ባለፈው የትምህርት ዘመን 94 ሺህ 668 ተማሪዎችን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ያስፈተነው የአማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎቹ ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል:: ከተፈተኑት ውስጥ 12 ነጥብ አምስት በመቶዎቹ የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡ ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 452 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ዕውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል::
ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ዕውቅና ከተበረከተላቸው ተማሪዎች መካከል አርሴማዊት ተስፋዬ ትገኝበታለች:: የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሐን ከተማ በሚገኘው የኅይለማርያም ማሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው::
ክልሉ የገጠመው የሰላም እጦት በርካታ ተማሪዎችን ከትምህርት ውጪ አድርጓል የምትለው አርሴማዊት፣ በደብረ ብርሐን ከተማ የነበረው አንጻራዊ ሰላም ግን እሷ እና በአካባቢው ይማሩ የነበሩ ሌሎች ተማሪዎች የ12 ዓመታት ልፋታቸውን በውጤት እንዲቋጩ እንዳደረጋቸው ተናግራለች:: ይህም የተሻለ ሰላም ትምህርቷን ከማጠናቀቅ ባለፈ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባ ቀጣዩን ጉዞ እንድትጀምር አስችሏታል:: ጠንካራ የጊዜ አጠቃቀም እና የወላጅ ክትትል ላስመዘገበችው 515 ነጥብ 667 ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ገልጻለች::
አርሴማዊት በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ጤና ሳይንስ (ሜዲስን) ማጥናት ፍላጎቷ ነው:: የትኛውም ችግር ግቧን ከማሳካት ወደ ኋላ እንደማይጎትታት አርሴማዊት ስትናገር፣ በእስካሁን ቆይታዋ የነበሩ ችግሮች ይበልጥ እንድትበረታ እና ለተሻለ ውጤት እንድትበቃ አድርጓታል::
“በነዚህ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተማርሁት ሀገር ሰላም መሆን እንዳለባት ነው:: ምክንያቱም እኛ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተጠቅመን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችንን አጠናቀቅን፤ የሰላም ችግሩ የተሻለ አቅም እና ዕውቀት ኖሯቸው ግን ዓላማቸው የተስተጓጎለባቸው ብዙ ተማሪዎች እንዲኖሩ አድርጓል:: በመሆኑም የሀገራችን ሰላም ወደነበረበት ተመልሶ ሁሉም በተሰማራበት ሥራ ውጤታማ ሆኖ እንዲጓዝ ሁሉም ስለ ሰላም መሥራት ይኖርበታል” ስትል ነው ተጽእኖውን ያጋራችን::
አርሴማዊት ልምዷን ሌሎች እንዲጋሩት መልዕክት አስተላልፋለች:: አንድ ሰው ዓላማውን እና ግቡን አስቦ መጓዝ ከጀመረ የነገሮች የመሳካት ዕድል በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ታምናለች:: ችግሮች ሲፈጠሩ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አማራጭ መውጫ መንገዶችን መፈለግ፣ ዕቅድ ማቀድ እና በዕቅዱ መሠረት መራመድ፣ ዓላማን በየጊዜው ማስታወስ እንደሚገባም መክራለች::
ችሎታው ደሴ ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ ዛግዌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 509 ነጥብ 88 ውጤት በማስመዝገብ ለሽልማት በቅቷል:: “እውቅና እና ሽልማቱ ለሠራነው እንደ ማበረታቻ ሆኖ ይበልጥ እንድንሠራ የሚያደርግ የአደራ ቃል ኪዳን ነው” ብሏል:: ተተኪዎችም ይበልጥ እንዲሠሩ የሚያነሳሳ እንደሆነ ያምናል::
የግል ጥረት፣ ጠንካራ የጊዜ አጠቃቀም፣ የወላጅ ክትትል፣ የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ድጋፍ ላስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግሯል:: በትምህርት ሰዓት የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት መከታተሉ፣ ከትምህርት ውጪ ያለውን ጊዜ በተደራጀ መንገድ ከፋፍሎ መጠቀሙ፣ ቤተሰብም የሚያስፈልገውን የትምህርት ቁሳቁስ ለይተው ማሟላታቸው፣ ትምህርት ቤቱም እሁድ እና ቅዳሜን ጨምሮ ሁሉንም ቀናት ቤተ መጻሕፍት ክፍት እንዲደረግ ማድረጉ እና በማጠናከሪያ ትምህርት እገዛ ማድረጉ ለተመዘገበው ውጤት በምክንያትነት አንስቷል:: በብሔራዊ ፈተና ያሳካው ውጤት የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ለዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ እንደ መስፈንጠሪያ እንደሚሆነው ገልጿል::
የቀጣይ ተፈታኝ ተማሪዎችም ከወዲሁ ጊዜያቸውን በአግባቡ ከፋፍለው መጠቀም እንደሚኖርባቸው መክሯል:: የ12 ዓመታት ልፋትን ከግብ ለማድረስ ጊዜ ትልቁ ምስጢር ነው ያለው ችሎታው፤ በዚህ ወቅት በምንም ምክንያት የሚባክን ጊዜ ሊኖር አይገባም ብሎ መነሳት እንደሚገባ አሳስቧል:: ደግሞ ደጋግሞ ማጥናት፣ የፈተና አወጣጡን ቀድሞ ማወቅ እና በዚያ ልክ መዘጋጀት፣ የቡድን ጥናትን ማጠናከር ያስፈልጋልም ብሏል::
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ዶ/ር ነጻነት ጌጤ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የቤተሰብ ክትትል ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ገልጸዋል:: ለዚህም ልጃቸው ኤፍራታ ምትኩን አብነት አድርገዋል:: በደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደር በሚገኘው ኀይሌማናሳ አዳሪ ትምህርት ቤት ትምህርቷን ስትከታተል የቆየችው ኤፍራታ 540 ነጥብ 92 ውጤት በማስመዝገብ ዕውቅና እና ሽልማት እንደተሰጣት ተናግረዋል:: አካሄዳቸውን መከታተል፣ የሚያስፈልጋቸውን ለይቶ ማሟላት ደግሞ ዋና ዋናዎቹ የወላጆች ሚና እንደሆኑ ጠቁመዋል:: “ልጄ በራሷ ጠንካራ ናት፤ በ14 ዓመቷ ጀምሮ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብታ ህልሟን ያሳካች ናት፤ እኔም ጥረቷን በሚያስፈልጋት ሁሉ በአግባቡ እደግፋት ነበር፤ የተመዘገበው ውጤትም የወላጅ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያሳየ ነው” ብለዋል::
አማራ ክልል ያለው የሰላም እጦት ታዳጊዎችን ሳይቀር ዋጋ እያስከፈለ ነው ያሉት ዶ/ር ነጻነት፣ ነገር ግን ይህንን ጫና ተቋቁመው ያስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የጽናታቸው ማሳያ አድርገው እንደሚወስዱት ገልጸዋል:: ከአራት ዓመት በፊት ልጃቸውን ከደብረ ታቦር ወደ ደብረ ብርሐን በተሸከርካሪ ይልኩ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ነጻነት፤ ዛሬ ላይ ግን ለእረፍትም በአውሮፕላን ካልሆነ የማይታሰብ ነው ሲሉ የጸጥታ ሁኔታው ምን ያህል ለቤሰብ ፈተና እንደሆነ እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል::
“እንደ እኔ ልጅ ጥሩ ቦታ ላይ መድረስ የሚችሉ በርካታ ልጆች አሉ:: ሩቅ መሄድ ሳያፈልግ ገጠር ላይ ያሉ የወንድሞቼ እና የእህቶቼ ልጆች ዛሬም ከትምህርት ውጪ እንደሆኑ ናቸው:: ይህ ችግር እንደ ዜጋ ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል:: ሁሉም ለሰላም ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የነገ ሕይወታቸው እየጨለመባቸው ያሉ ታዳጊዎችን ተስፋ መመለስ ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል::
በዕውቅና እና ሽልማት መርሀ ግብሩ ላይ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ወቅታዊ ችግሮች ሳይበግራቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ወደ የኒቨርሲቲ ለሚቀላቀሉ ተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል::
“የቀጣዩ ትውልድ እና ሀገር ሰላም፣ ልማት እና ብልጽግና የሚረጋገጠው በትምህርት ነው” ያሉት ዶ/ር ሙሉነሽ፣ “ተሸላሚዎች ከእስካሁን ቆይታችሁ ለየት ባለ መንገድ ራሳችሁን፣ ጊዜያችሁን እና አካሄዳችሁን በራሳችሁ መንገድ የምትመሩበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል::
ዶ/ር ሙሉነሽ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም ሆነ በሌላኛው የሕይወት መንገዳቸው ሊያዳብሯቸው ይገባል ያሏቸውን ቁልፍ ጉዳዮችን ጠቁመዋል:: ትብብር ቀዳሚው ጉዳያቸው ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል:: የትብብር ተማሪዎች የጋራ ግቦችን ለማሳካት በመሯሯጥ፣ ሐሳቦችን በመጋራት እና ሀብቶችን በማዋሀድ የተካኑ ናቸው ሲሉ የመተባበርን አስፈላጊነት አስረድተዋል:: በግለሰባዊ ጥንካሬዎች ላይ ተመሥርቶ ተግባራትን መመደብ እና የተለያዩ አመለካከቶችን እየገመገሙ መግባባት ላይ ለመድረስ ኀይል እንደሚሆንም ገልጸዋል:: ይህም የመተሳሰብ፣ የመደማመጥ እና የመደራደር ችሎታን እንደሚያሳድግ ነው የገለጹት::
ፈጠራን ማዳበር ሌላኛው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከሚቀላቀሉ ተማሪዎች የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነ አብራርተዋል:: የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጠራ ከባህላዊ ማዕቀፎች ውጭ ማሰብን፣ አዳዲስ ሐሳቦችን ማመንጨትን፣ ችግሮችን በአዲስ መንገድ መቅረብ እና መፍታትን እንደሚያካትት አስረድተዋል::
የፈጠራ ተማሪዎች ብዙ ጊዜ ኃላፊነትን ለመውሰድ፣ አዳዲስ ነባራዊ ሁኔታዎችን ተቀብሎ የተለያዩ መፍትሔዎችን ለመሞከር ዝግጁ ናቸው ብለዋል:: የፈጠራ ተማሪዎች ተግዳሮትን ለፈጠራ እንደ ዕድል ይመለከታሉ፤ ለስኬት መውጫ አድርገው ይጠቀማሉ፤ በውድቀት አይደናቀፉም ሲሉ ባህሪያቸውን ገልጸዋል:: ተሸላሚ ተማሪዎችም ክልሉ የገጠመው ችግር ሳይበግራቸው ይልቁንም ያጋጠሙ ፈተናዎችን እንደ ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው ከፍተኛውን ውጤት በራስ ዕውቀት እና አቅም ማሳካታቸውን ገልጸዋል::
ሦስተኛው ተፈላጊ ችሎታ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ መሆኑን ዶ/ር ሙሉነሽ ጠቁመዋል:: ሂሳዊ አስተሳሰብ ችግሮችን ለመፍታት፣ የማይቀለበስ ውሳኔ ለመወሰን እና አዳዲስ ጽንሰ ሐሳቦችን ለመማር የሚጠቀሙባቸው የአዕምሮ ሂደቶች፣ ስልቶች እና ውክልናዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል:: ከግምገማ፣ ከተሞክሮ፣ ከማሰላሰል፣ ከማሰብ ወይም ከተግባራዊ መንገዶች የሚመነጩ መረጃዎችን የመተግበር፣ የመተንተን፣ የማዋሀድ እና የመገምገም ሂደትን ያካትታል::
ዓለማቀፋዊ ዜግነት የተማሪዎች የነገ ተጠባቂ ዕውቀት እና አስተሳሰብ መሆኑን በአራተኛነት አስቀምጠዋል:: ዓለም አቀፍ ዜጋ ዓለማቀፋዊ ጉዳዮችን፣ ባህሎችን እና አመለካከቶችን ማወቅ እና መረዳት ነው:: ለዚህም ራስን የማስተማር፣ የመጻፍ እና ዓለም አቀፍ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ ተማሪዎች ለዚህ ከወዲሁ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል:: ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የተለያዩ መጣጥፎችን ማንበብ፣ በውጭ ቋንቋ ራስን ማብቃት፣ አካባቢያዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን እያገናዘቡ መተንተን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል:: በቴክኖሎጂ አቅም ራስን ማዳበር እና ዓለም በሁሉም ዘርፍ የምትፈልገው ዜጋ ለመሆን ሁሉን ዓቀፍ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል:: ፡፡
ቅምሻ
የአራቱ ዓመታት የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤቶች – አማራ ክልል
በ2014 ዓ.ም፡-
246 ሺህ 946 ተማሪዎች ተፈተኑ፡፡
ሦስት ነጥብ ስድስት በመቶ የማለፊያ ነጥብ አስመዘገቡ፡፡
ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት 70 ተማሪዎች ናቸው፡፡
በ2015 ዓ.ም፡-
210 ሺህ 323 ተማሪዎች ተፈተኑ
አራት ነጥብ አንድ በመቶዎቹ አለፉ፡፡
60 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ፡፡
2016 ዓ.ም፡-
95 ሺህ 879 ለፈተና ተቀመጡ
219 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ፡፡
በ2017 ዓ.ም፡-
94 ሺህ 668 ተማሪዎች ፈተና ወሰዱ፡፡
12 ነጥብ አምስት በመቶዎቹ የማለፊያ ውጤት አስመዘገቡ፡፡
452 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ምንጭ፡- የአማራ ክልል ት/ቢሮ
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም