ቻይና በተንሳፋፊ ዓየር የተሞላ የኘላስቲክ ፊኛ ላይ ተርባይን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል የተሳካ ሙከራ ማድረጓን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::
ሀገሪቱ አረንጓዴ ታዳሽ ኃይልን ተተካይ የነፋስ ማመንጫዎች ከሚፈልጉት ከፍተኛ ወጪ በአነሰ ለየት ያለ መፍትሄ ዘይዳ ማስተዋወቋ ነው ለንባብ የበቃው::
ቻይና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት አቅዳ እየሰራች ካለችው አንዱ መሆኑ የተነገረለት ተንሳፋፊው ዓየር የተሞላ ኘላስቲክ በተፈለገ ጊዜ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል በመሆኑ ተመራጭ ነው ተብሏል::
ዓየር የተሞላው በዓየር ላይ የሚንሳፈፈው ኘላስቲክ ቁመቱ 13 ፎቅ ስፋቱ የቅርጫት ኳስ ሜዳ ያህል መሆኑ ተጠቋማል:: አዲሱ ቻይና ተግባራዊ ያደረገችው ስልት ከተለምዷዊው ተተካይ ከነፋስ ኃይል ማመንጫ የበለጠ ፈጣን እና አስተማማኝ መሆኑ ተገልጿል በባለሙያዎች::
ተንሳፋፊውን ዓየር የተሞላ ኘላስቲክ በማስተንፈስ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር ወይም ማንቀሳቀስ መቻሉ የአዲሱ ታዳሽ ኃይል ማመንጫ ጠንካራ ጐን ነው- እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ::
በቻይናው የቤጂንግ ሊኒዮንቹዋን የኃይል አምራች ኩባንያ የተመረተው አዲሱ ስልት እስከ 100 ኪሎዋት በሚጭኑ 12 ጀኔሬተሮች በመታገዝ ኃይል አመንጭቶ በኤሌክትሪክ ገመዶች ያለ ማቋረጥ ኃይል ማስተላለፍ ይችላል::
አዲሱ ስልት ከነፋስ ኃይል ለማመንጨት ቋሚ (ማማ) ምሰሶዎችን እና ተሽከርካሪ ዘንጐች ስለማያስፈልገው በአነሰ ወጪ የሚገነባ መሆኑ ነው በድረ ገፆች የተገለፀው:: ከሁሉም በላይ ርቀት ባለው ቦታ በመትከል ኃይል ማመንጨት እና ማከፋፈል ማስቻሉም ተመራጭ አድርጐታል::
በመጨረሻም የቤጂንጉ ሊኒቶንቹዋን ኃይል አምራች ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት እስከ 1500 የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን ለማምረት ማቀዱ ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም