ተስፈኛዉ የአትሌቲክስ ፕሮጀክት

0
18

ለብዙዎቻችን ባህርዳር አትሌቶች የሚገኙባት ከተማ ላትመስለን ይችላል።ከከተማዋ ስፋትና እድገት አንጻር በስሟ የሚጠራ አትሌቲክስ ክለብ አይደለም ማዕከል እንኳ የሌላት ከተማ በመሆኗ ከባህርዳር የተገኘ አትሌት ነው ተብሎ ስሙ የሚጠራ ታላቅ አትሌት በብዛት ሰምተን አናውቅም። ሆኖም ጨርሶ የላትም ሳይሆን እነ አለባቸው ደርሶ(አፖስቶ) የመሳሰሉ በአንድ መቶ እና ሁለት መቶ ሜትር የአጭር ርቀት ሯጮችከባህርዳር አልፎ ኢትዮጵያን ወክሎ የተወዳደረው አትሌት የተገኙባት ከተማ መሆኗን ለተመለከተ አእምሯችን ላይ የሚመጣው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ ያገኛል፤ ባለመሰራቱ የአትሌቶች መገኛ ከተማ አትሌት አልባ ሆናለች።

አንባቢያን ለዛሬ እንዲገነዘቡት ወደ ፈለኩት ነጥቤ ስወስዳችሁ ባህርዳር ከተማ ሞቃታማ የአየር ንብረት የታደለች ከተማ መሆኗ ይታወቃል።የባህርዳር አየር ንብረት ደግሞ ለአጭርና መካከለኛ የሩጫ አይነቶች ተስማሚ ብትሆንም ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት አካል አልተገኘም።የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከዘጠኝ አመት በፊት የአትሌቲክስ ፕሮጀክት አቋቁሞ ተተኪዎችን ለማፍራት ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።

ከሰሞኑ የአትሌቲክስ ፕሮጀክቱን ለማየት  ወደ ዩኒቨርሲቲው ጎራ ብየ ባገኘሁት መረጃ ፕሮጀክቱ ባለፉት ዘጠኝ አመታት ከታሰበው በላይ እድገት እያሳየ ይገኛል።ከ48 በላይ አትሌቶችን ሌሎች ክለቦች ማዕከላት እና አካዳሚዎች ማበርከት የቻለው ይህ ፕሮጀክት እድገቱ ከእድሜው በላይ ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት ግን ውጤታማነቱን ገደል የሚከት ነው።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አትሌቲክስ ፕሮጀክት በሶስት አሰልጣኞች ይሰለጥናል።ቁጥራቸው ከ50 በላይ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ የፕሮጀክቱ አባል ናቸው።ፕ ሮጀክቱ ለሩጫ ፍቅር ያላቸውን አትሌቶች በየአመቱ እየመለመለ ታላቅ አትሌት የማፍራት አላማ አድርጎ እየሰራ ይገኛል ሲል አሰልጣኝ ደሴ አታላይ አጫውቶኛል። አሰልጣኙ ሲቀጥል የአትሌቲክስ ስራ አድካሚ ነው፤ በተለይም የለፋንባቸውን ልጆች በየአመቱ ለሌሎች ክለቦች እንለቃለን፤ በምትካቸው አዳዲስ አትሌቶችን መልምለን ለማብቃት ብዙ ውጣ ውረድ እናሳልፋለን ብሎኛል። አትሌቶችን ማብቃትና ማሳደግ ብሎም ውጤታማ ማድረግ ስራችን ቢሆንም ድካማችን ዋጋ የሚያጣው እዚህ ከተማ ላይ የአትሌቲክስ ማዕከል ባለመኖሩ የለፋንባቸውን አትሌቶች የሚመሰገኑባቸው ሌሎች ማዕከላት እና ክለቦች ናቸው ብሎኛል።

በአትሌቲክስ ፕሮጀክቱ ውስጥ ባለፈው አመት ብቻ 12 አትሌቶችን አሰልጥኖ ወደ ተለያዩ ክለቦች መላክ የቻለው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አትሌቲክስ ፕሮጀክት የውጤታማነቱን ያህል በዩኒቨርስቲው በኩል የተሰጠው ድጋፍ እምብዛም የሚወደስ አይደለም። አትሌቶች በሰጡኝ ሀሳብ መሰረት ዩኒቨርሲቲው የመለማመጃ ሜዳ ፈቅዶላቸው እየሰሩ ነው ትጥቅና የስልጠና ቁሳቁስ ጉድለት እንዳለባቸው ነግረውኛል።ከዩኒቨርስቲው ተገኝተው አሁን በአለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ አትሌቶች የፈሩበት ዩኒቨርሲቲ የስራውንና የድካሙን ውጤት ማንጸባረቅ የሚችል አርማና ሎጎ ያረፈበት አልባሳት አሰርቶ ለአትሌቶቹ መስጠት አለመቻሉ ስራውን እንዳጎደለው አትሌቶች ያነሱት ቅሬታ ነው።

ፕሮጀክቱን በተመለከተ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስፖርት አካዳሚ ዲን ሲሳይ አዱኛ የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑት አንዱ ናቸው።ከክትትል አንጻር ዩኒቨርስቲው ምን እየሰራ ይሆን ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ለአትሌቲክስ ፕሮጀክቱ በሚጠበቀው ልክ ባይሆንም ክትትል እንደሚደረግ ተናግረው በተቻለ መጠን በተያዘው በጀት አመት ወደ ማዕከል ለማሳደግ ታቅዶ ተፈጻሚ እንዲሆን እየሰራን ነው ብለዋል።ለዚህ ደግሞ የባህርዳር  ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት  ዶክተር  መንገሻ አየነ  ፈቃደኛ  ናቸው ብለዋል ዲኑ ሲሳይ አዱኛ።ትጥቅን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሲሳይ አዱኛ በዚህ አመት ለእግር ኳሱ የክረምት ሰልጣኞች እንዳደረግነው ሁሉ ለአትሌቲክስ ፕሮጀክቱ አባላትም የባህርዳር የዩኒቨርሲቲው  አርማ ያለበት ትጥቅ አሰርቶ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።

ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ይህ የአትሌቲክስ ፕሮጀክት ለስራ ጉዳይ ተንቀሳቅሸ በክልሉ ውስጥ ከተመለከትኳቸው ፕሮጀክቶች በስልጠና ቁሳቁስ ረገድ የተሻለ ሆኖ ተመልክቸዋለሁ።ለምሳሌ የመሰናክል ሩጫ የሚሰራበት ቁሳቁስ በፕሮጀክት ደረጃ ብዙዎች የሌላቸው ቢሆንም እዚህ ግን  መኖሩን ተመልክቻለሁ። ከዚያ ባለፈ በኢትዮጵያ የመቶ ሜትር ውድድር ባለክብረወሰን የሆነችው ፈጣኗ አትሌት ራሄል ተስፋየ ከዚህ የአትሌቲክስ ፕሮጀክት የተገኘች መሆኗን ላስተዋለ ሞቃታማዋ ከተማ ባህርዳር የምርጥ አትሌቶች መፍለቂያ የመሆን እድል እንዳላት አሰልጣኞቹ ተናግረዋል።

አንባቢያን የተነሳሁበትን ነጥቤን ከመቋጨቴ በፊት ለአትሌቲክስ ፕሮጀክቱ ተስፋ የሚሆን  አንድ ነጥብ ልጨምር። የውሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እያሉ የተንታ አትሌቲክስ ማዕከል ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ ትልቅ ስራ ስለመሰራታቸው የተነገራላቸው ዶክተር መንገሻ አየነ አሁን የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መሪ መሆናቸው ለፕሮጀክቱ ትኩረት ሰጥተው በመስራት እንደሚያሳድጉት ተስፋ ተደርጓል።

 

(መልሰው ጥበቡ)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here