በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ 585 ሺህ 879 ተማሪዎች መካከል 48 ሺህ 929ኙ የማለፊያ ነጥብ (የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ) ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒሥትሩ ኘሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ መስከረም ወር መግቢያ ላይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል:: ይህም ስምንት ነጥብ አራት ከመቶ ነው:: ውጤቱ ከባለፈው የትምህርት ዘመን ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው የተሻለ ነው:: ባለፈው የትምህርት ዘመን የማለፊያ ውጤት ያመጡት ተማሪዎች አምስት ነጥብ ሁለት ከመቶ እንደነበር ልብ ይሏል::
ሚኒሥትሩ እንዳሉት በ2016 የትምህርት ዘመን አንድ ሺህ 263 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላሳለፉም ነበር:: በተመሳሳይ በ2017 የትምህርት ዘመንም አንድ ሺህ 249 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም:: 61ዱ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በአማራ ክልል እንደሚገኙ ተጠቁሟል::
ውጤቱ በየትምህርት ተቋማቱ ሲገለጽ ደግሞ ካስፈተኗቸው ተማሪዎች መካከል አዳሪ ት/ቤቶች 81 ነጥብ አንድ በመቶ፣ ዓለም አቀፍ የማኅበረሰብ ት/ቤቶች 86 ነጥብ ስድስት በመቶ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ /የግል/ ት/ቤቶች 51 በመቶ እንዲሁም የመንግሥት ት/ቤቶች አምስት ነጥብ ስድስት በመቶ ማሳለፋቸውን ሚኒሥትሩ አስታውቀዋል:: ውጤቱ እንደሚያመላክተው የአዳሪ፤ የዓለም ዓቀፍ እና የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ውጤት ከመንግሥት ት/ቤቶች የላቀ ነው::
እኛም በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኙ ት/ቤቶች መካከል ያስፈተናቸውን 41 ተማሪዎቹን ሙሉ በሙሉ ባሳለፈው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ማበልፀጊያ ማዕከል /ስቲም ሴንተር/ አቅንተን ነበር:: የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ተስፋሁን እንዳሉት ማዕከሉ በየዓመቱ ተማሪዎችን የሚቀበለው በስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የላቀ ውጤት አምጥተው የመግቢያ ፈተናውን ማለፍ የሚችሉ 50 ተማሪዎችን ብቻ ነው:: በሀገር አቀፍ ፈተናውም 41 ተማሪዎችን አስፈትኖ ከዚህ ውስጥ 26ቱ ከፍተኛ (ከ500 በላይ) ውጤት አስመዝግበዋል::
በስምንተኛ ክፍል ባስመዘገቡት የላቀ ውጤት በማዕከሉ ተወዳድረው ትምህርታቸውን ከተከታተሉት መካከል ደግሞ ሰላማዊት አያሌው አንዷ ናት:: ከስድስት መቶው ከፍተኛ ውጤት /ከ500 በላይ/ ካስመዘገቡ 26 ተማሪዎች መካከልም 549 በማምጣት አንዷ ሆናለች::
ሰላማዊት እንደምትለው በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የረዳት ከዘጠነኛ ክፍል ጀምራ በማዕከሉ ከገባች በኋላ የተሻለ ዕውቀት ባላቸው መምህራን፣ በተሟላ ቤተ መጻሕፍት፣ ለመማር ማስተማሩ ምቹ በሆነ ት/ቤት መማሯ ነው፤ ይህ ብቻ ሳይሆን በፊት የነበራት (ከታች የክፍል ደረጃዎች ይዛው የመጣችው መሠረት) ለአሁኑ ውጤት ሥንቅ ሆኗታል::
ተማሪ ሰላማዊት ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በተለያዩ ት/ቤቶች ተምራለች:: በቆይታዋም ወላጆቿ ያልገባትን ከማስረዳት ጀምሮ አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላት፣ የየዕለት ውሎዋን በመከታተል፣ እርሷም መምህራን በክፍል ሲያስረዱ በሚገባ መከታተሏ፣ ያልገባትን ጠይቆ ለመረዳት የምታደርገው ጥረትና ወደ ቤት ከተመለሰች በኋላም የጥናት መርሀ ግብር አውጥታ መተግበሯ የተሻለ ውጤት (ከታች ክፍሎች) ለማስመዝገብ አስችሏታል፤ ይህም ወደ ማዕከሉ እንድትገባ አቅም ሆናት:: አለፍ ሲልም በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት እንድታስመዘግብ አስችሏታል::
ተማሪዋ እንዳካፈለችን በማዕከሉ ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያለው የትምህርት አሰጣጥ ከቃል ባለፈ በተግባር የተደገፈ መሆኑ የበለጠ እንድትመራመር፣ የተለያዩ አጋዥ መጽሐፍትን እንድታነብ አስችሏታል:: ከዚህ በተጨማሪ መምህራን የሚያስተምሩበት ሥነ ዘዴ፣ ለጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ግልጽ መሆን፣ በማዕከሉ የሚሰጡ ፈተናዎች ለውጤት ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ መፍትሔን አመላካች እንዲሆኑ ማስቻላቸው ለውጤቷ ሌላው መሠረት ነው::
በተመሳሳይ መመህራን ከማስተማሪያ መጻሕፍት በተጨማሪ አጋዥ ያዘጋጃሉ፤ ይህም ተማሪዎች ተጨማሪ መረጃ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል::
“ተማሪ ዓላማው የተሻላ ውጤት በማምጣት ራስንም ሀገርንም ማሳደግ ነው” የምትለው ተማሪዋ ተማሪዎች ት/ቤት መጥተው ትምህርታቸውን በሚገባ መከታተል፣ ጥሩ ውጤት እንዴት ነው ማምጣት የምችለው? በማለትም ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ የጥናት ኘሮግራም በማውጣት መተግበር፣ በየት/ቤታቸው ያሉ አጋዥ መጻሕፍትን ማንበብ፤ ጥያቄ ለመጠየቅ አለመፍራት፣ የማያውቁትን ደግሞ የበላዮቻቸውን ብቻ ሳይሆን ታች ክፍል ያሉትን መጠየቅ የተረሳን ለማስታወስ ያስችላል” በማለት ምክሯን ለግሳለች::
ሌላው በማዕከሉ በ2017 የትምህርት ዘመን 556 በማምጣት ሦስተኛ ደረጃ የያዘው ተማሪ ናትናኤል አይዞህበል ነው:: ናትናኤል እስከ ስምንተኛ ክፍል በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ት/ቤቶች ትምህርቱን ተከታትሏል:: በትምህርቱም በየክፍሎቹ አንደኛ ደረጃን አስጠብቆ ዘልቋል:: ለዚህ ያበቃው ደግሞ አጋዥ መጻሕፍትን በማንበብ ጥልቅ ዕውቀት መጨበጡ፣ የክፍል ውስጥ ትምህርቱን በአግባቡ መከታተሉ፣ ያልገባውን መጠየቁ እና የራሱን የጥናት ስልት መከተሉ ስለመሆኑ ነው የነገረን::
ናትናኤል ከት/ቤት ውጭ ማጥናት ባለበት ሰዓት ያጠናል፣ የመዝናኛ ጊዜም አለው:: በየዕለቱ የተማረውን ማታ ለአንድ ሰዓት ለቤተሰቦቹ በእንግሊዘኛ ያቀርባል፤ ይህን ማድረጉ ሁሉም ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስለሚሰጥ ትምህርቱን በጥልቀት እንዲረዳ፣ በሰዎች ፊት ሀሳቡን ያለፍርሃት እንዲገልጽ እና በየዕለቱ የተማረውን እንዲያስታውስ ረድቶታል::
የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብም (ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ) የእሱ፣ የቤተሰቦቹ እና የምምህራን ድጋፍ ጥረት በእጅጉ እንዳገዘው ነው ያጫወተን::
በአንደኛ እና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ለውጤት ያበቃው ስነ ዘዴ ከማዕከሉ ከገባ በኋላም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉ ለስኬቱ አቅም እንደሆነው ይናገራል:: ተማሪው ኮምፒውተር ሳይንስ የማጥናት ፍላጐት እንዳለውም ነግሮናል::
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ማዕከል ርእሰ መምህር ዓለሙ ተስፋሁን ማዕከሉ ሥራ የጀመረው በ2004 ዓ.ም ከተለያዩ ክልሎች በክረምት መርሀግብር በየትምህርት ቤታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን አወዳድሮ በመቀበል እንደነበር ነግረውናል:: ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በስምንተኛ ክፍል ውጤት እና የመግቢያ ፈተና በመስጠት እያወዳደረ በየዓመቱ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ነው ብለዋል::
ርእሰ መምህሩ እንዳሉት የማዕከሉ ዓላማ ተማሪዎች በማዕከሉ ቆይታቸው በቀለም ትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻ ሳይሆን ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማድረግ ነው:: ለዚህም ውጤታማ እንዲሆኑም መምህራን ካሁን በፊት የተሰጡ ፈተናዎችን ያሠሯቸዋል፣ በቴክኖሎጂ ብቁ እንዲሆኑና በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ እንዲሆኑ ምክክርም ይደረጋል::
ማዕከሉ በሀገሪቱ ከሁሉም አካባቢ በስምንተኛ ክፍል ውጤታቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተወዳድረው መግባት እንደሚችሉ የጠቆሙት ርእሰ መምህሩ፤ በቀጣይም ማዕከሉ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች ከ50 በላይ ለማሳደግ ዕቅድ መኖሩን ጠቁመዋል::
መረጃ
ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዴት ውጤታማ መሆን ይችላሉ ?
- ውጤታማ ተማሪ ለመሆን የጥናት ስልቶችን መከተልና የጥናት ግቦችን ማስቀመጥ፡፡
- ከዚህ በኋላ የጥናት እቅዶች ማዘጋጀት፡፡ በዚህ ውስጥ በተለይም ዛሬ፣ ነገ ጠዋት እና ከስዓት በሚል ጊዜን በመከፋፈል ለእያንዳንዱ የራሱ የትምህርት አይነት የጥናት ጊዜ በመመደብ ወደ ተግባር መግባትን ይጠይቃል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ በኋላ ያልተዘብራረቀ የጥናት ጊዜ መጠቀም ወሳኝነት አለው፡፡ይህ ማለት መደበኛ የጥናት ጊዜ ሊኖር ይገባል፡፡
- ጥናት ከተጀመረ በኋላ በየጊዜው ጥያቄዎችን በማውጣት ራስን መፈተሸ፤ ይህ የጥናት ዘዴ ስህተቶችን በየጊዜው እያረሙ የበለጠ እውቀት ለመጨብጥ ይረዳል፡፡
- ተማሪዎች በቡድን ማንበብ፣መጠያየቅ… እውቀትን ከፍ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዱ ያልገባውን ከሌሎች እንዲረዳ ያደርገዋል፡፡በሌላ በኩል እውቀትንም በማጋራት ሌሎች የተሸለ እውቀት እንዲቀስሙ ያስችላል፡፡
- በጥናት ጊዜ ውስብስብ የሆነን ነገር ወዲያውኑ መምህርን በማማከር መፍትሔ ማግኘት፡፡
እዚህን የጥናት ዘዴዎች በየጊዜው ተግባራዊ ያደረገ ተማሪ በትምህርቱ ውጤታማ ይሆናልል ፡፡
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም