በህንድ ለቤት እንስሳት በነበራቸው ፍቅር መንስኤነት ተቀራርበው ለትዳር የበቁ ጥንዶች በአንድ ጣሪያ ስር ለመኖር ይዘዋቸው በገቡት ውሻ እና ድመት መካከል ትንኮሳ እና ተደጋጋሚ ጥቃት እየተፈጠረ ሊስማሙ ባለመቻላቸው ተጋቢዎቹ ለመለያየት ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በ2024 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነበር ትዳር መስረተው በአንድ ጣሪያ ስር መኖር የጀመሩት፡፡ ጥንዶቹ አፍላ የጫጉላ ቤት ጊዜያቸውን በፍቅር ቢያሳልፉም ውለው ሲያድሩ የየግል ባህሪያቸው እየገነነ ለከረረ ፀብ ተዳርገዋል፡፡ ለፀባቸው መንስኤ የሆኑት ደግሞ ለትዳራቸው መንስኤ የሆነበሩ የባልውሻ እና የሚስት ድመት መሆናቸው ነው ለንባብ የበቃው፡፡
ፀባቸው ከሮ ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ፍቺ ለመፈፀም የፀባቸውን መንስኤም አስረድተዋል፡፡ ሚስት የባል ውሻ በድመቷ ላይ የሚያደርሰው ትንኮሳ እና ባል ድመቷ ላይ የሚፈፅመው ዱላ በእጅጉ እንዳስመረራት ተናግራለች፡፡
ባል በበኩሉ ድመቷ በቤታቸው ውስጥ በተቀመጠው ሰው ሰራሽ የዓሣ ማኖሪያ መስታዉት ስታንዣብብ በመመልከቱ እንዳልወደዳት ነው ያስረዳው::ተጋቢዎቹ በተናጠል ባል ለውሻው፣ ሚስት ለድመቷ ወግነው ተከራክረዋል- ሊያስታርቁ በሸመገሉ ጓደኞቻቸውም ፊት፡፡
ተጋቢዎቹ አንዱ የአንዱን ሊታገስ እና ሊቻቻሉ ፈቃደኛ ባለመሆናቸውም ወደ ችሎት አምርተዋል፡፡
ፍርድ ቤት ቀርበው ፍቺውን ለማፀደቅ “ነገርን ከስሩ…” እንዲሉ ጭብጣቸውን አሰምተዋል- ለዳኞች፡፡
ዳኞቹም ሁኔታውን በውል ገምገመው ፍቺውን አፅድቀዋል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም