ለጥሩ ውጤት ያቀደዉ

0
21

ልጆችዬ እንደምን ሰነበታችሁ?  የመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ተጀምሯል:: ልጆች የአምናውን ውጤት በያዝነው ወሰነ ትምህርት የተሻለ ለማድረግ መጣር አለባችሁ:: በጣም ጥሩ ልጆችዬ::

ልጆች የዚህን ዓመት ትምህርት ውጤቱን ለማሻሻል ቆርጦ የተነሳን ተማሪ እናስተዋውቃችሁ:: ተማሪ ቢኒያም ፈንታሁን በባሕር ዳር ከተማ ፈለግ አባይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው:: አምና አንደኛ ክፍል ተማሪ 10ኛ ነው የወጣው:: በዚህ ዓመት ይህን ውጤት ማሻሻል እንዳለበት ቢኒያም አምኗል::

ቢኒያም ክፍል ውስጥ የሚሰጠዉን ትምህርት በአግባቡ እንደሚከታተል ተናግሯል:: ወደ ቤቱ ካመራ በኋላ የተሰጠዉን የቤት ሥራ ወዲያው ይሠራል:: የቤት ሥራዉን ከጨረሰ በኋላ በቀን የተማረዉን የመከለስ ልምድ አልነበረዉም፤ ይልቁንም የፈተና ጊዜ ሲደርስ በክፍል ውስጥ መምህሩ የሰጡትን ጽሑፍ ያጠናል::

በያዝነው ዓመት ግን በቀን የተማረዉን እና የተሰጠዉን ጽሑፍ በየዕለቱ የቤት ሥራዉን ከጨረሰ በኋላ መከለስ ጀምሯል:: በቀጣይ ቀን የሚማረዉን ቀደም ብሎ አንብቦ ክፍል መግባት እንዳለበት መምህሩ መክረውታል፤ ይህንንም ተግባራዊ አድርጓል::

ቢኒያም ዉጤቱን ለማሻሻል እቅዱን መተግበር ጀምሯል:: ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን ይዞ የመጀመሪያ ወሰነ ትምህርት ለመጨረስ እንዳሰበም ነው የነገረን::

ቢኒያም መከተል የጀመረዉ የማጥኛ ዘዴ ጥሩ ነው አይደል ልጆችየ? እናንተም በዕለት የተማራችሁትን በዚያዉ ቀን የመከለስ፣ በቀጣይ ቀን የምትማሩትን ቀድሞ አንብቦ ክፍል መገኘትን መልመድ አለባችሁ:: ይህም በክፍሉ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑ እና ውጤታችሁንም ለማሻሻል ይረዳችኋል:: ሳምንት በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም ጊዜ::

ተረት

ብርቱዋ ሴት

በሀገራችን አንድ ብልህና ታዋቂ የነበሩ አለቃ ገብረሃና የተባሉ ሰው ነበሩ:: እኝህ ሰው ታዲያ ከእርሣቸው የተሻለ ብልህ ሰው ሁልጊዜ ይፈልጉ ነበር:: ሆኖም ብዙ ጊዜ አይሳካላቸውም ነበርና ከእርሳቸው የተሻለ ብልህ ያለ አይመስላቸውም ነበር:: ታዲያ አንድ ቀን ከእርሳቸው የተሻለች ብልህና አዋቂ ሴት አለች መባሉን ሰምተው ወደሷ መንደር በመሄድ ቤቷን አፈላልገው አግኝተውት በእንግድነት ተስተናገዱ::

ቤቱም የሴትየዋ ወላጆች ቤት ነበርና በባህሉም መሠረት አንድ እንግዳ ሲመጣ እግሩን ማጠብ፣ ምግብ ማቅረብ፣ አልጋ ማንጠፍና የመሣሠሉትን በማድረግ እንግዳውን መቀበል ልማድ ነበር:: በዚህም መሠረት በብልኋና በአዋቂዋ ሴት እንዲሁም በወላጆቿ አለቃ ገብረሃና አስፈላጊው መስተንግዶ ሁሉ ተደረገላቸው::

በመጨረሻ ሴትየዋ አለቃን ለሰገራ ይዛቸው እንድትወጣ ነገሯት፤ ፊት ፊትም እየመራች ቤቱን ብዙ ጊዜ አዞረቻቸው:: ከዚያ አለቃ ስለደከማቸው ወደ ደጃፉ ሄዱ:: የልጅቷም ቤተሰቦችምን ሆኑ? ለምንድነው ወደ ሜዳው ያልወረዱት?” ብለው ቢጠይቁ፣ ብልኋም ሴትእምቢ ብለው እዚህ አደረጉትብላ መለሰች::

ሁሉም ሰው ስቆባቸው አለቃ ገብረሃና ስለተናደዱ ወደ መኝታቸው ይሄዳሉ:: ብልኋም ሴት አልጋቸውን እንድታነጥፍላቸው ሲነግሯት መደባቸው ላይ ትንሽ ድብዳብ ጣል አድርጋ ልትወጣ ስትል አለቃአልጋዬን ለምን በደንብ አታዘጋጅልኝም? ይህ ለአንድ ሰው ይበቃል እንዴ?” ብለው ቢጠይቋት እሷምእንግዲያው ይህንን ሲጨርሱ ሌላ እጨምርልዎታለሁአለቻቸው:: እሳቸውም ምንም ምርጫ ስላልነበራቸው እዚያችው ድብዳብ ላይ ተኝተው አደሩ::

በማግስቱም ጠዋት ቂም ይዘው ወደቤታቸው ተመለሱ:: ከዚያም ሁለት ቁምጣ ጤፍ በሁለት አህዮች ጭነው ይልኩላትና የጤፉን ብዛት እንድትነግራቸው ይጠይቋታል:: እሷም ለመቁጠር ብትሞክር እርሳቸው ስለሚያሸንፏት ሞኝ ልትባል ሆነ:: ስለዚህ እንዲህ ብላ መለሰችጤፉን ቆጥሬ የአህዮቹን ፀጉር ብዛት ያክል ሆኗል:: ስለዚህ የአህዮቹን ፀጉር ቆጥረው ብዛቱን ይድረሱበትአለቻቸው፤ በዚህም አባ ገብርሃናን በብልጠት እንደዚች ብልህ ሴት የተፈታተናቸው የለም ይባላል::

ሞክሩ

  1. በዓለም የሚገኙ ሰዎች ሁሉ የሚያስፈልጋቸው ነገር ነው፤ ነገር ግን አብዛኞቹ ከመውሰድ ይልቅ ለሌሎች የሚሰጡት ምንድን ነው?
  2. ምንም አጋዥ ሳትጠቀም ባለሦስት ፎቅ ከሆነ ህንፃ ብትዘል ማረፊያህ የት ይሆናል?
  3. በእንግሊኛው ፊደላት ባለ 10 ሆሄ ቃል ነው፤ ነገር ግን በውስጡ ብዙ ሺህ ቃላትን የሚይዝ ምንድን ነው?

 

መልስ

  1. ምክር
  2. ሆስፒታል
  3. Dictionary (ዲክሽነሪ) ወይም መዝገበ ቃላት

 

ነገር በምሳሌ

ሥራ ያጣ ሙቅ ያኝካል፤

ሥራ ፈት ሰው ምንም ውጤት የማይገኝበትን ሥራ ይሠራል፡፡

መናገር ሳያስቡ፣ ምላጭ መሳብ ሳያልሙ፤

ከመናገርህ በፊት አስብ!

ለአንዱ የዘነበለት፣ ለሌላው ሳያካፋ አይቀርም፤

ሁሉም እንደሥራውና እንደልፋቱ መጠን ማግኘቱ አይቀርም፤

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here