ዕቅዱ ድህነትን  ለማስወገድ እና  ሰላምን ለማብሰር ያለመ ነው

0
30

መግቢያ

ተደጋጋሚ ግጭቶች እየፈጠሩት ካለው መጠነ ሰፊ ጉዳት እና ሥር ከሰደደ ድህነት ለመውጣት የአማራ ክልል የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድን አቅዷል:: የግጭት አዙሪት እና ድኅነት የክልሉ ችግሮች ሆነው በዕቅዱ መለየታቸውን ያስታወቁት የክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊው ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) ናቸው:: የዕቅዱ የመጨረሻ ግብም ዛሬ የዓለም ሀገራት ከደረሱበት ብልጽግና ማድረስ፣ በቴክኖሎጅ ተወዳዳሪ መሆን፣ ደስተኛ ኅብረተሰብን መፍጠር እንደሆነ አስታውቀዋል::

በዕቅዱ የ30 ዓመታት ዳታዎች በምሁራን እና ከፍተኛ ሙያተኞች ተተንትኖ መቅረቡን ያስታወሱት ቢሮ ኅላፊው፣ ይህም ክልሉ ያለውን ጸጋ መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል:: በዕቅዱ ክልሉ በስድስት የልማት ቀጣና መከፈሉንም ዶክተር ደመቀ ተናግረዋል:: እነዚህም የጣና የልማት ኮሪደር፣ የደቡብ ምዕራብ አማራ፣ የሰሜን ምዕራብ፣ የተከዜ ኮሪደር፣ የማዕከላዊ አማራ እና የምሥራቅ አማራ ናቸው::

ካለፉት ዘመናት በምን ይለያል?

የ25 ዓመቱ ዕቅድ ከባለፉት ዓመታት ዕቅዶች ምን ይለየዋል የሚሉ ድምጾች የተስተጋቡበት ነው:: ዶ/ር ደመቀ ግን ዕቅዱ ባለፉት ዘመናት ከነበሩ የአጭር እና የመካከለኛ ዘመን ዕቅዶች የሚለይበትን አግባብ አስረድተዋል::

ዕቅዱ ከ2018 ዓ.ም እስከ 2042 ዓ.ም ከሚኖረው የጊዜ ቆይታ አንጻር ከአጭር እስከ ረጅም ዘመን የዕቅድ ዓይነቶችን መሸፈኑ አንዱ መለያ ባህሪው አድርገዋል::

መሪዎች፣ ምሁራን እና ከፍተኛ ሙያተኞች ተባብረው እንዲሠሩ ታሳቢ ተደርጎ መቀረጹ ሁለተኛው ባህሪው ነው:: መሪዎች የዕቅዱ ባለቤቶች ሆነው ይሠራሉ፤ ዕቅዱ የንድፈ ሐሳብ እና የተለያዩ ሞዴሎች ችግር እንዳይገጥመው፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችንም የተረዳ እንዲሆን  የምሁራን ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ እንዲካተቱ  መደረጉን ገልጸዋል::

ልምድ ያላቸው ከፍተኛ ሙያተኞች እንዲካተቱ የተደረገው ደግሞ ዕቅዱ በፖሊሲ እና በስትራቴጂ ምክንያት የተግባራዊነት ችግር እንዳይገጥመው ታሳቢ ተደርጎ ነው::

በቀደሙት ጊዜያት የነበሩት የአጭር እና የመካከለኛ ዘመን ዕቅዶች ጥቅል የኢኮኖሚ ማዕቀፍን በመያዝ ወደ ሴክተር የሚወርዱ ነበሩ:: የአሁኑ ዕቅድ ግን ከጥቅል የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ተነስቶ እስከ ፕሮጀክት ድረስ የተናበበ ትስስር እንዲኖረው ተደርጎ ተቀርጿል::

በጥቅል ኢኮኖሚ ክልሉ ከየት ተነስቶ የት መድረስ እንዳለበት ትንበያ ያስቀመጠ ዕቅድ እንደሆነ ገልጸዋል:: ይህም ትንበያ ግቡን እንዲያሳካ ዕቅዱ ወደ ዘርፍ መበተኑን አስታውቀዋል:: ብዝኃ ዘርፍ የሆነው የ25 ዓመቱ ዕቅድ ወደ ዘርፍ ሲቀየር በእያንዳንዱ ዘርፍ የት መድረስ እንዳለበት የተመላከተም ነው:: ዕቅዱ በዘርፍ ብቻ ተወስኖ አልቀረም:: ወደ ተቋማት ዕቅድ፣ ፕሮግራም እና ፕሮጀክት ድረስ መውረዱ ዕቅዱ ወደ ግብ እንዲደርስ የሚያደርግ ነው:: ይህ ደግሞ ሕዝቡ የሚያነሳቸው የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዘላቂነት ምላሽ እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥ ነው::

የዕቅዱ የትኩረት መስኮች

የክልሉን ሰላም እና የህግ የበላይነት ማረጋገጥ የዕቅዱ ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ ተመላክቷል:: የክልሉ ሰላም ካልተረጋገጠ ልማት የለም ያሉት ዶ/ር ደመቀ፣ ለዚህም መሳካት የሚያስፈልጉ ግቦች እና ተግባራት በዕቅዱ ላይ መመላከታቸውን አስታውቀዋል::

የተሸረሸረውን ባህል እና እሴት ማረም ሁለተኛው የዕቅዱ ትኩረት ነው:: ይህም የሆነው በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና ራሱ ሕዝቡ ትኩረት ባለመስጠቱ ነው::

ሳይንሳዊ ዕውቀት የተላበሰ ማኅበረሰብ መፍጠር ሌላው የዕቅዱ ትኩረት ነው:: የአሁኑ ትውልድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጥ ዕውቀት ባለቤት እና ተፈላጊ መሆን አለበት:: በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ አምራች እና ተወዳዳሪ ለመሆን የዓለምን ዕውቀት መሸመት ያስፈልጋል:: ለዚህም ለዕውቀት እና ለምርምር ቦታ የሰጠ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ዕቅዱ ቦታ ሰጥቷል::

ምርታማነትን በሁሉም ዘርፍ ማሳደግ የዕቅዱ አራተኛው የትኩረት መስክ ነው:: ሰላማዊ እና ሕጋዊነት ከተረጋገጠ፣ ባህሉን አውቆ ለባህሉ ዘብ የሆነ ማኅበረሰብ ከተገነባ፣ ስነ ምግባርን የተላበሰ ትውልድ ከተፈጠረ እና በሳይንሳዊ ዕውቀት ራሱን የገነባ ትውልድ ከተፈጠረ የማምረት አቅምን ማሳደግ ይቻላል:: ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲመረት አቅም ይሆናል:: በሰው ኅይል ቁጥር፣ በሰው ኅይል ስምሪት፣ በመሬት ማስፋት፣  ምርታማነትን በሄክታር ከፍ ማድረግ፣ አዳዲስ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል::

ዕቅዱ የየአካባቢውን እምቅ ሀብት መሠረት ያደረገ የሰው ኅይል ስምሪት እንዲኖር ምርታማነትን ለማሳደግ ሌላው መፍትሔ ነው:: የተቋማትን የመፈጸም እና የማስፈጸም  አቅም ማጠናከር የዕቅዱ መዳረሻ አሳሪ ትኩረት ሆኖ ተመላክቷል::

ዕቅዱ ከክልሉ ጸጋዎች መካከል አንዱ በሆነው ቱሪዝም ላይ ትኩረቱን ያደርጋል:: የ25 ዓመቱ ዕቅድ ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ጸጋ በመጠበቅ እና በማደስ ለዓለም የቱሪዝም ገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ አዳዲስ መዳረሻዎች እንዲፈጠሩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ  አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ገልጸዋል:: የጣና ኃይቅን እና የሾንኬ መንደርን በዓለም የቅርስ መዝገብ ለማስመዝገብ እየተሠራ ያለውን ሥራ አብነት አንስተዋል::

ዕቅዱ የት አካባቢ ምን አይነት የቱሪዝም መዳረሻ ማልማት ይገባል? የሚለውን የመለሰ እንደሆነ አስታውቀዋል:: የዘመኑ አዳዲስ የቱሪዝም ፍላጎቶችም የተለዩበት ነው:: የተራራ እና የውኃ ላይ ቱሪዝም፤ ታሪካዊ  ትስስር ያላቸው ሁነቶች በተለይም እንደ ጉዞ አድዋ ያሉ አይነት ሁነቶችን እንዲሠሩ ዕቅዱ ትኩረት መስጠቱንም ገልጸዋል::

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ በ25 ዓመት አሻጋሪ የዕድገት እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 85 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ጠቅሰዋል:: ዕቅዱ የሚሳካውም በአጋር አካላት ትብብር እና ቅንጅት መሆኑን ቢሮው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ባደረገበት ወቅት አስታውቀዋል:: ለአምራች ኢንዱስትሪው የተሰጠው ትኩረት ግቡን እንዲመታ ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት::

ከሀገራት ተሞክሮ…

ኢትዮጵያ ለማደግ ከሁሉም ያደጉ ሀገራት የመማር ዕድል አላት:: የሁሉም ሀገር የእድገት መነሻው ተፈጥሮ ሀብት (መሬት፣ ውኃ…) ነው::  ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ማኅበራዊ ካፒታል ላይ ትኩረት አድርገው የሰሩ ሀገራት ዕድገታቸውን እንዳረጋገጡ ዶ/ር ደመቀ ገልጸዋል::

ያደጉ ሀገራት አሁን የደረሱበት ዕድገት ደረጃ እንዳለውም ዶ/ር ደመቀ ያስረዳሉ:: ተፈጥሮ ሀብታቸውን ተጠቅመው ቁሳዊ ሀብታቸውን ያለሙበትን መንገድ ቀዳሚው ደረጃ አድርገዋል:: ቁሳዊ ሐብትን ለሰብዓዊ ሀብት ልማት፤ በለማው የሰው ኀይል ዕውቀትም ቴክኖሎጂን ማልማታቸውን ጠቁመዋል:: የተፈጠረው እና የለማው ቴክኖሎጂም  የማምረት አቅም ከፍ በማድረግ የመጨረሻው የዕድገት ደረጃ የሆነውን ማኅበራዊ ካፒታል እንዲያረጋግጡ እንዳደረገ አንስተዋል::

የአማራ ክልልም ለዕድገቱ መነሻ የሚሆነው የተፈጥሮ ሀብቱ ነው:: ለአብነት ክልሉ ሀገሪቱ ካላት አጠቃላይ የውኃ ሀብት ውስጥ 60 በመቶ ድርሻ አለው:: በመሬትም ሰፊ ሀብት ያለው ክልል መሆኑን ዶ/ር ደመቀ ያነሱት ወደ ፊት አሁን ከሚታረሰው አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ወደ ሰባት ሚሊዮን ሊደርስ የሚችል የሚታረስ መሬት እንዳለው አስታውቀዋል:: በሰው ኀይልም እምቅ አቅም መኖሩ ሌላው ክልሉ ከ25 ዓመት በኋላ ላስቀመጠው ግብ እንደ መስፈንጠሪያ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል:: ዕቅዱ ታሪክን እና ባህልንም እንደ መነሻ ይወስዳል:: የጀግንነት ታሪክን ወደ ልማት ማዞር ደግሞ ለክልሉ ብልጽግና ዋልታ ሆኖ ይሠራበታል ነው ያሉት::

ክልሉ ያለውን ሀብት ተጠቅሞ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋት፣ መሠረተ ልማትን መዘርጋት፤ የሰለጠነ፣ ሳይንሳዊ ዕውቀትን የታጠቀ፣ ጤናማ እና ስነ ምግባር ያለው ዜጋ ማፍራት ላይ በትኩረት መሥራት ለግቡ ስኬት ቀድሞ የሚሠራባቸው ሥራዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል::

ጸጋን የመጠቀም ፈተናዎች

ዶ/ር ደመቀ ጥናቶችን መሠረት አድርገው እንደገለጹት አንድ ሀገር ያለውን ሀብት (ጸጋ) በአግባቡ ካልተጠቀመ ለከፋ ድህነት ይዳርጋል። ከመንግሥት አሥተዳደር ችግር እና ከባህል ጋር የተገናኙ ነገሮችም ለድህነት የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ነው የገለጹት። ባህል ለድኅነት በተለዬ ሁኔታ ተጽእኖ እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ደመቀ፣ የሥራ ባህል ካልተቀየረ የሥራ ዕድል ፈጠራ አይሰፋም፣ ምርታማነት አያድግም። ይህም በሁለንተናዊ ዘርፍ ከተወዳዳሪነት ውጪ ያደርጋል።

አንድ ሀገር ያለውን ጸጋ በአግባቡ እንዳይጠቀም ትልቁ ፈተና መልካም የመንግሥት አስተዳደር አለመኖር ነው ብለው ያነሳሉ። አስተዳደር ካልተሻሻለ የሰብዓዊ ሀብትን በአግባቡ መምራት አይቻልም። ባለፉት ዘመናት እርስበእርስ እየተመጋገቡ የመጡት ድህነትና ግጭት በተመሳሳይ ሰዓት ለመስበር የመንግሥት አስተዳደር ዋናው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል። ለዚህም እስከ ታች የወረደው ዕቅድ እንዲተገበር የሚያደርጉ ስትራቴጂ እና ፖሊሲዎችን መቅረጽ ዋናው ጉዳይ እንደሚሆን ገልጸዋል። በመሆኑም ዘርፈ ብዙ የሆነውን ድኅነት ለመቅረፍ የመንግሥት አስተዳደርን ማዘመን ዋናው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለተጠባቂዉ ውጤት…

በዓለም ላይ ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው 20 ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያን አንዷ ማድረግ የ2040 ዓ.ም ግብ ነው:: ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥም ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሁለት ሀገራት መካከል አንዷ ትሆናለች ተብሎ እየተሠራ ነው:: ይህም ቀድሞ ወደነበረው የአክሱም ዘመነ መንግሥት ስልጣኔ እና የተወዳዳሪነት ዘመን የሚመልሳት ይሆናል ተብሎ ይታመናል::

የክልሉ የ25 ዓመት ዕቅድም ክልሉን በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ማድረግ፣ ደስተኛ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው:: ለዚህም ቁጭት አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት:: ሁሌም ድኅነት እና ግጭት እየተመጋገቡ እንዲቀጥሉ ከመፍቀድ ይልቅ መውጫ መንገዶቹን እያሰቡ በቁጭት መሥራት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ነው ያስታወሱት:: “አንድ ሰው ሲቆጭ እንደ ሺህ ይሠራል” የሚሉት ዶ/ር ደመቀ፣ “ዕቅዱ የሕዝብ ነው፤ የሚፈጽመው እና ተጠቃሚ የሚያደርገው ሕዝብን ነው፤ በመሆኑም ዓድዋን እና ሕዳሴን በአንድነት እንዳሳካነው ሁሉ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸ ሀገር ለመፍጠር አላማ ላደረገው ዕቅድ መሳካት በቁጭት እና በወኔ መሥራት ይገባል” ብለዋል::

የተሰጣቸውን ግብ የሚያሳኩ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት በ2040 ዓ.ም ለመድረስ ለታቀደው ብልጽግና ሌላው መሠረት መሆኑን ዶ/ር ደመቀ ገልጸዋል::

ዓለም ተቀያያሪ ስለሆነ ተለዋዋጭ ስትራቴጂ እና ፖሊሲ እያወጡ መተግበርንም ለመዳረሻው ግብ መፍትሄ ሆኖ መቀመጡን አረጋግጠዋል:: ኅብረተሰቡም የአሠራር ባህሉን ማሻሻል እንዳለበት ጠቁመዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here