ዕቅድ አንድን የልማት ሥራ በተወሰነ ጊዜ ለማከናወን በቅድሚያ የሚዘጋጅ፣ የመነሻ ነጥብን፣ የማስፈፀሚያ ስልቱንና የመድረሻ ውጤቱን የሚያመላክት፣ የተወሰነ ዓላማን ለማሳካት የሚያስፈልግ ሀብትን የምንወስንበት፣ የተግባራትን ቅደም ተከተል የምናስቀምጥበት የተቀናጀ ስልት ነው።
በተለያዩ ሃገራት እና ተቋማት ዉስጥ እንዲሁም በሕብረተሠብ ሁሉን አቀፍ ችግር ላይ ተመሥርቶ የሕብረተሠቡን ፍላጎት ለማሟላት ጥናቶችና የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማዎች ይካሄዳሉ። ከጥናቶች እና ግምገማዎች በኋላም ለችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ ግኝቶች ይኖራሉ። ይህን ውጤት መሠረት በማድረግም ዕቅዶች ይዘጋጃሉ።
በዚህ መነሻ አማካኝነትም የአማራ ክልል መንግሥት በቅርቡ የክልሉን የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ አቅዳል። ወደ ተግባርም ተገብቷል፤ የግጭት አዙሪት እና ድሕነት የክልሉ ሁነኛ ችግሮች መሆናቸውንም እቅዱ ለይቷል።
በመሆኑም ይህንን የግጭት አዙሪት እና ድህነትን በፍጥነት ከክልሉ ለማስወገድ እና የክልሉ ነዋሪ ዓለም ሀገራት ከደረሱበት ዕድገት ለማድረስ፣ ደስተኛና በቴክኖሎጅ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ነው።
እቅዱ በመነሻነት የተጠቀመውም የአካባቢወችን እምቅ ሐብት፣ የክልሉን ፀጋወች፣ የተፈጥሮ ሐብቶች፣ የውኃ ሐብት፣ ሠፊ የሚታረስ መሬት እና የቱሪዝም መዳረሻወችን ነው፡፡
ዕቅዱ እንደየአካባቢወቻቸዉ ጸጋ ክልሉን በስድስት የልማት ቀጣናዎች ከፍሎታል። የክልሉን ሰላም እና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ የዕቅዱ ቀዳሚ ትኩረት ሆኖም ተለይቷል። የየአካባቢዉን እምቅ ሃብት መሰረት ያደረገ የሰዉ ሃይል ስምሪት እንዲኖር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደ መፍትሔ ተወስዳል።
ዕቅዱ በፍጥነት ወደ መሬት ወርዶ በተግባር ይተረጎም ዘንድ የክልሉ ሰላም መሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ቁልፍ ተግባር ነው። ከሰላሙ ባሻገርም የተሸረሸረውን ባሕል እና እሴታችንን ወደነበረበት መመለስ፣ ሳይንሳዊ ዕውቀት የተላበሰ ማሕበረሰብ መፍጠር እና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ የእቅዱ ዋነኛ የትኩረት መስኮች መሆናቸው ተመላክቷል።
የክልሉ የ25 ዓመቱ ዕቅድ እንደ ዋና አላማ ያስቀመጠውም ክልሉን በኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጅ ተወዳዳሪ ማድረግ እና ደስተኛ ማሕበረሰብ መፍጠር ሲሆን ለዚሕም ቁጭት ያስፈልጋል፤ የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ ሐላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) ሁሌም ድሕነት እና ግጭት እየተመጋገቡ እንዲቀጥሉ ከመፍቀድ ይልቅ መውጫ መንገዱን እያሠቡ በቁጭት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዕቅዱ ቀደም ሲል ከነበሩት ከሚለይባቸዉ በርካታ ምክንያቶች መካከልም በአሁኑ እቅድ ላይ በርካታ ከፍተኛ ልምድ ያላቸዉ ሙያተኞች፣ ምሁራን እና መሪዎች የተሳተፉበት መሆኑ እንዲሁም የዕቅዱ ቆይታ ጊዜ የረጅም ዘመን መሆኑ ተጠቃሽ ነው፤ ለስኬታማነቱም የአጋር አካላትን ትብብር እና መናበብ ይፈልጋል። ወደየዘርፎች በመቀየርም እንዳንዱ ዘርፍ የት መድረስ እንዳለበት ያመላከተ ነው፤ ወደ ግብ እንዲደርስ አስቻይ ሁኔታወዎችን የተላበሰ መሆኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዘላቂነት ምላሽ እንዲያገኙ ዕድል ሰጪ በመሆኑ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እቅድ ነው።
ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸ ሀገር ለመፍጠር ዓላማ ላደረገው ዕቅድ መሣካትም ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል። የሚተገበረውም ሆነ የሚጠቀመው ሕዝቡ በመሆኑ ለዕቅዱ መሣካት ክልሉ ያለውን ሃብት ተጠቅሞ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት፣ መሠረተ ልማትን በመዘርጋት፣ የሰለጠነ፣ ሳይንሳዊ ዕውቀትን የታጠቀ ጤናማ እና በስነ ምግባር የታነፀ ዜጋን ማፍራት ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ለከፋ ድህነት ያጋልጣል፤ ከመንግሥት አስተዳደር ችግር እና ከባሕል ጋር የተገናኙ ነገሮችም ለድህነት የየራሳቸዉ አስተዋጽኦ ስላላቸዉ ተለይተዉ መታየት እና ጠንካራ ስራ መሥራትም ያስፈልጋል። በተለይም ባሕል ለድህነት የተለየ አስተዋጽኦ እንዳለዉም ዶ/ር ደመቀ ጠቁመዋል። በመሆኑም የሥራ ባሕልን በመቀየር የሥራ ዕድል መፍጠር እና በማስፋፋት ከድህነት ለመላቀቅ ሁሉም አስቦ መሥራት አለበት፤ ለዕቅዱ ተግባራዊነት እና ስኬታማነት በጋራ መሥራት የዜግነት ግዴታችን ሊሆን ይገባል።
በኲር የጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም