የጠፈር ኢንድስትሪው እያደገ የሚወነጨፉ “ሮኬቶች” በመበራከታቸው ከሚለቁት ጢስ እና የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲያበቃ ህዋ ላይ ከሚቀር ስብርባሪ የሚወጣው መርዛማ ትነት የከባቢ ዓየር ሽፋን (ኦዞን)ን ከመሸንቆር ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በሲውዘርላንድ የዙሪክ ዩኒቨርሲቲ የጠፈር መከታተያ ጣቢያ ተመራማሪዎች በምስለ ሙከራ ከሮኬቶች የሚወጣው ጢስ የከባቢ ዓየር የላይኛውን የ“ኦዞን” ንጣፍ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስበት መገንዘብ ችለዋል፡፡
በ2030 እ.አ.አ በየዓመቱ የሚወነጨፉ ሮኬቶች በ2024 ከነበረው 1040 ከአራት እጥፍ በላይ እንደሚያድጉ ሲገመት “ኦዞን” የጨረር መከላከያው ንጣፍ ዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶ እንደሚሳሳ ነው የአስቀመጡት፡፡
ቀደም ብሎ አገራት በ1989 እ.አ.አ በሞንትሪያል በደረሱበት ስምምነት መሰረት “ኦዞን”ን የሚጐዳው “ክሎሮፍሎሮካርቦን” የተሰኘው የሀይል ምንጭ በመታገዱ ጉዳቱ እያገገመ እንደነበር ነው ባለሙያዎች ያስታወቁት፡፡
“ኦዞን” ማለትም ከፀሀይ የሚመጣን ጐጂ ጨረር የሚከላከለው ንጣፍ በቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን ከነበረበት በግምት ሁለት በመቶ መሳሳቱ ነው የተገለፀው፡፡ ይህ ጉዳት ሙሉ በሙሉ እንዲያገግም እስከ 2066 እ.አ.አ በትጋት እየተሰራ ነው ያሉት ባለሙያዎቹ አሁን ላይ በተደረገ ጥናት መሰረት ቁጥጥር ካልተደረገበት በብዛት ወደ ህዋ ከሚመጥቁ ሮኬቶች የሚለቀቀው ጢስ ልፋቱን ሁሉ ከንቱ አድርጐ የኋሊት ይጐትተዋል፡፡
ለ’’ኦዞን’’ መሳሳት ወይም መሸንቆር መንስኤ ከሆኑት የሮኬት ልቀቶች የክሎሪን ትነት “gaseous chlorine’’ እና “soot particles” ይገኙበታል፡፡ “soot particles” የተሰኙት መካከለኛውን የጨረር መከላከያ ንጣፍ ሲያሞቁት የክሎሪን ትነቱ ደግሞ የኦዞን ሞሎኪውሎችን ወይም ጥቃቅን ቅንጣቶችን ያመናምናል፤ ያጠፋል፡፡
በአጠቃላይ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ጐጂ የሆነው የፀሀይ ጨረር ምድርን ወደ ከበባት ከባቢ ዓየር ዘልቆ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ አስቀድሞ የክልከላ እና ቁጥጥር መመሪያ ሊወጣ እና ሊፀድቅ ይገባል በሚል ማሳሰቢያ ነው ድረ ገፆች ዘገባቸውን ያደማደሙት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም