ስዊዘርላንድ

0
16

ሀገሪቷ በከፍተኛ የኑሮ ደረጃዋ፣ በቀልጣፋ የህዝብ አገልግሎቶቿ፣ በጠንካራ የጤና አጠባበቅ ስርዓት እና በተረጋጋ ኢኮኖሚዋ በብዙዎች የምትወደድ  ናት። በቸኮሌት እና አይብ ምርቷ እንዲሁም በእጅ ሰዓት ኢንዱስትሪዎቿ እና ባሏት ልዩ ባሕሎቿ ታዋቂም ናት-፡ ስዊዘርላንድ:: ስዊዘርላንድ ከዓለም ሃብታም ሀገራት ተርታ የምትመደብ እና ህዝቦቿም ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ናቸው::

የስዊዘርላንድ ነዋሪዎች በርካታ ገንዘብን ለተለያዩ ነገሮች የሚያወጡ ቢሆንም የሚሰሩት ግን ለውስን ሰዓታት ነው:: አብዛኛው ሰውም በሳምንት ሦስት ቀን ብቻ ነው ሥራ የሚገባው:: በስዊዘርላንድ ከመዋለ ህጻናት እስከ ኮሌጅ ትምህርት በነጻ የሚሰጥ ሲሆን፤ የሁሉም ዜጋ የህክምና ወጪ በመንግስት ይሸፈናል:: ስዊዞች ገንዘብ መቆጠብን አያስቡም ከዛ ይልቅ ሕይወትን ተዝናንተው ማሳለፍ ይመርጣሉ::

በሀገሪቱ የሚገኙ ባንኮችም በአብዛኛው አገልግሎት የሚሰጡት ለውጪ ዜጎች ነው:: በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ በዚች ሀገር ህጋዊ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው ቢሠራም ባይሠራም በወር ሁለት ሺህ 200 ዶላር ያገኛል:: ሆኖም አንድ አንድ ሰዎች ያንን ገንዘብ ለመቀበል ፈቃደኛ ሲሆኑ አይታይም::

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2016 መንግስት ለሕዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍ መቀበል ግዴታ ነው የሚል ህግ ቢያወጣም 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ግን የመንግሥትን ድጋፍ አንፈልግም ሲል የተቋውሞ ሰልፍ ወጥቷል::

የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በ2019 በተጠና ጥናት በስዊዘርላንድ አማካይ በሕይወት የመኖር ጣርያ 83 ዓመት ሲሆን ይህም ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ሲነጻፀር በአማካይ የአምስት ዓመት ብልጫ ያሳያል:: ሰዎች ረጅም ዕድሜ እንዲኖራቸው የሀገሪቱ ንጹሕ መሆን እና ዝቅተኛ የወንጀል መጠን መኖሩ በዋናነት ይነሳል::

ስዊዘርላንድ ስትባል በአዕምሯችን የሚመጣው ውብ መልክዓ ምድር፣ ሰላም የሰፈነበት ገጽታ እና ግርማ ሞገስ የተላበሱ የአልፕስ ተራሮች ናቸው። የስዊዘርላንድ ውብ ተራሮች ከሚታየው ገጽታቸው በስተጀርባ ጥልቅ ምስጢር ይዘዋል፤ ይኸውም በሆዳቸው ተፈልፍለው የተሰሩት ግዙፍ ወታደራዊ ምሽጎች ናቸው። እነዚህ ምሽጎች የተገነቡት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ስዊዘርላንድ ገለልተኝነቷን ለመጠበቅ የተከተለችው “ብሔራዊ ምሽግ” (National Redoubt) የተባለ የመከላከያ ስልት አካል ናቸው። ዋናው እቅድ ሀገሪቱ ጥቃት ቢሰነዘርባት ሙሉ የስዊዘርላንድ ሕዝብ ወደ አልፕስ ተራሮች በመግባት በተፈጥሮ ከለላ እና በሰው ሰራሽ ምሽጎች ታግዞ ወራሪን መከላከል ነው። የእነዚህ ምሽጎች አለኝታነት የተሟላ እንዲሆን፣ ለወራት እና ለዓመታት የሚያስችል ምግብ ተከማችቶበታል። እንደ ጦር ሰራዊት ብስኩቶች፣ ቸኮሌት፣ የታሸጉ ምግቦች እና ደረቅ ስንቆች ያሉ ለህልውና አስፈላጊ የሆኑ ምግቦች በብዛት ይገኙ ነበር። ይህ የምግብ ክምችት የስዊዘርላንድን የዝግጁነት እና ራስን የመቻል መንፈስ ያሳያል።

በአጭሩ የተራሮቹ ጥንካሬ፣ በውስጣቸው ከተገነቡት ምሽጎች እና ለህልውና ከተከማቸው ምግብ ጋር ተዳምሮ የስዊዘርላንድን የማይበገር አለኝታነት እና የጸና ማንነት ይገልጻል። ተራሮቹ ውብ ብቻ ሳይሆኑ የሀገሪቱ ዝምተኛ ጠባቂዎች ናቸው ሲል ተጓዡ የማኅበራዊ መገናኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ አቤል ብርሃኑ ስዊዘርላንድን ይገልጻታል።

ስዊዘርላንድ ግዙፍ ተራሮች፣ አስገራሚ ሐይቆች እና ውብ መንደሮችን ጨምሮ በሚያስደንቅ የተፈጥሮ ውበቷ ትታወቃለች። ስዊዘርላንድ በዓለም ላይ ልዩ የሆነ የሲቪል መከላከያ ዝግጅት ያላት ሀገር ነች። ለሁሉም ሕዝቦቿ የሚበቃ የኒኩሌር ጥቃት መጠለያ ስፍራ ያላት ብቸኛ ሀገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን ከጠቅላላ የሕዝብ ብዛቷ 100 በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን ከጥቃት መከላከል ትችላለች። ይህ ሊሆን የቻለው እያንዳንዱ የስዊስ ዜጋ የመጠለያ መብት እንዳለው በሚደነግገው ሕጋቸው ምክንያት ነው። በዚህም መሠረት ሁሉም አዲስ የመኖሪያ ህንጻዎች መጠለያ መገንባት አለባቸው፤ ወይም የግንባታ ወጪያቸውን ይጋራሉ። ይህ ሕግ ስዊዘርላንድን በዓለም ላይ እጅግ በጣም ዝግጁ ከሆኑ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል። መጠለያዎቹ ለኑክሌር ጥቃት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችም ጭምር የሚያገለግሉ ናቸው።

የስዊዘርላንድ አዲስ ገጸ-በረከት “ሶላርስትራቶስ” የተባለ የፀሐይ ኃይል አውሮፕላን ከ31,000 ጫማ በላይ በመብረር የዓለም ክብረወሰን አስመዝግቧል። ይህ አውሮፕላን፣ ምንም አይነት የአካባቢ ብክለት ሳያስከትል በፀሐይ ኃይል ብቻ በመብረር ለወደፊት ዘላቂ አቪዬሽን ትልቅ ተስፋን አስቀምጧል። ይህ ስኬት ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆኑ በረራዎች እውን መሆን እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው ሲል ፍራንስ 24 ዘግቧል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሚሊኒየሮች ካሏቸው ሀገራት አንዷ ስዊዘርላንድ ናት። ስዊዘርላንድ በምጣኔ ሀብቷ እና ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ዜጎች ሀገር በመሆን ትታወቃለች፤ ለዚህ እንደማሳያ የሚቀርበው ከ18ሺ የስዊዘርላንድ ዜጎች አንዱ አዲስ የሆነ የፌራሪ (ቅንጡ መኪና)  ባለቤት መሆኑ ነው። ይህም ሀገሪቱ ያላትን የኢኮኖሚ ከፍታ ከማሳየት አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አብዛኞቹ ዜጎቿ ቅንጡ ምርቶች የማግኘት አቅምን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

ስዊዘርላንድ ከ1815 ጀምሮ የገለልተኝነት ፖሊሲን ስትከተል የቆየች ሲሆን፣ በውጪ ጦርነቶች እና ግጭቶች ውስጥ ከመሳተፍ ተቆጥባ እየኖረች ነው። ሀገሪቱ የባሕላዊ ብዝሃነቷን የሚያንጸባርቁ አራት ይፋዊ ቋንቋዎች አሏት፤ እነሱም ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛ እና ሮማንሽ ናቸው። ስዊዘርላንድ ዜጎች በተደጋጋሚ በሚደረጉ የሕዝብ ውሳኔዎች አማካኝነት በሕጎች እና ፖሊሲዎች ላይ ድምጽ እንዲሰጡ የሚያስችል የቀጥታ ዴሞክራሲ ስርዓት ትተገብራለች።

ከ60 በመቶ በላይ የስዊዘርላንድ መሬት በአልፕስ ተራሮች የተሸፈነ ሲሆን፣ ይህም ለበረዶ ላይ መንሸራተት ለተራራ መውጣት እና ለቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል። ስዊዘርላንድ በዓለም አቀፍ የኑሮ ጥራት መመዘኛዎች ውስጥ በተደጋጋሚ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ እንደ ዙሪክ እና ጄኔቫ ያሉ ከተሞቿ ብዙውን ጊዜ በዝርዝሩ አናት ላይ ይቀመጣሉ።

ሀገሪቱ በግል የባንክ ዘርፏ የምትታወቅ ሲሆን ጥብቅ የምስጢራዊነት ሕጎቿ ከታሪክ አኳያ የዓለምን ሀብት ስበዋል። ስዊዘርላንድ እንደ ኔስሌ (ምግብ እና መጠጥ አምራች ኩባንያ) እና ሮሌክስ (የሰዓት አምራች ኩባንያ) ያሉ ኩባንያዎች እንዲሁም ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎችን እና የምርምር ተቋማትን በማስተናገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈጠራ መሪ ሀገር ነች። ስዊዘርላንድ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቸኮሌት (ለምሳሌ ሊንት) እና የቅንጦት ሰዓቶችን (ለምሳሌ ፓቴክ ፊሊፕ፣ ኦሜጋ) በማምረት ትታወቃለች።

ዋና ከተማዋ በርን፣ እንደ ዙሪክ ወይም ጄኔቫ ካሉ ሌሎች ከተሞች ጋር ሲነጻጸር በአንጻራዊነት ትንሽና ዝቅተኛ የበላይነት ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያላት ናት። ስዊዘርላንዳውያን ወንዶች ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ሀገሪቱ በዜጎች ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የመከላከያ ስርዓት አላት።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) በ1863 በሄነሪ ዱናንት እና ጓደኞቹ በጄኔቫ የተመሠረተ ሲሆን ስዊዘርላንድ የጄኔቫ ስምምነቶች አደራ ተቀባይ (ባለአደራ) ሀገር ነች። ስዊዘርላንድ በጄኔቫ አቅራቢያ የሚገኘውን እና በዓለማችን ካሉ ግዙፍ እና የተከበሩ የሳይንሳዊ ምርምር ማዕከላት አንዱ የሆነውን ሰርን (የአውሮፓ የኑክሌር ምርምር ድርጅት) ይዛለች። ስዊዘርላንድ ከአልፕስ ተራሮቿ ባሻገር እንደ ጄኔቫ ሐይቅ፣ ሉሰርን ሐይቅ እና ዙሪክ ሐይቅ ባሉ በርካታ ንጹህና ውብ ሐይቆቿ ትታወቃለች፤ እነዚህም ለመዝናኛና ለዕይታ ተወዳጅ ናቸው።

ቀልጣፋ እና የተሳለጠ የሕዝብ ማመላለሻ ሀገሪቱ አሏት:: ስዊዘርላንድ ባቡሮችን፣ አውቶቡሶችን እና ጀልባዎችን በማቀናጀት እና በማስተሳሰር በዓለም ላይ ካሉ እጅግ በጣም ጥንቅቅ ያሉ ሰዓት አክባሪ እና ከፍተኛ ብቃት ያላቸው የሕዝብ ማመላለሻ  መረቦች ገንብታለች።

ስዊዘርላንድ  እስከ 40 በመቶ የሚደርሰውን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ አራት የኒውክሌር ኃይል ማብላያዎች እንዳሏት የዓለም ኒውክሌር ማህበር አስታውቋል። ስዊዘርላንድ በፈረንጆቹ 2017 የኒውክሌር ኃይልን ለማስወገድ ወስና የነበረ ቢሆንም ጣቢያውን ለመዝጋት ግን ቀነ-ገደብ አለማስቀመጧን አር ቲ አስነብቧል። ይሁን እንጅ ማመንጫ ጣቢያዎቹ ደህንነታቸው የተጠበቀ እስከሆነ ድረስ በስራ ላይ እንዲቆዩ ወስናለች ነው የተባለው።

ጎብኝዎች ወደ ስዊዘርላንድ የተለያዩ መልክዓ ምድሮችን እንዲሁም የተለያዩ መሳጭ ሁነቶች ላይ ለመሳተፍ ያቀናሉ:: ይህም የአልፕስ የአየር ንብረት እና የመሬት አቀማመጥ፣ በተለይም የበረዶ መንሸራተቻ እና ተራራ መውጣትን የመሳሰሉ የጀብዱ ተግባራት ላይ ይሳተፋሉ:: ጥንታዊ ስነ ሕንጻዎች፣ ሃውልቶች፣ የባቡር ሀዲዶች እና ሌሎች መልካም ገጽታዎች ጎብኝዎችን ቀልብ ይስባሉ:: ስዊዘርላንድ በፈረንጆቹ 2024 ከቱሪዝም ዘርፍ 20 ቢሊዮን ዶላር  ማግኘቷን የሀገሪቷ የስታትስቲክስ ቢሮ አስታውቋል::

አጭር እውነታ

ስዊዘርላንድ

  • ስዊዘርላንድ በከፍተኛ የኑሮ ደረጃዋ፣ በቀልጣፋ የህዝብ አገልግሎቶቿ፣ በጠንካራ የጤና አጠባበቅ ስርዓት እና በተረጋጋ ኢኮኖሚዋ በብዙዎች የምትወደድ ሀገር ናት።
  • በቸኮሌት እና አይብ ምርቷ እንዲሁም በእጅ ሰዓት ኢንዱስትሪዎቿ እና ባሏት ልዩ ባሕሎቿ ታዋቂም ናት::
  • አብዛኛው ሰው በሳምንት ሦስት ቀን ብቻ ነው ሥራ የሚገባው::
  • ሰው ቢሠራም ባይሠራም በወር ሁለት ሺህ 200 ዶላር ያገኛል::
  • በሕይወት የመኖር ጣሪያ 83 ዓመት ሲሆን ይህም ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋር ሲነጻጻር በአማካይ የአምስት ዓመት ብልጫን ያሳያል::
  • ስዊዘርላንድ ግዙፍ ተራሮች፣ አስገራሚ ሐይቆች እና ውብ መንደሮችን ጨምሮ በሚያስደንቅ የተፈጥሮ ውበቷ ትታወቃለች።
  • በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሚሊኒየሮች ካሏቸው ሀገራት አንዷ ስዊዘርላንድ ናት።
  • ከ60 በመቶ በላይ የስዊዘርላንድ መሬት በአልፕስ ተራሮች የተሸፈነ ነው::

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here