ሴት  ነጋዴዎች በዲጂታል ገበያው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተጠየቀ

0
20

ከሰሞኑ በአማራ ክልል ለአነስተኛ እና ለመካከለኛ የንግድ አንቀሳቃሾች የብድር አቅርቦት ተግዳሮቶች፣ የገበያ ማረጋጋት እና የሥራ ፈጠራ ፖሊሲ እና አዋጅን በተመለከተ በመንግሥት፣ በፋይናንስ ተቋማት እና በግሉ ዘርፍ መካከል  የምክክር መድረክ ተካሂዷል::

የአማራ ክልል ሴት ነጋዴዎች ማሕበር ፕሬዝዳንት ሲስተር ትቅደም ወርቁ እንደገለጹት  ማሕበሩ ከተመሠረተ 25ኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፤ ይህን ሲያከብርም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና የጀመረችበት ወቅት ላይ ሆኖ ነው:: በመሆኑም ሴት ነጋዴዎች የሚወዳደሩት ከኢትዮጵያ ነጋዴዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካዊያን ነጋዴዎች ጭምር በመሆኑ ራሳቸውን  ለውድድሩ  ብቁ  ማድረግ  አለባቸው:: በተለይም ወደ ዲጂታል የገበያ ሥርዓት ለማስገባት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ዕውቀት ሊያዳብሩ ይገባል ብለዋል:: ማሕበሩ ሴት ነጋዴዎች ለክልሉ እና ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ከማድረግ ባለፈ መብት እና ጥቅማቸውን ለማስከበር ታላሚ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አክለዋል::

በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ ነጋዴ ሴቶች  አሁን ካለው የዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ የብድር መጠን ቢጨመር፣ የመሥሪያ እና የመሸጫ ቦታዎችም ቢመቻቹ የሚሉ ጥያቄዎችን  አንስተዋል፤ የመንግሥት እና የግል ተራድኦ ድርጅቶች ተወካዮችም  አሠራር በሚፈቅደው መጠን እንደሚያመቻቹላቸው ቃል ገብተውላቸዋል::

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አትክልት አሳቤ በሰጡት ምላሽ ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው በልዩ ልዩ ንግድ ዘርፎች ተሠማርተው እየሠሩ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው:: ቢሮው አጋጠሙ የተባሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን በመፍታት ነጻ እና ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት እንዲስፋፋ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል:: የአሠራር ክፍተትን እና መጓተትን ለማስቀረትም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዲጂታል የገበያ ሥርዓትን መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል::

የአማራ ክልል ሴት ነጋዴዎች ማሕበር በ121 ከተሞች እና ወረዳዎች ከ151 ሺህ በላይ ሴቶችን ወክሎ እየሠራ ይገኘኛል::

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here