ጢያ

0
19

ከአዲስ አበባ 86 ኪሎ ሜትር ርቀት  ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል  ጉራጌ ሶዶ ወረዳ ውሰጥ የጢያ ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስን እናገኛለን። ብርሊያንት ኢትዮጵያ በተሰኘ ድረገፅ ላይ እንደተፃፈው አዳዲስ የቁፋሮ ምርምር በስፍራው የተካሄደ ሲሆን አሁን 40 ያህል ቅርሶች ከምድር ተቆፍረው ወጥተዋል። ነገር ግን እስካሁን ከእይታ የጠፉ ብዙ የተቀበሩ ቅርሶች እንደሚኖሩ ይገመታል።

የጢያ ትክል ድንጋዮች በሶዶ አካባቢ ካሉ 160 የድንጋይ ሀውልት የቅርስ ስፍራዎች አንዱ ነው። በጢያ ከ45 በላይ የተተከሉ ድንጋዮች አሉ። ጥቂቶቹም ለተጨማሪ ጥናት እና ምርምር ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተወሰዱ መረጃዎች ያመለክታሉ። አብዛኛዎቹ የጢያ ትክል ድንጋዮች ቁመት ከአንድ ሜትር እስከ ሦስት ሜትር ሲሆን ትልቁ ደግሞ አምስት ሜትር ይደርሳል። ትክል ድንጋዮቹ ጠፍጣፋ እና ሞለል ያለ ቅርፅ አላቸው። ድንጋዮቹ  የተለያዩ ነገሮችን በሚወክሉ  ምስሎች አጊጠዋል። አብዛኞቹ የተቀረፁት ምስሎች ጎራዴዎች ናቸው። ከዚያ በተጨማሪ ጥንድ የበሬ ቀንድ፣ የተጋደመ መስቀል፣ የተክሎች ወይም የቅጠሎች ምስል፣ ጋሻ እንዲሁም ከበሮ ይታያሉ።

በጢያ ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ከ45 እስከ 48 የሚደርሱ ታሪካዊ ትክል ድንጋዮች እንደተተከሉ ይገመታል። ትክል ድንጋዮቹ ተበታትነው  ሦስት ቦታዎች ላይ ይገኛሉ፤ አንደኛው በዋናው የጢያ  ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ ውስጥ ያሉት 41 ትክል ድንጋዮች ናቸው። ወደ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ  ደግሞ አራት ትክል ድንጋዮችን የያዘ ሌላ ምድብ እናገኛለን። በሦስተኛነት ከዋናው መካነ ቅርስ ስፍራ 25 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ደግሞ ሦስት የትክል ድንጋዮች ያሉበት ስፍራ አለ።

በዋናው መካነ ቅርስ ውስጥ 41 ትክል ድንጋዮች ያሉ ሲሆን በርካታ ምስሎች ተቀርፀውባቸው ይታያል። ቅርሶቹ በ1972 ዓ.ም  በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። በ1974 ዓ.ም ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ እና በፈረንሳይ ተመራማሪዎች በአካባቢው የቁፋሮ ምርምር የተካሄደ ሲሆን በውጤቱም ከ700 እስከ 900 ዓመታት የቆየ የነገሥታት፣ የታዋቂ ሰዎች እና የተዋጊዎች መቃብር ተገኝቷል። በቁፋሮውም 52 የሰው አጥንቶች ተገኝተዋል። ከአጥንቶቹም ጋር የሸክላ ስብርባሪዎች፣ ባልጩት፣ ጨሌ፣ ዶቃ እና ሰዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ሌሎች መገልገያዎች አብረው ተገኝተዋል።

የጢያ ትክል ድንጋይ የአውሮፓውያንን ዓይን መሳብ ከጀመረ ብዙ ዓመትን ያስቆጠረ ሲሆን የዛሬ 84 ዓመት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ጀርመናዊ አጥኚ በዚህ ሥፍራ በኩል አልፎ እንደነበረ እና የጎራዴ ምስል ያላቸው የድንጋይ ትክሎች እንዳየ በጥናቱ አመልክቷል:: ከዚህ አጥኚ ቀደም ሲልም ኑቪለ እና ፔር ዛይስ (Neuville and Pere Azais.) የተባሉ አውሮፓውያን ጥያን መጎብኘታቸውን የዩኔስኮ ጥናቶች ያመለክታሉ::

ተረት

መልካምነት

ሁለት  ሃብታም እና ድሃ ወንድማማቾች ነበሩ:: ሃብታሙ ድሃ ሰዎችን በፍፁም አይወድም ነበር:: ድሃው ግን ጥሩ ሰው ነበር:: ድሃው ለእንግዶች የሚያካፍለው ነገር ባይኖረውም ያለውን ይሰጥ ነበር:: ሃብታሙ ግን ማንም ሰው ወደ እርሱ ቤት እንዲመጣ አይፈልግም ነበር::

እንግዶች ወደ ድሃው ወንድም በመጡ ጊዜ ድሃው “እዚህ ልናካፍላችሁ የምንችለው ምንም ማረፊያ ቦታ ስለሌለን ልናሳድራችሁ አንችልምና እባካችሁ ወንድሜ ዘንድ ሄዳችሁ ጠይቁት” ይላቸዋል:: እነእርሱም ወደ ሃብታሙ ቢሄዱም እንደተለመደው “አዚህ ለእናንተ የሚሆን ቦታ የለም” ብሎ አባረራቸው:: ተመልሰውም ወደ ድሃው ወንድም ቤት ሄዱ:: ከሃብታሙ ወንድም ቤት ተባረው የተመለሱ እንግዶችም ድሃው ሰው “አንተ አትቸገር ከደጃፍህ ላይ አድረን ጠዋት እንሄዳለን” አሉት::

ድሃው ወንድም እና ሚስቱም “የምትመገቡትን ምን ልንሰጣችሁ እንችላለን?” ብለው ጠየቋቸው:: “አትቸገሩ የራሳችንን ምግብ ይዘናል” ብለው መለሱላቸው:: የሚጠጡትንም ውኃ ሰጧቸው:: ውኃውንም ከጠጡ እና የራሳቸውን ምግብ ከበሉ በኋላ በዚያው ሌሊት ተነስተው ሄዱ:: ባል እና ሚስቱም ከእንቅልፋቸው ሲነቁ እንግዶች ሄደው ቤታቸው ግን በሃብት ተሞልቶ አገኙት:: መልካምነት ለራስ ነው ማለት ይህ ነው::

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ተረቶች መጽሐፍ::

 

ይሞክሩ

  1. ለአህያ አናፋ ከተባለ ለአንበሳ ምን ይባላል?
  2. የዶሮ ማደሪያ ስሙን ጥቀስ?
  3. የምስጥ መኖሪያ ምን ይባላል?

መልስ

  1. አገሳ
  2. ቆጥ
  3. ኩይሳ

 

ነገር በምሳሌ

መልካም ጭራ ለደብተራ ማበረታታት ጥሩ ለሚሰራ ሰው ነው፡፡

 

መልካም ተመኝ መልካም እንድታገኝ

ጥሩ ላደረገ ጥሩ ያጋጥመዋል::

 

መልካም ወገን የፀሐይ ወጋጋን

አስተማማኝ ሰው ለችግር ጊዜ ይደርሳል፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here