የጎብኚዎችን ቀልብ እየሳበች ያለች ከተማ

0
33

ሀገራት ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ፣ ሰው ሠራሽ እና ሌሎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዙ ሃብቶቻቸውን በተለያየ መንገድ ያስተዋውቃሉ፤ ምጣኔ ሃብታቸውንም በከፍተኛ መጠን ይደጉማሉ።

የአማራ ክልል በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ጥብቅ የማኅበረሰብ ሥፍራዎች፣ ብርቅየ የዱር እንስሳት እና የማይዳሰሱ ደማቅ የማኅበረሰብ በዓላት የሚገኝበት ለቱሪዝም ተመራጭ ነው። በክልሉ የሚገኙ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማስተዋወቅ፣ ማልማት እና መጠበቅ ደግሞ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

በአማራ ክልል ከሚገኙ ከተሞች መካከል ድንቅ የተፈጥሮ ገጸ በረከት የተጎናፀፈችው ባሕር ዳር አንዷ ናት። የዓባይ እና ጣናን ስብጥር ተፈጥሮ ለውበቷ የቸራት ባሕር ዳር አሁን ላይ በኮሪደር ልማት ሥራዎችም እየደመቀች ነው። በተለይም ጣና ሐይቅን ተከትለው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎቿ ምቾትን፣ ለአዳዲስ ጎብኚዎቿ ደግሞ ሀሴትን የሚፈጥሩ ናቸው።

የጣና ሐይቅ እና በውስጡ ያሉት ገዳማት፣ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ፣ ዘምባባዎቿ፣ ሰው ሠራሽ ፏፏቴ (ፋውንቴን)፣ ዘመናዊ የእግረኛ መንገድ፣ የግራና ቀኝ የብስክሌት መንገድ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሰፋፊ መንገዶች፣ በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው አዲሱ የዓባይ ድልድይ፣ ውብ መናፈሻዎች እና መዝናኛ ቦታዎች የባሕር ዳር ከተማን ይበልጥ ካደመቋት መካል ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የከተማዋ ድምቀቶች ታዲያ የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የቱሪዝሙን እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ እያደረጉ ነው።

ቱሪዝም ለሀገር ምጣኔ ሃብት ዕድገት የሚሰጠውን ፋይዳ ከግምት በማስገባት በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን “የቱሪዝም ቀን” በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ይውላል።

የዘንድሮው የዓለም የቱሪዝም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ46ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ38ኛ ጊዜ እንዲሁም በአማራ ክልል ለ33ኛ ጊዜ ተከብሯል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ “ቱሪዝም ለዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ መልዕክት መስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም የዓለም የቱሪዝም ቀንን ከአጋር አካላት ጋር በውይይት አክብሯል። በውይይት መድረኩ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ጋሻው እንዳለው  እንደተናገሩት ቱሪዝም የእርስ በርስ ግንኙነትን ያጠናክራል፣ ገጽታን ይገነባል፣ ባሕልን ያስተዋውቃል፣ አብሮነትን ያጎለብታል፣ የምጣኔ ሃብት መነቃቃትንም ይፈጥራል።

በከተማዋ የሚገኙ ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶችን (እንደ ጢስ ዓባይ ፏፏቴ፣ ጣና ሐይቅ እና ብዝኃ ህይወቱ፣ ጥቁር ዓባይ (ግዮን ወንዝ)፣ ቤዛዊት ኮረብታማ ቦታ፣ ዓባይ በጣና ላይ ቆርጦ የሚሄድበት፣ ዘጌ ባሕረገብ ሥፍራ፣ ደሴቶች እና ገዳማት) በማንሳት ቱሪዝሙን እንዴት እናሳድገው በሚል ሐሳቦች ተነስተዋል።

መምሪያ ኃላፊው እንደገለፁት ውብ እና ማራኪ ቦታዎች መኖራቸው፣ ምቹ የአየር ንብረት፣ ሳቢ መልክዓ ምድር፣ የተሟላ የቱሪዝም መሠረተ ልማት፣ ትራንስፖርት፣ መልካም የእንግዳ አቀባበል እና መስተንግዶ ባሕር ዳር ከተማን በጎብኚዎች ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል።

ከተማዋ ካሏት የተፈጥሮ ፀጋዎች በተጨማሪ በከተማ አሥተዳደሩ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተስፋፉ ናቸው። አጠቃላይ የከተማዋን ፀጋዎች መሠረት በማድረግ ባሕር ዳር ከተማን የጎብኚዎች ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን መምሪያ ኃላፊው አመላክተዋል።

አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን እና መናፈሻዎችን መሥራት፣ ነባሮችን መልሶ ማልማት፣ ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ፣ ከተማዋን የሚመጥኑ ሆቴሎች እንዲገነቡ እና ያልተሟሉ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ማድረግ በትኩረት እየተሠራባቸው ያሉ ተግባራት ናቸው። በተለይም የቱሪዝም መስህብ በሆኑ (ጣና ሐይቅ ዙሪያ፣ ጢስ ዓባይ እና ዘጌ) ቦታዎች መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

ሌላው ትኩረት የተሰጠው ተግባር የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ማስፋፋት ነው፤ ለዚህ ደግሞ የሆቴል ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ማድረግን ይጠይቃል፤ እየተሠራበትም ይገኛል። ለዚህ ማሳያዎችም በጣና ዳር እየተሠሩ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሪዞርቶች እና የአረንጓዴ ልማት ተጠቃሽ ናቸው።

ኃላፊው እንዳብራሩት ብዙ የሚነገርላቸው የጣና ሐይቅ እና አካባቢው ጸጋዎችን አልምቶ ለመጠቀም ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ ነው። አስጎብኚ ድርጅቶችም የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።

ከተማዋን የጉብኚት ማዕከል እንድትሆን እየሠሩ ከሚገኙት መካከል ናቡ ኢትዮጵያ የተባው ድርጅት አንዱ ነው፤ የናቡ ኢትዮጵያ የአቅም ግንባታ አማካሪ ባይህ ጥሩነህ እንዳሉት የቱሪዝም ዘርፉ የክልሉን ምጣኔ ሃብት ዕድገት የሚደግፍ ነው። በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ዕምቅ ሃብቶችን በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ፣ መጠበቅ፣ መጠቀም እና የማኅበረሰቡን ኑሮ እንዲሻሻል ማድረግ ይገባል።

ከተሞች ውብ፣ ፅዱ እና ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅቱ (ናቡ ኢትዮጵያ) ከሚመለከታቸው ጋር እየሠራ ይገኛል ብለዋል። በጣና ሐይቅ ውስጥ ያሉት ቅርሶች እና የመስህብ ሃብቶች ተጠብቀው እንዲተዋወቁ፣ የተፈጥሮ ሃብቶች፣ ቅርሶች እና ገዳማት እንዲጠበቁ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ቱሪዝም የብዙ ተቋማትን ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን በመጥቀስ ሁሉም አካባቢውን ማወቅ፣ ማልማት፣ ማስተዋወቅ እና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ መትጋት ይገባል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዓባይ መንግሥቴ እንዳስገነዘቡት ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የቱሪዝም ልማት ሥራ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል። ዘርፉ ለማኅበራዊ ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለውን ሚና ለማሳወቅም በየዓመቱ የቱሪዝም ቀን እንደሚከበር አስረድተዋል።

አስጎብኚዎች ሀገር ያላትን እምቅ ሃብት በማስተዋወቅ አምባሳደር መሆናቸውን በማንሳት በዕውቀት የተካኑ ሆነው ገጽታን መገንባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ክልሉ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የባሕል እና የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት መሆኑንም ጠቅሰዋል። እነዚህ ፀጋዎች በተለያዩ አማራጮች (የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ጨምሮ) እንዲተዋወቁ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት። ለአብነትም በማህበራዊ ሚዲያ ቪዚት አማራ (Visit Amhara) እና  አማራ ካልቸር ኤንድ ቱሪዝም (Amhara Culture and Tourism) በሚሉ ድረ ገፆች በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ፀጋዎች እየተዋወቁ ይገኛሉ ብለዋል። በተጨማሪም አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንን (አሚኮ) ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙኃንን እየተጠቀመ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል። በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ቱሪዝም ሰላምን ይፈልጋል ያሉት አቶ ዓባይ መንግሥቴ ጎብኚዎች በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው በሰላም እንዲዝናኑ እና እንዲጎበኙ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል። ቱሪዝም ገጽታን ከመገንባት እስከ ገቢ ማሳደግ የሚኖረውን አበርክቶ ለማሳደግ የቅርስ ልየታ፣ ዕድሳት፣ ጥበቃ እና ልማት በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።

 

መረጃ

የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (World Tourism Organization) በሚያስቀምጠው መስፈርት መሰረት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረግ ጉዞ ሁሉ ቱሪስት ሊባል አይችልም። ቱሪስት ለመባል አንድ ሰው ከሚኖርበት አካባቢ ወጥቶ መዋል እና ማደር፣ መዝናናት፣ አልጋ መከራየት፣ ለአስጎብኚ መክፈል፣ ምግብ መመገብ… በአጠቃላይ ከ24 ሰዓት የበለጠ ጊዜያትን ማሳለፍ ይጠበቅበታል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here