካዊ አጋሮች መካከል የክብር ወይም የታማኝነት ምልክት ሆኖ ይታይ ነበር።

ዛሬ እጅ መጨባበጥ በመላው ዓለም በሙያዊና በዲፕሎማሲያዊ ሁኔታዎች ውስጥ ተስፋፍቷል። አተገባበሩ ላይ ጥቃቅን ባህላዊ ልዩነቶች አሉት። ለምሳሌ፣ በቻይና ውስጥ እጅ መጨባበጥ ቀለል ያለ ነው። በጀርመን እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጠንካራ ነው። በመካከለኛው ምስራቅ ደግሞ ግራ እጅ ንጹሕ አይደለም ተብሎ ስለሚታመን ቀኝ እጅ ብቻ ጥቅም ላይ ይውላል።

በብዙ የምስራቅ እስያ ባህሎች ውስጥ፤ በተለይም በጃፓን፣ ኮሪያና በአንዳንድ የቻይና ክፍሎች መስገድ የተመረጠው የሰላምታ አይነት ነው። የመስገዱ ጥልቀት እንደ ሁኔታው ይለያያል፣ ትህትናንና አክብሮትን ያመለክታል። ይህ ሰላምታ አብዛኛውን የምስራቅ እስያን ማህበራዊ ልማዶች ከቀረጸው የኮንፊሽየስ ፍልስፍና ሥርዓት የመጣ ነው። የኮንፊሽየስ እሳቤዎች ለሥልጣን ተዋረድ፣ ለአዋቂዎች ክብርና ማህበራዊ ደረጃዎች  ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። እነዚህ ሁሉ በመስገድ ተግባር ውስጥ ይንፀባርቃሉ። ለምሳሌ፣ በጃፓን ውስጥ በጣም ዝቅ ብሎ  መስገድ ከፍተኛ የአክብሮት ደረጃን የሚያመለክት ነው።

አፍንጫ የማይነካ፣ ጉንጭ የሚነካ የአየር ላይ መሳሳም በአውሮፓና በላቲን አሜሪካ ክፍሎች የተለመደ ነው። በፈረንሳይ ውስጥ፣ የአሳሳሞች ብዛት ድግግሞሽ ይለያያል። ከሁለት እስከ አራት የተለመደ ሲሆን፣ በስፔንና ጣሊያን ደግሞ ሁለት ነው። ይህ ሰላምታ አመጣጡ በሮማውያን ዘመን ሲሆን፤ በዚያም ወቅት  ጉንጭ ላይ መሳሳም የጓደኝነት ምልክት ነበር። በኋላም ፍቅርንና ዝምድናን ለማሳየት መንገድ ሆነ። በደቡብ አሜሪካ፣ በተለይም እንደ አርጀንቲናና ብራዚል ባሉ አገሮች ውስጥ፣ የአየር ላይ መሳሳም የማህበራዊ ግንኙነቶችን ሞቅ ያለ እና  ግልጽ ባህሪ ያንፀባርቃል።

ከሁሉም ያልተለመዱ ሰላምታዎች አንዱ የመጣው ከቲቤት ነው። በዚያም ምላስ ማውጣት ባህላዊ የሰላምታ ዓይነት ነው። ይህ ልማድ የጀመረው በ9ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን በተለይ ጨካኝ የነበረው ላንግ ዳርማ የተባለ ንጉሥ ዳግመኛ ተወልዷል የሚል ፍራቻ ምላሽ እንደሆነ ይታመናል።

ላንግ ዳርማ በጥቁር ምላሱ የሚታወቅ ሲሆን ምላስ ማውጣት ደግሞ እኔ ላንግ ዳርማ አይደለሁም የሚል ማረጋገጫ መስጫ ነው። ይህ ሰላምታ አሁን በሰፊው ባይተገበርም፣ በአንዳንድ ማህበረሰቦች ውስጥ በባህላዊ መልኩ ጠቃሚ ምልክት ሆኖ ቆይቷል።

 

ኬንያና ታንዛኒያ እጅ ከመጨባበጥ በፊት መትፋት የተለመደ የሰላምታ ባህል ነው። በዓለም ላይ ካሉት የመጨረሻዎቹ ታላላቅ የጦረኞች ጎሳዎች አንዱ በሆኑት በማሳይ እና ሃድዛ ጎሳዎች ዘንድ የሰላምታ አካል ነው። እንደ በረከት ምልክት እጅ ከመጨባበጣቸው በፊት እርስ በእርስ ይተፋሉ። ለጤና እና ለረጅም ዕድሜ መልካም ዕድል ያመጣል ተብሎ ይታሰባል።

ሰላምታዎች ቀላል የዕለት ተዕለት ምልክቶች ሊመስሉ ይችላሉ። ነገር ግን ትርጉምና ባህላዊ ጠቀሜታ አላቸው። ከምዕራቡ ዓለም እጅ መጨባበጥ እስከ ምስራቁ መስገድ ድረስ፣ እያንዳንዱ የሰላምታ አይነት የማህበረሰብ እሴቶች፣ ታሪክና ማህበራዊ መስተጋብር መስኮት ሆኖ ያገለግላል። ከሌሎች ጋር እንዴት እንደምንገናኝ ብቻ ሳይሆን ክብርን፣ ሰላምንና አንዳንዴም ማህበራዊ ተዋረድን እንዴት እንደምንገልጽ ያሳያሉ።

እነዚህን ባህላዊ ልዩነቶች በመረዳት፣ የሰውን ልጅ አገላለጽ ልዩነት እናደንቃለን። የተሻለ የባህል ተግባቦት ግንኙነት እናዳብራለን። በግሎባላይዜሽን ዓለም ውስጥ፣ የተለያዩ የሰላምታ ዓይነቶችን መማርና ማክበር ጨዋነት ብቻ ሳይሆን ወደ ትልቅ ባህላዊ  መግባባት የሚወስድ ወሳኝ እርምጃ ነው። ሁሉም ባህል በራሱ ውብ ነው። አንዱ ከሌላው አይበልጥም አያንስም። የአንዱ ሰላምታ ለሌላው ስድብ ሊሆን ይችላል። ትርጉማቸውን ማወቅ ተከባብረን ለመኖር ያግዘናል።

 

ማረፊያ

ሄሎ

ሄሎ የሚለው ቃል  እንዴት እንደመጣ አስበው ያውቃሉ? ዛሬ በብዛት ከምንጠቀምባቸው ሰላምታዎች አንዱ ነው:: ታሪኩ በጣም በጣም አስደሳች ነው:: ሄሎ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ እንደ ሰላምታ ቃል ጥቅም ላይ አልዋለም ነበር። ቃሉ በመጀመሪያ የተለየ ዓላማ ነበረው:: ዛሬ “ሄይ”ን እንደምንጠቀም ሁሉ ሰዎች የአንድን ሰው ትኩረት ለመሳብ ሄሎን ይጠቀሙበት  ነበር::

ስልክ ስናነሳ በተለምዶ ‘ሄሎ’ እንላለን። ግን ሄሎ ምንድነው? ‘ሄሎ’ ሰላምታ ብቻ ሳይሆን የአንድ የተወሰነ ሰው ስም መሆኑን ብዙዎችን ሊያስደንቅ ይችላል። ‘ሄሎ’ በእርግጥም የአሌክሳንደር ግራሃም ቤል እጮኛ ማርጋሬት ሄሎ ስም ነበር።

ስልኩን የፈጠረው ቤል የፈጠራ ስራውን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሞክር ‘ሄሎ’ የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። ይህ ቀላል አነጋገር በፍጥነት በዓለም ዙሪያ የስልክ ጥሪዎች መደበኛ መክፈቻ ሆነ:: ዛሬ ላይ ስልካችንን ስናነሳ የምንጠቀመው ሰላምታ ሆኖ ቀጥሏል። ግራሃም ቤል ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ለሚስቱ የደወለው በ እ.አ. አ1876 ነበር።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here