ለሃገራት ደረጃ ሲወጣ በአፍሪካ የቀዳሚነትን ደረጃ ትይዛለች። የደስተኛ ዜጎች መኖሪያ፣ ሃብታም፣ እጅግ ሰላማዊ እና የተረጋጋች፣ የህፃናትን ደህንነት አስጠባቂ የሚሉትን የመመዘኛ መስፈርቶች በየዓመቱ በማሟላት ከአፍሪካ ሃገራት የመጀመሪያ መሆኗ ተመስክሯል።
ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በሃገሯ ለሚሰማሩ ባለሃብቶችም ተመራጭ ናት። የአፍሪካ አህጉር አካል የሆነችው ውብ ሃገር-ሞሪሺየስ።
የ”አፍሪካ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም” ለህፃናት መብት መጠበቅ የሚደረጉ የህግና የፖሊሲ ከለላዎችን፣ ተገቢ የሆነ የአመጋገብ ስርዓት፣ ለህፃናት የሚደረግ የጤና አጠባበቅ፣ ትምህርትና የልደት ምዝገባዎችን ያሟላች መሆኗን አረጋግጦ በ2018 እ.አ.አ የአፍሪካ ቀዳሚ ሃገር ብሏታል። በዓለም የደስተኛ ሃገራት መመዘኛ መስፈርት መሰረትም ሞሪሺየስ የ2020 እ.አ.አ ደስተኛ ህዝብ ያላት የደረጃው ቁንጮ አፍሪካዊት ሃገር ተብላለች። በተጨማሪም የአሜሪካው ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ አና የብሪታንያው ለንደን የኢኮኖሚክስ ዩኒቨርስቲ ከዘላቂ ልማት ኔትወርክ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋም ጋር በመቀናጀት ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በ2023 አ.አ.አ ሞሪሽየስን ደስተኛ ህዝብ ያላት በሚል ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ አስቀምጧል። የዜጎች ዓመታዊ ገቢ፣ የጤና እና ማህበራዊ አገልግሎት መጠን፣ የሙስና ደረጃ እና የዜጎች በነፃነት የመወሠን መብት መመዘኛዎችን በማሟላቷ ነበር ደረጃው ላይ መቀመጥ የቻለችው።
የኢኮኖሚ እና ሰላም ኢኒስቲትዩት የ2021 እ.አ.አ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ ሃገራት መካከል፤ የሰላምና መረጋጋት መመዘኛዎችን መሰረት አድርጎ ለሞሪሽየስ በአፍሪካ እጅግ ሰላማዊ ሃገር ሲል የመጀመሪያ ደረጃን ሰጥቷል። በ2025 እ.አ.አ በድጋሜ የተሻለ ሰላም ያላት ቀዳሚዋ የአፍሪካ ሃገር ሆናለች።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/አይ ኤም ኤፍ/ በ2024 እ.አ.አ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ሃብታም እና ድሃ ሃገራትን ዝርዝር ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህም መሠረት ከ54ቱ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ሞሪሺየስ ሃብታሟ ሃገር ተብላ በግንባር ቀደምትነት ደረጃውን ለመያዝ ችላለች።
ከዋናው የአፍሪካ ምድር የተገነጠለች፤ በህንድ ውቅያኖስ የተከበበች ትንሽዬ ደሴት ናት-ሞሪሺየስ። ከደቡብ ምሥራቃዊቷ አፍሪካዊት ሃገር ሞዛምቢክ በሁለት ሺህ ኪሎሜትር፤ ከአፍሪካዊቷ ትልቋ ደሴት ማዳጋስካር ደግሞ በ1100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ሃብታሟ ትንሽዬ ሃገር ሞሪሺየስ፤ በመልካምነት ለትላልቆቹ የአፍሪካ ሃገራት ሁሉ ተምሳሌት ናት። ሁለት ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋቷ ነው። የዜጎቿ ቁጥርም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ 68 ከመቶ የሚሆኑት የህንድ ዝርያ ያላቸው ናቸው። ገንዘባቸውም ልክ እንደ ህንድ ሩፒ ነው። የሃገሪቱ ትልቁ ሃይማኖትም ሂንዱይዝም ነው። የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ሞሪሺየሳውያን ከሃገሪቱ የህዝብ ቁጥር ውስጥ 27 ከመቶውን ይይዛሉ።
ከ18ኛው መቶ ክፍለዘመን ጀምሮ ፈረንሳዮች እና እንግሊዛውያን እየተፈራረቁ ቅኝ ገዝተዋታል። በዚህ የተነሳ ዜጎቿ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛን አቀላጥፈው ይናገሩበታል። ከዚያ በፊት ደሴቷ ነባር ዜጋ ኖሯት አያውቅም። ዛሬ ሞሪሺየሳውያን የምንላቸው ዜጎቿ ፈረንሳውያን ሸንኮራ አገዳ ለማምረት ደን እንዲመነጥሩላቸው ከአፍሪካ ቅኝ ግዛታቸው ያመጧቸው ጥቁሮች እንዲሁም እንግሊዛውያን ስኳር እንዲያመርቱላቸው ከህንድ ያመጧቸው የጉልበት ሰራተኞች እና ለቅኝ ገዥነት መጥተው ተመችቷቸው የቀሩ ነጮች ናቸው።
ሞሪሺየስ 130 ደሴቶች አሏት። ከነዚህ ውስጥ አንዷ ሞሪሺየስ ስትሆን ከሁሉም ትልቋ እና የሃገሪቱም መጠሪያ ናት። 95 ከመቶ የሃገሪቱ ዜጎችም በዚች ደሴት ይኖራሉ። ሮድርጊየስ ደግሞ በስፋትም፤ በህዝብ ብዛቷም ሁለተኛዋ ትልቅ ደሴት ናት። ምንም እንኳን የሞሪሺየስ አካል ብትሆንም በመንግሥታዊ አስተዳደር ግን ራስ ገዝ ደሴት ናት። 108 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት አላት። ከዋና ደሴቷ ሞሪሺየስ በስተምሥራቅ 560 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ጥቁር ሞሪሺየሳውያን በብዛት የሚኖሩባት ደሴትም ናት። አጠቃላይ የደሴቷ ነዋሪዎች ቁጥር 43 ሺህ ይገመታል።
የሞሪሺየስ ዋና ከተማ ፖርትሎይ ትባላለች። 150 ሺህ ነዋሪዎች አሏት። የመንግሥት ዋና መቀመጫ፣ ወደ ሃገሪቱ የሚደረጉ ዋና በረራዎች መዳረሻ እና የሃገሪቱ ትልቁ ወደብ መገኛ ናት። የዓለማቀፍ ባንኮች እና የታላላቅ ቢዝነስ ማዕከል፣ የበርካታ ቅንጡ ሆቴሎች እና ሪዞልቶች መገኛ እንዲሁም የሃብታሞች መኖሪያ ናት።
ሞሪሺየስ በሰው ሃብት ልማት መለኪያ በአፍሪካ ቁጥር አንድ ላይ የምትቀመጥ ሃገር ናት። ለዜጎቿ እና የመኖሪያ ፈቃድ ላላቸው የሃገሪቱ ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት በነፃ ታቀርባለች። ትምህርትም ልክ እንደ ህክምና አገልግሎቱ በነፃ ይሰጣል።
ሞሪሺየስ የተዋጣለት የህዝብ ትራንስፖርት ያላት ሃገር ናት። ተማሪዎች፣ ጡረተኞች እና አካል ጉዳተኞች ቀላል የባቡር መስመርን ጨምሮ ባስ እና ሌሎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በነፃ መጠቀም ይችላሉ።
ደሴቷ ከዓለማችን ቁጥር አንድ መዳረሻዎች አንዷ ናት። ቱሪዝም የሃገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው። ከዓመታዊ ገቢዋ 24 ከመቶውን ያመነጫል። በየዓመቱም ከዜጎቿ ቁጥር በላይ የሆኑ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ቱሪስቶች ይጎበኟታል። ለቱሪስቶች የጉዞ ደህንነትን አሟልታ በመስጠት ትታወቃለች። የዓለማችን ቅንጡ ሆቴሎች እና ሪዞልቶች መገኛ ናት። በርካታ የጎልፍ መጫዎቻወችም አሏት።
በደቡባዊ ምዕራብ የሚገኘው የጥቁር ወንዝ ጎርጅ ብሔራዊ ፓርክ፣ የደቡባዊ ምሥራቅ የባህር ዳርቻዎች ልዩ የመልካምድር ገፅታ፣ የእፅዋት እና ብርቅዬ እንስሳት ሀብቷ የጎብኝዎችን ቀልብ ከሚስቡት መገለጫዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በአጠቃላይ በዓለም መድረክ አፍሪካ ስሟ በበጎ ከተነሳ ምክንያቷ ይህችው ሃገር ናት። ምክንያቱም የተለያዩ ዓለማቀፍ ደረጃዎችን ከዓለም ሃገራት ጋር እየተሻማች በመያዝ ስማችንን በበጎ የምታስጠራልን ይህችው ትንሽዬ አፍሪካዊት ደሴት ናት። በሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ሰላም ሰፍኖ ዜጎች ደስተኛ ሆነው የሚኖርበትን ዘመን ተመኘን፤ ቸር ይግጠመን።
ምንጭ፡- am.wikipedia.org
-bbe.com
-ceochronicles
am.sadaalomma.com
አጫጭር እውነታዎች
ሞሪሺየስ
- የተሻለ ሰላም ያላት ቀዳሚዋ የአፍሪካ ሃገር ናት።
- ደስተኛ ሕዝቦች ያላት ሀገርም ናት፡፡
- ከ54ቱ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ሞሪሺየስ ሃብታሟ ሃገር ተብላ በግንባር ቀደምትነት ደረጃውን ለመያዝ ችላለች።
- በህንድ ውቅያኖስ የተከበበች ትንሽዬ ደሴት ናት፡፡
- ሁለት ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋቷ ነው።
- የዜጎቿ ቁጥርም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብቻ ነው።
- ገንዘባቸው ልክ እንደ ህንድ ሩፒ ነው።
- የሃገሪቱ ትልቁ ሃይማኖት ሂንዱዚም ነው።
- ሞሪሺየስ 130 ደሴቶች አሏት።
- የሞሪሺየስ ዋና ከተማ ፖርትሎይ ትባላለች።
- ቱሪዝም የሃገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው።
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም