የጸጥታው ምክርቤት ትችቶችን እያስተናገደ መሆኑ ተገለጸ

0
29

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት (UNSC) የድርጅቱ ዋና የቀውስ አስተዳደር አካል እንዲሆን በ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ አስገዳጅ ግዴታዎችን የመጫን ስልጣን ተሰጥቶታል።

ምክር ቤቱ አምስት ቋሚ እና ዐሥር ጊዚያዊ  አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን በየጊዜው በመሰብሰብም የዓለም አቀፍ የደኅንነት ስጋቶችን ማለትም የእርስ በርስ ጦርነትን፣ የተፈጥሮ አደጋዎችን፣ የጦር መሣሪያ መስፋፋትን እና ሽብርተኝነትን ይገመግማሉ።

የጸጥታው ምክር ቤት እ.አ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ኢራቅን፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያን እና ሄይቲን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ማዕቀቦችን በመደበኛነት ሲጠቀም ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜም ዐሥራ አራት የማዕቀብ ሥርዓቶች አሉት።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መሠረት አባላት ኃይልን መጠቀም የሚችሉት እራሳቸውን ለመከላከል ወይም ከጸጥታው ምክር ቤት ፈቃድ ሲያገኙ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የሀገሮች አባላትና ጥምረት ብዙውን ጊዜ ከእነዚህ ሁኔታዎች ውጪ በሆነ አግባብ ወታደራዊ ኃይልን ሲጠቀሙ ይስተዋላል።

ዋና ተግባሩ የዓለም አቀፍ ደኅንነትን ማስጠበቅ የሆነው የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስት ቋሚ አባል ሀገራቱም ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ናቸው። ከእነዚህ ሀገራት መካካል አንዳቸው መላው የምክር ቤቱ አባላት የተስማሙበትን ውሳኔ መቃወም እና መሻር ይችላሉ።

በተመሳሳይ ለሁለት ዓመታት ብቻ የስልጣን ዘመን የሚኖራቸው ዐሥር የጸጥታው ምክር ቤት የተመረጡ አባል ሀገራት አሉ፤ ይሁን እንጂ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ወይም የቬቶ ስልጣን አልተሰጣቸውም።

አምስቱ ሀገራት (ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት) ልዩ መብት ሊያገኙ የቻሉት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ አሜሪካ እና ሶቪየት ሕብረት በጦርነቱ አሸናፊዎች ስለነበሩ የኃይል ሚዛኑ ወደ እነሱ ያጋድል ነበር።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አዲስ ዓለም አቀፍ አካል እንዲቋቋም በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ እና በሶቪየት ሕብረት በኩል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በሌላ በኩል እ.አ.አ ከ1945 በኋላ ቻይና ከእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ኮሚኒስት ሀገር ሆነች፤ እናም የቀድሞው የቻይና መንግሥት ወደ ትንሿ ታይዋን ደሴት አፈገፈገ።

እ.አ.አ እስከ 1971 ድረስ የቻይና ሪፐብሊክ (ታይዋን) በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ነበራት። ሆኖም የጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ ይህንን መቀመጫ ወደ ቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ አስተላልፏል። የጽጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ደግሞ ከ15ቱ አባል ሀገራት የ9ኙን ድምጽ ይጠይቃል።

ይሁንና የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ከምሥረታው ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ድረስ ባለው ዘመኑ ውጤታማነቱ በጣም አከራካሪ ነው፡፡

የምክር ቤቱ ጉዞ እና ውጤቱ

ፖሊቲክስ ቲቺንግ ከተሰኘው ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ቋሚ አምስት አባል ሀገራቱ በያዙት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን እና ጊዜ ያለፈበት  ውክልና በሌለው መዋቅሩ ምክንያት ውድቀቶቹ ይጠቀሳሉ። ምክር ቤቱ አስገዳጅ ውሳኔዎችን የማውጣት ስልጣን ቢኖረውም እነሱን የማስፈፀም አቅሙ በአባል ሀገራቱ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ምክር ቤቱ አስገዳጅ ውሳኔዎችን የማውጣት፣ የሰላም ማስከበር ሥራዎችን የማቋቋም እና ዓለም አቀፋዊ ሰላምን እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ማዕቀቦችን የመጣል ስልጣን ያለው ብቸኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ነው፤ ይሁን እንጂ የአምስት አባላቱን ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅምን በመጠቀም እርምጃዎችን የማገድ ችሎታው ብዙውን ጊዜ ወደ ሽባነት እና ወደ እንቅስቃሴ አልባነት እየመራው ይገኛል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ደግሞ ውጤታማ ስለአለመሆኑ ክርክሮች የሚነሱበት ምክር ቤቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን የሚጠቀሙት አባል ሀገራቱ (ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ) የሚሳተፉበት ወይም የሚደግፉት ሰብዓዊ ቀውሶች የሚያስከትሉ ጦርነቶች ላይ እንኳን እርምጃ ከመውሰድ ሲያግደው ተስተውሏል።

በጎርጎሮሳዊያኑ በ1945 የተመሠረተው የምክር ቤቱ መዋቅር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያለውን የኃይል ለውጥ የሚያንፀባርቅ እና አሁን ያለውን ዓለም አቀፋዊ ሥርዓትን ወይም ታዳጊ ኢኮኖሚዎችን በበቂ ሁኔታ አይወክልም በሚልም ጥያቄዎች እንዲነሱበት ምክንያት ስለመሆኑ ዘገባው አመላክቷል።

አብዛኛውን ጊዜ  ውሳኔዎቹን ለማስፈጸም በአባል ሀገሮች ላይ መተማመኑም  እርምጃ የመስጠት አቅሙን በእነዚህ መንግሥታት የፖለቲካ ፍላጎት የተገደበ አድርጎታል። ምክር ቤቱ የረዥም ጊዜ የጸጥታ ጉዳዮችን በንቃት ከመከላከል ይልቅ ግጭቶች ሲፈጠሩ ብቻ የሚፈታ “የእሳት አደጋ መከላከያ” አካል ነው ተብሎም ይወቅሳል።

የጸጥታው ምክር ቤት እርግጥም ዓለምን የወከለ እና ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ሲጠይቅ ቆይቷል። የምክር ቤቱን ቋሚ አባልነት ማስፋት፣ በተለይም ቋሚ የአፍሪካ ተወካይ እንዲኖር እና ሌሎች የታዳጊ ኢኮኖሚ አባላትን መጨመር እና በቬቶ ሥርዓት ላይ ለውጦችን ማጤን ይገባዋል በሚል በተደጋጋሚ  የሚነሱበት ጥያቄዎች ሆነዋል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ የአባላቱ ተፎካካሪ ፍላጎቶች የጸጥታው ምክር ቤትን እየፈተኑ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የሶሪያ የእርስ በርስ ግጭት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሩሲያ ክሪሚያን መቀላቀል፣ እ.አ.አ የ2022 የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና በ2023 የተጀመረው የእስራኤል-ሃማስ ግጭቶችን ጨምሮ ለዋና ዋና እና ቀውሶች ምላሽ የመስጠት አቅሙ የተፈተኑበት ክስተቶች ናቸው።

እ.አ.አ በ2014 ሩሲያ ክሪሚያን ከቀላቀለች በኋላ በሩሲያ፣ በአሜሪካ እና በአውሮፓ አባላት መካከል ውጥረት ነግሷል፡፡ ይህም የጸጥታው ምክር ቤት ቀውሶችን ማረጋጋት አይችልም የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ሩሲያ የጸጥታው ምክር ቤት ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ ነሐሴ 2025 ድረስ 159 የውሳኔ ሃሳቦችን በማገድ የቬቶ ኃይል (ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት) ተደጋጋሚ ተጠቃሚ ነበረች።

በሄይቲ ሁለት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ ያከናወነው የጸጥታው ምክር ቤት እ.አ.አ በ2011 የተከሰተውን የሶሪያ ግጭት ለመቆጣጠር ግን አስቸጋሪ ሆኖበታል፡፡

ሩሲያ አንዳንዴ ከቻይና ጋር በመወገን ለተመዘገቡት አሰቃቂ ድርጊቶች የበሽር አል አሳድን መንግሥት ተጠያቂ ለማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት (ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸውን) ያቀዱትን ውሳኔዎች ወደ ሃያ ጊዜ የሚጠጋ የቬቶ ስልጣኗን በመጠቀም ተቃውማለች። እ.አ.አ በ 2022 ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ግንኙነቱ የበለጠ ውጥረት ውስጥ ገብቷል፡፡ ሞስኮ የቬቶ ሥልጣኗን ተጠቅማ ግጭቱን የሚያወግዙ በርካታ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች እንዳይጸድቁ አድርጋለች።

ምንም እንኳን በታሪክ ከአሜሪካ ወይም ከሩሲያ የበለጠ ባይሆንም ቻይና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቬቶውን በተደጋጋሚ ተጠቅማለች። ቤጂንግ ሀያ አንድ ውሳኔዎችን አግዳለች፣ እንዲሁም ሞስኮ ቻይና ውድቅ ያደረገችውን ውሳኔ ከሦስት አራተኛ በላይ ደግፋለች። በአንፃሩ ፈረንሳይም ሆነች እንግሊዝ ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር ከ1989 ጀምሮ የቬቶ ሥልጣናቸውን እንዳልተጠቀሙ ነው ያገኘነው መረጃ የሚያትተው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ምዕራፍ ስድስት መሠረት የጸጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፍ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለመ ሲሆን ይህም ወገኖች በድርድር፣ በግልግል ወይም በሌላ ሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲፈልጉ ስልጣን ሰጥቷል። ይህ ካልተሳካ በምዕራፍ ሰባት መሠረት የጸጥታው ምክር ቤት እንደ ማዕቀብ መጣል ወይም ዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ወይም ወደነበረበት ለመመለስ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ መፍቀድ ያሉ የበለጠ አረጋጋጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ ስልጣን ይሰጠዋል።

በሌላ በኩል ውጤታማነታቸው ላይ ጥያቄ ቢኖርም የየአካባቢዎች (የክልል) ድርጅቶች በሰላም ማስከበር እና በግጭት አፈታት ውስጥ ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለአብነትም ኢጋድ፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የአረብ ሊግ ይጠቀሳሉ፤ አንዳንድ ጊዜም የጸጥታው ምክር ቤት ወደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ እና ሌሎችን በመወከል እንደ ንኡስ ሕግ አስፈጻሚ ሆነው ያገለግላሉ።  የአፍሪካ ሕብረት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር በሶማሊያ እና በሱዳን የዳርፉር ክልል ተልዕኮዎችን ሲያከናውን የነበረውን ፍላጎት እና አቅም ማደጉንም ባለሙያዎች ያብራራሉ።

እንደ ዕድሜው ውጤታማ አይደለም ከሚለው ባለፈ የታዳጊው ዓለም አባል ሀገራትን ጨምሮ ብዙ ተቺዎች የጸጥታው ምክር ቤት መዋቅር ወቅታዊውን የጂኦፖለቲካዊ እውነታዎችን አያሳይም ሲሉም ይከራከራሉ።

እንደ ብራዚል፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ፈርጣማ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት የጸጥታው ምክር ቤትን ለማስፋት ወይም የራሳቸው ቋሚ መቀመጫዎች ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በባልካን ሀገሮችም አሳፋሪ ሽንፈትን አስተናግዷል። ሰላም አስከባሪ ኃይሎቹ የስሬብሬኒካ አካባቢ ሰላማዊ ዜጎችን ከእልቂት መከላከል አልቻሉም። በሩዋንዳ ተካሂዶ በነበረው የዘር ጭፍጨፋም ተወቃሽ ነው። ሆኖም ከነጉድለቶቹ ቢሆንም በቀውስ ውስጥ መፍትሔ አፈላላጊ እና የውይይት ዋና መድረክ ሆኖ ቀጥሏል።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከድርጅቱ ድረ ገጽ (www.un.org) ተጠቅመናል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here