ውለታ ለባለውለታዎች

0
21

አረጋዊነት ምንድን ነው? ስንል በ1980 የታተመ  ጥናት (Glascock, 1980) በታዳጊ ሀገራት ውስጥ ከእድሜ መግፋት ጋር አያይዞ  በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አስፍሯል::እነሱም የእድሜ ዘመን መግፋት፣ የማኅበራዊ ሚና ለውጥ እና በአቅምና ችሎታ ላይ ለውጥ መታየት  ናቸው::

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትርጉም መሠረት ደግሞ አረጋውያን የሚባሉት እድሜአቸው 60  እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው:: የድርጅቱ  መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ ዕድሜያቸው 60 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ በዓለማችን የሚገኙ አረጋውያን ቁጥርም በ1950 እ.አ.አ 200 ሚሊዮን፣ በ2000 እ.አ.አ 590 ሚሊዮን እንደነበር አመላክቷል::  እ.አ.አ በ2050 ደግሞ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን እንደሚደርስ ትንበያውን አስፍሯል::

በኢትዮጵያ ያለው የአረጋውያን ቁጥር በ1998 ዓ.ም መረጃ መሰረት 3 ሚሊዮን 568ሺህ 810 ነበር::  ይህም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሕዝብ አራት ነጥብ ስምንት  ከመቶ ያህሉን የሚወክል ነበር::  የአረጋውያን ቁጥር በኢትዮጵያ እስከ 2014 ዓ.ም በገጠርና በከተማ  ከአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊየን በላይ እንደሚሆን  የማእከላዊ ስታትስቲክስ ትንበያ ያሳያል::

ስለአረጋዊነት አረጋውያን ምን ያላሉ? በማለት ለአረጋውያን ጥያቄ አንስተን ነበር:: በጡረታ የሚተዳደሩት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አቶ አበባው ታከለ እንደሚሉት ሁሉም ሰው ወጣትነት ዕድሜ ላይ ቢቆምም አረጋዊነትን  በቀላሉ የሚደረስበት የዕድሜ ክልል ነው:: አረጋዊነት በወጣትነት የነበረው ብርታት እና ጉልበት ከዕድሜ ጋር ተያይዞ እየደከመ  የሌሎቹን ድጋፍ የሚፈለግበት የዕድሜ ክልልም ነው::

ሁሉም አረጋዊ የገንዘብ ድጋፍ ይፈልጋል ማለት እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ አበባው፤ ድጋፉ ከአጠገባቸው ሰዎች ባይኖሩ እነሱን ተክቶ የማስተባበር፣ በጤና ተቋማት፣ በመጓጓዣ/ትራንስፓርት/ ቦታዎች እና በባንኮች አገልግሎት ሲፈልጉ መጋፋት ስለማይችሉ ቅድሚያ ሠጥቶ ማስተናገድንም እንደሚጨምር ነው::

“ሀገራችን ዛሬ ላይ ላለችበት ደረጃ ትላንት የራሳቸውን አሻራ አሳርፈው ያለፉትን ስናከብር እኛም ነገ የሚያከብረን ትውልድ ይፈጠራል፤ አረጋዊያንን በየዘርፉ በመደገፍ የሁሉም ኃላፊነት ከመሆኑ ባሻገር መንግሥትም ቢሆን የሀገር ባለውለታን ማሰብ እና ማሳተፍ የሚችል ፓሊሲ እና ተግባ ሊኖረው ይገባል“ በማለትም አቶ አበበ ለአረጋውያን ትናንት ለሀገራቸው ባበረከቱት ተግባር ዛሬ ሁሉም ሊደግፋቸው እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::

ለሀገራቸው በውትድርናው ዘርፍ ያገለገሉት ሻንበል የሽብር ሞላ በበኩላቸው በወጣትነት ዕድሜያቸው  ደማቸውን እና አጥንታቸውን ለሀገራቸው እንደገበሩ ያነሳሉ:: በጦር ጉዳት  ከውትድርና ከወጡ በኋላ  የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተው ቤተሰባቸውን ይመሩ ነበር፤  ዛሬ ላይ ደግሞ በልጆቻቸው ድጋፍ እንደሚኖሩ ያነሳሉ::

“ዕድሜ እንዳለ አይቀጥልም፤ በአብዛኛው የዕድሜ መጨመርን ተከትሎ   ደግሞ የገንዘብ እጥረት፣ የጤና መጓደል፣ የአቀም ማነስ…. ይከሰታል:: ለሀገራቸው ካደረጉት ውለታ እና አስተዋፅኦ አንፃር መንግሥት ድጋፍ ማድረግ የሚችልበት መንገድ ሊኖር ይገባል:: በሀገራችን በየመንገዱ ወድቀው የምናያቸው አረጋዊያንን ሊደግፉ የሚችሉ ተቋማት በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን  በመንግሥት በኩል ተከፍቶ የምግብ ድጋፍ ለሚሻው የምግብ፣ ቤት ለሚያስፈልገው ቤት ፣የጤና ችግር ላለበት የጤና ድጋፍ እየተሠጠ በአግባቡ ውለታው ሊታሰብ ይገባል“ በማለት ጠይቀዋል::

ሻንበል የሽብር በዕድሜ መግፋት በየቦታው የሚወድቁ አረጋዊያን በርካታ ልምድ ፣ ዕውቀት …እንዳላቸው ጠቁመዋል:: ነገር ግን ምንም ጥቅም እንደሌለው ያላቸው እውቀት ተንቆ  ሳንጠቀምበት መኖሩ ቀጣይም የሚመጣው ወጣት የነገ እጣ ፈንታ ካለፈው የማይሻል እንዲሆን ያደርገዋል:: በመሆኑም በዕድሜያቸው ካገኙት ትምህርት እና የሕይወት ልምድ ልጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ወጣቱ ሁሉ ልምድን የሚቀስምበት መድረክ፣ በዕድሜያቸው ሁሉ ያላቸውን እውቀት የሚያካፍሉ እና መሥራት የፈለገ አረጋዊ ሁሉ  ሊሠሩበት የሚችሉትን አጋጣሚ ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቁመዋል::

በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ  ቢሮ እየተደገፈ የአረጋዊያን ሕንፃ  ተሠርቶ አንዳንድ ድጋፎች ቢኖሩም ያለውን የአረጋዊያን እምቅ ሃብት በመጠቀም በአግባቡ ሰብስቦ በመርዳት እና ቅድሚያ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ግን አሁንም ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅ ነው ሻንበል የሽብር ያሳሰቡት::

በባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ሰብለ ዘውዱ በ2017 ዓ.ም በበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በከተማው ለሚገኙ አረጋውያን የተለያዩ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል። ሌሎችን የማኅበረሰብ ክፍሎች በማስተባበር የአልባሳት፣ የዕለት ምግብ እና የንጽህና መጠበቂያ ችግር ላለባቸው የመደገፍ ሥራ ተከናውኗል።

በበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመምሪያው አስተባባሪነት ለአረጋውያን 12 ቤቶች ተሠርተው መተላለፋቸውን ኃላፈዋ ጠቁመዋል።  እንደ ከተማ አሥተዳደርም 31 ቤቶች ቅድሚያ ለአረጋውያን ተሰጥቶ መተላለፋቸውን ተናግረዋል። ለ14 አረጋውያን ደግሞ መሥራት እንዲችሉ የመሥሪያ ሱቆች እንዲሰጣቸው መመቻቸቱንም ተናግረዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ለአረጋውያን 28 ቤቶችን በአዲስ ለመሥራት በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን እና 172 ቤቶችን የማደስ እንዲሁም ለ111 አባወራ አረጋውያን የምግብ ፍጆታ የማቅረብ ተግባር እየተከናወነ ነው::

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ንጹሕ ሽፈራው በበኩላቸው አረጋውያን የሀገር  ባለውለታ ናቸው፤ ለትውልዱ ሀገርን፣ እሴትን፣ ባሕል እና ወግን ጠብቀው የሚያስተላልፉ ናቸው:: አረጋውያን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የሠሩ የሀገር አለኝታ በመሆናቸው በጤና መታወክ፣ በእርጅና፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በመፍታት፣ ለእነሱ የሚገባቸውን እንክብካቤ እና ፍቅር በመስጠት በኩል ከቢሮው ጎን በመሆን  ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል መሳተፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል::

 

ዜና

አረጋውያን ለሀገር በርካታ ሥራዎችን ያበረከቱ ባለውለታ መሆናቸው ተጠቆመ

አረጋውያን የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው፤ በዕድሜያቸው በርካታ ዕውቀቶች፣ ልምዶች እና ጥበቦችን አግኝተዋል፡፡ በቀለም ትምህርት፣ በኑሮ ሁኔታ እና በተግባር ተምረው፣ አስተምረው ትውልድ አንጸዋል፡፡ እነዚህ አረጋውያን ለሀገር በርካታ ሥራዎችን የሠሩ እና  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አደባባይ  ተከብራ የኖረች ሀገር እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት  ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማቆየት ያልወጡት ዳገት፣ ያለወረዱት ቁልቁለት እንደሌለ የማህበሩ አባላት ጠቁመዋል፡፡

 

መምህር አትንኩት አባዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር አባል ናቸው። አረጋውያን ለሀገር ብዙ የሠሩ፣ ተማሪዎችን በአግባቡ ያስተማሩ፣ ሀገራቸውን ከጠላት የጠበቁ፣ የሃይማኖታዊ አገልግሎት የሰጡ፣  በሁሉም ሙያ ላይ በመሳተፍ በወጣትነት ዘመናቸው ለሀገር ትልቅ ሥራ በመሥራት ውለታ የዋሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

 

ለሀገራቸው ብዙ ያገለገሉ ነገር ግን በመንገድ ዳር የወደቁ፣ ረዳት ያጡ በተለያዩ የሥራ መስኮች የሠሩ አረጋውያን መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን በወጣትነት ዘመናቸው ለሀገር ትልቅ ሥራ የሠሩ አረጋውያን በአንድ ማዕከል ተሰባስበው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

ሌላው የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር አባል መምህር ሥራው ይሁን ለአሚኮ እንደገለጹት አረጋውያን ባሳለፏቸው የዕድሜ ዘመናቸው በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ሀገር ማገልገላቸውን ጠቁመዋል፡፡ በግላቸው የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው፣ ልጅ አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡ የሀገር መሠረቱ የቤተሰብ ጽናት እና ጥንካሬ በመኾኑ ለሀገር ባለውለታ ተክተዋል ነው ያሉት፡፡ በተለያዩ የሥራ ዘርፎችም ሀገራቸውን ያገለገሉ በመሆናቸው ለሀገር ባለውለታ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁንም በእርጅና ዘመናቸው ለሀገር የሚሠሯቸው ሥራዎች ስላሉ “አረጋውያን ታላቅ የሀገር ቅርስ ናቸው” ነው ያሉት።

 

አረጋውያን እድሜ የመከራቸው በመሆኑ ንግግራቸው እና ምክራቸው በሙሉ ሰላም መሆኑን አንስተዋል፡፡ ቤተሰብ በፍቅር እና በሰላም እንዲኖር፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ተግባብተው እና ተስማምተው እንዲኖሩ በመምከር እና በመምራት፣ ግጭት ሲኖር በማስታረቅ ሀገርን ሰላም እንድትሆን የሚመክሩ እና የሚዘክሩ በመሆናቸው ለሰላም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ካለው ብዛት አንጻር በቂ ነው ባይባልም በማኅበራዊ ዘርፍ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት አበረታች ነው ብለዋል፡፡ ለሀገር ብዙ የሠሩ እና ባለውለታ የሆኑት አረጋውያንን በተለያየ መንገድ መደገፍ እንደሚያስፈልግም ጠይቀዋል፡፡

 

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here