ሕጉ ስለውል ምን ይላል?

0
35

ውል ማለት በሁለት/ውል ሰጭ እና ውል ተቀባይ/ ወይም ከዚያ በላይ ባሉ ሰዎች መካከል ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለማስቀረት የሚደረግ ስምምነት እንደሆነ  የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ዐቃቢ  ሕግ  ወ/ሮ ናርዶስ ጥላሁን ገልፀውልናል:: እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ውል ሰዎች በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ከሚያከናውኗቸው የግንኙነት መገለጫዎች አንዱ ነው::

ውል በፍትሃብሔር ሕጉ አንቀፅ 1678 ላይ ሊይዛቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸው ሰፍሯል:: በአንቀጹ የውል አቋሞች /አመሠራረት/ በሚል ከሰፈሩት   የሚፈጽሙት ውል በሕግ የተፈቀደ እና ሕጋዊ ሽያጭ አሊያም ኪራይ ሊሆን ይችላል የሚለው ቀዳሚው ነው::

ሌላው ተዋዋይ ወገኖች  ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ እና በሕግ መብታቸውን ለመጠበቅ ያልተገፈፉ፣ ለመዋዋል ችሎታ ያላቸው/ የአዕምሮ ችግር የሌለባቸው/ መሆን ይገባቸዋል:: በውል ተቀባይ እና ሰጭ መካከል የሚፈፀመው የውል ስምምነት  በጽሑፍ መደረግ እንደሚገባም በሕጉ የሰፈረ ሌላው መስፈርት ነው:: እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ አንዳንድ ውሎች ጉዳያቸው ቀላል ከሆነ በቃል ይፈጸማሉ፤ አንዳንዶች  ግን የግድ በጽሑፍ የሚደረጉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ  የቤት ሽያጭ ውል ተጠቃሽ ነው:: በፍትሃብሔር ሕጉ አንቀፅ 1723 ላይም የግድ ውሉ አንዲጻፍ ያስገድዳል::

ውል ለመፈፀም ሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ወደው እና ፈቅደው ፣ ተስማምተው  ሊይዙት /ሊያደርጉት/ የሚገባው ጉዳይ እንጂ በግዳጅ /ማስገደድ/ ሊፈጸም እንደማይችልም የዐቃቢ ሕግ ባለሙያዋ ጠቁመዋል:: በጠቅላላው ሕጉ የተሟላ ነው ለማለት የተጠቀሱት  ሃሳቦች  ሲሟሉ ነው::

ስለጠቅላላ ውል እንዲሁም ልዩ ውሎች በሚል ርዕስ ሥር የሽያጭ፣ የብድር፣ የኪራይ … ውሎች በፍትሃብሔር ሕጉ ከአንቀፅ 2266 ጀምሮ ተደንግገው ይገኛሉ:: የሽያጭ ውል ትርጓሜ ምን ማለት ነው? የሚለውን ባለሙያዋ ሲያብራሩ  ሽያጭ ማለት ሻጭ የሆነ አንድ ወገን ገዢ ለሆነ ሌላ ወገን ዋጋው በገንዘብ የተወሰነውን አንድ ነገር ለገዢው ሊከፍል ግዴታ በገባበት መሠረት ሊያስረክብ እና ሀብትነቱን ሊያስተላልፍ የሚገባበት ግዴታ ነው::

የሽያጭ ውል በሚንቀሳቀስ ፣ በማይንቀሳቀስ እና ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት ሽያጭ ውል ሊፈፀም ይችላል:: ለምሳሌ የማይንቀሳቀስ ቤት፣ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ እና ሌሎች እቃዎች ናቸው::  በልዩ የሚንቀሳቀሱ  ንብረቶች ደግሞ  ከዋናው ንብረት ተነጥለው የሚሸጡትን ነው::  ለአብነት  ዛፎች ቢሆኑ ዛፍ መሬቱ ላይ ይበቅላል፤ መሬቱ ሳይሸጥ ላዩ ላይ ያለው ዛፍ ተቆርጦ ሊሸጥ ይችላል:: ይህ ነው ልዩ ተንቀሳቃሽ (special moveable) ተብሎ የተደነገገው::

የሽያጭ ውል አፈጻጸሙን  በተመለከተ የፍትሃብሔር ሕጉ አንቀፅ 2270 ላይ  ውሉ በሚደረግበት ጊዜ ሻጭ በተጨባጭ   በእጁ  ያለ ንብረት መሆን ይገባዋል  ወይም ደግሞ     በሽያጭ ዋጋ የሚያወጡ  እንደ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናት  ሊሆኑ ይገባል:: በዚህ ውስጥ ታዲያ የሻጭ ግዴታ በተቀመጠው ውል አግባብ መሰረት ለገዥው ዕቃውን ለማስረከብ  ንብረቱ ከሦስተኛ ወገን ነፃ መሆን አለበት፤ ሦስተኛ ወገን  ንብረቱ የኔ ነው ብሎ ቢመጣ ኃላፊነቱ የሻጭ መሆኑን ማወቅ፤ የሚሸጠው ንብረት ጉድለት ቢገኝበት ኃላፊነቱን ይወስዳል::

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ የማስረከብ ግዴታን በተመለከተ በፍትሃብሔር ሕጉ አንቀፅ 2274 መሰረት በውሉ ልክ /ውሉ ላይ በተገለፀው አግባብ/ ማስረከብ እና ሥመ ንብረቱን ወይም ባለቤትነቱን ጭምር የማስረከብ ግዴታ አለበት:: ገዥ ደግሞ በሚረከብበት ወቅት ሁሉንም ነገሮች አይቶ መረከብ አለበት፤ እዛው ላይ የሚያያቸው ችግሮች ካሉ  ወዲያው ጉድለቶችን ለሻጭ ማሳወቅ አለበት፤ የገዛውን ነገር ምርመራ ሲያደርግም ሻጭን ይዞ ማድረግ ይችላል:: ሁለቱ ወገኖች ጉድለት ቢገኝ በምን ያህል ጊዜ ማሳወቅ እና መስተካከል እንዳለበትም በውሉ ላይ አካተው መጻፍ እና መዋዋል ይገባቸዋል:: የገዥ ግዴታ ደግሞ በውሉ ላይ የተገለፀውን ንብረት መረከብ፣ በተረከበው ንብረት ልክ ዋጋውን የመክፈል ግዴታ አለበት::

በተሸጠ ንብረት ላይ ጉድለት ከተገኘ እና  ውሉ ላይ በተቀመጠው አግባብ ካልሆነ ግዥው ይመለሳል፤ የፍትሃብሔር ሕጉ አንቀፅ 2288 ላይም እቃው ውሉ ላይ በተቀመጠው  ልክ ትክክል ስለመሆኑ የሚባለው ሻጩ ከሸጠው ነገር አንዱን ክፍል ብቻ የሠጠ እንደሆነ፣ ሻጩ ሊሰጥ በውል ቃል ከገባው ልክ አብልጦ ወይም  በውሉ የተመለከተው ሳይሆን አይነቱ ሌላ ነገር የሠጠ፣  ያጎደለ ሲሆን እንዲሁም የፍትሃብሔር  ሕጉ አንቀፅ 2289 ላይ ደግሞ እቃው የተሸጠው ለመገልገያነት  ሆኖ ሳለ ለመገልገያነት የማያገለግል ከሆነ መመለስ እንደሚችል ተቀምጧል::

በሽያጭ ውል አፈፃፀም ወቅት ተዋዋይ ወገኖች በውላቸው አግባብ ሻጭ የሸጠውን ንብረት ገዥው በተባለው ሰዓት ተረክቦ ገንዘቡን ከከፈለ በኋላ  የውሉ ውጤት ያበቃል:: ውል በተባለው አግባብ  ሳይፈፀም ከተገኘ እና በተባለው ጊዜና ሰዓት ካልተረከበ ፣ንብረቱ ለገዥው ሳይተላለፍ ከቀረ ፣ ጉድለት ካለበት ግን ገዥው ውሉን በተባለው አልተፈፀመልኝም ብሎ ማፍረስ ይችላል::

ሻጭም ገንዘቡ ካልተከፈለው፣ በተባለው ጊዜና ሰዓት ካልተረከበ ውሉ ሊፈርስ ይችላል:: እንደ ውላቸው ሳይፈፀም ሲቀር በፍትሃብሔር ሕጉ አንቀፅ 2229 ላይ ሻጩ የሸጠውን ነገር በደንብ ያላስረከበ እንደሆነ የተዋዋለበትን ውል በግድ ሲፈፅም ልዩ የሆነ ጥቅም የሚያስገኝ መስሎ ሲታየው ገዥው ውሉ በግድ እንዲፈፀምለት ለማስገደድ ይችላል::

በዚህ አንቀፅ መሠረት ገዥው የገዛው እቃ ልዩ ጥቅም የሚያስገኝለት ከሆነ ማለትም ንብረቱ የማይገኝ ከሆነ፣  ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስገኝለት ከሆነ ሻጩ በውሉ መሰረት ተገዶ ንብረቱን ለገዥው እንዲያስረክበው ሊጠይቀው ይችላል::  በፍትሃብሔር ሕጉ አንቀፅ 2330 ላይ የተገዛው እቃ በልምድ ምትክ ማግኘት የሚቻል ፣ ያለ ችግር ከሌላ ቦታ የሚገኝ ከሆነ ግን ላያስገድድ ይችላል:: እንደውሉ አግባብ ካልተፈፀመ ግን ሁለቱም ማለትም ገዥም ሻጭም እንደውሉ አግባብ ይፈፀምልን ብለው ወደ ፍርድ ቤት መሔድ ይችላሉ:: ከዛ ውጭ ውሉ በመፍረሱ ወደ ነበሩበት መመለስ ይችላሉ፤ ንብረቱ ሲመለስ ግን ገንዘብ የተቀበለ አካል ወለዱን ጨምሮ ሲከፍል የተጎዳ አካል ካለ ደግሞ የጉዳት ካሳ አብሮ ይከፍላል::

ግዥ ሲፈፀም በውል ማድረግ የሚያስገኘው ዋና እና መሠረታዊ ጥቅም ውሉ ሳይፈፀም ቢቀር በሽያጭ መካከል ችግር ቢፈጠር ንብረቱን  አሊያም ደግሞ የጉዳት ካሳ እንዲያገኝ  ሕጉ የሚያስገድድ በመሆኑ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ነው:: የገበያው ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ ውል በተዋዋይ ወገኖች መካከል ሕግ ሆኖ የሚፈለገውን ለማግኘትም  ያገለግላል::

ባለሙያዋ ወ/ሮ ናርዶስ እንደሚሉት  ውሉ በጽሑፍ ይደረግ እና ፍትሕ ጽ/ቤት ወይም በተዋረድ ባለው አካል ውሉን መመዝገብ  ይገባል:: ከዛ በኋላ ባለው ሂደት ገዥው የሚመለከተው ቦታ ሄዶ የሥመ ንብረት ዝውውር ያደርጋል፤ አሊያም ይረከባል::

የሕግ አንቀጽ

የሽያጭ ውል ምንነት
• በፍትሃብሔር ሕግ ቁጥር 2266 መሠረት የሽያጭ ውል ማለት ሻጭ የሆነው አንዱ ወገን ገዥ ለሆነው ሌላ ወገን ዋጋው በገንዘብ የተወሰነውን አንድ ነገር ገዢው ሊከፍለው ግዴታ በገባበት መሠረት ሊያስረክበውና ሀብትነቱን ሊያስተላልፍ የሚገደድበት ውል ነው፡፡
• ተዋዋይ ወገኖች ጊዜና ቦታውን ካልወሰኑ ደግሞ ጊዜውን በተመለከተ በመርህ ደረጃ የዕቃው ዋጋ ክፍያ ሲፈፀም ዕቃ የማስረከብ ግዴታውም ወዲያውኑ መከናወን ያለበት መሆኑን በፍትሃብሔር ሕጉ በቁጥር 2278 ላይ ተደንግጓል፡፡
• የገዥ ግዴታዎች ተብለው የሚታወቁት የዕቃውን ዋጋ የመክፈልና የገዛውን ዕቃ በተገቢው ጊዜ የመውሰድ ግዴታዎች መሆናቸው በፍትሃብሔር ሕግ ቁጥር 2303 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡
• ገዥው ክፍያውን ሳይከፍል ቢቀርና በንግድ ልማድ መሠረት ሁለቱን ተዋዋዮች በሚያቻችል ሽያጭ ለመሆን የሚችል ካልሆነ በስተቀር ሻጩ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2333 መሠረት ገዥውን እንዲከፍለው በሕግ ማስገደድ ይችላል፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here