ባለፉት ሁለት ዓመታት ተመዝግበው መማር ከነበረባቸው ከ13 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ውስጥ ሰባት ሚሊዮኖቹ ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው እንደከረሙ የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል:: ይህም የሆነው ክልሉ ባጋጠመው በትጥቅ የታገዘ ግጭት ምክንያት ነው:: በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻል፣ የትምህርት ቤቶች መዘጋት እና ለጉዳት መዳረግ ደግሞ ፈተናዎች ናቸው::
የ2018 የትምህርት ዘመን የእስካሁኑ ስብራት መጠገኛ እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ ወደ ሥራ ቢገባም አሁንም ከፍተኛ ሥራን የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቋሚ ምልክቶች እየታዩ ነው:: በተዋረድ የሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ግን አሁንም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ በትጋት እየሠሩ ነው::
ባለፉት ሁለት ዓመታት የቀጠለው እና አሁንም ድረስ ዘላቂ መፍትሔ ያላገኘው በትጥቅ የታገዘ ግጭት ክፉኛ ከፈተናቸው አካባቢዎች መካከል የምዕራብ ጎጃም ዞን ይገኝበታል:: በዚህም ምክንያት በዝቅተኛ አፈጻጸም ውስጥ ያለፈው ዞኑ በዚህ ዓመት 426 ሺህ 29 ተማሪዎችን ማስተማር ዕቅዱ አድርጓል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መመዝገብ የተቻለው ግን 78 ሺህ 646 ተማሪዎችን ብቻ መሆኑን የትምህርት መምሪያ ኃላፊዉ የስጋት ደሴ አስታውቀዋል::
ምዝገባ አከናውነው በትምህርት ላይ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች ቁጥር 90 እንደሆኑም ነው የተናሩት:: አሁንም 510 ትምህርት ቤቶች እና ከ347 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ መማር ማስተማር አልተመለሱም:: ሕዝቡ “ሕጻናት ከትምህርት ውጪ የሚሆኑበት ጊዜ ማብቃት አለበት!” ብሎ መነሳት እንዳለበት ኃላፊው ጠይቀዋል::
የደቡብ ጎንደር ዞን በበኩሉ በ2018 ዓ.ም 811 ሺህ 211 ተማሪዎችን መዝግቦ ማስተማር ዕቅዱ ነው። እስካሁን የተመዘገቡትም 418 ሺህ 931 ተማሪዎች እንደሆኑ ያስታወቁት የትምህርት መምሪያው ምክትል ኃላፊ ተፈሩ መላኩ ናቸው። የትምህርት ሥራው ከገጠመው መስተጓጎል ለማውጣት ከፖለቲካ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው ማኅበረሰብ ድረስ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።
የክልሉ ነዋሪዎችም ባለፉት ዓመታት በትምህርት ሥራው ላይ የታየው ችግር የሕጻናትን መብት ነፍጓል፤ ክልሉንም ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለው መሆኑን ተናግረዋል:: ዶ/ር ነጻነት ጌጤ የደብረታቦር ከተማ ነዋሪ ናቸው:: ባለፉት ሁለት ዓመታት ያጋጠመው የሰላም እጦት በትምህርት ሥራው ላይ የፈጠረው ጫና ውጤት የሚገለጠው ውሎ አድሮ እንደሆነ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት::
በክልሉ የቀጠለው የጸጥታ ችግር ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችሉ ልጆችን አቅም ማክሰሙን ብዙ መሄድ ሳያስፈልግ በራሳቸው የቅርብ ወገኖቸወ እንዳዩ ነው ለበኵር የገለጹት:: “መኖሪያቸውን ገጠር ያደረጉ በጣም ጎበዝ፣ የተሻለ ደረጃ መድረስ የሚያስችል አቅም ያላቸው የወንድሞቼ እና የእህቶቼ ልጆች አሉ:: ነገር ግን ህልማቸው እና የመማር ጉጉታቸው ባለፉት ዓመታት ተገቷል፤ ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሚባክን ዕድሜ ውጤቱ የሚታየው ከጊዜ በኋላ ነው:: ይህ እንደ ዜጋ እያንዳንዱን ሊያሳስብ ይገባል:: ከዓመታት በኋላ በሚገለጠው ውጤት ቁጭት ውስጥ ከመግባት ‘ልጆች ለምን አይማሩም?‘ ብሎ በቁጭት መሥራት መጀመር ያለበት ዛሬ ነው:: ለዚህም ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ሁሉም አጀንዳው አድርጎ ሊሠራ ይገባል” ብለዋል::
“የወላጅ ትልቁ ደስታ ልጁ ተምሮ ለቁም ነገር ሲበቃ ነው” ያሉት ደግሞ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ነዋሪው አቶ ነጋ ውብዬ ናቸው:: ለዚህም ወላጅ ልጁ የሚያስፈልገውን የትምህርት ቁሳቁስ ሁሉ ተቸግሮም ቢሆን እያሟላ ዓመታትን ይጓዛል:: ከሁለት ዓመት በፊት ያጋጠመው የሰላም እጦት ግን የወላጅን የዓመታት ልፋት መና ያስቀረ፣ ልጆችም በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ወዳልተገባ ድርጊት ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ እንደሆነ ለበኵር ተናግረዋል::
አሁንም ትምህርት ቤቶችን ከጥቃት በመጠበቅ ለነገ ልጆች ሕይወት መሥራት እንደሚገባ አቶ ነጋ ጠይቀዋል:: ለሦስተኛ ዓመት ትምህርት እንዳይቋረጥ ማኅበረሰቡ “ትምህርት ቤቶቻችንን ተውልን!” ማለት እንዳለበትም አስገንዝበዋል:: በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ትምህርት እንዳይቋረጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል::
በትምህርት ሥራው ላይ እየደረሰ ያለው መስተጓጎል አፍራሽ ውጤት እስከምን ድረስ ይዘልቃል? የሚለውን መመልከት ለቀጣይ የተሳካ ሥራ ስንቅ ይሆናል:: በአፍሪካ ሕብረት አፍሪካ – አቀፍ የፖሊሲ ምርምር፣ ሥልጠና እና የምክር አገልግሎት የሚሰጠው ‘አማኒ አፍሪካ ሚዲያና የምርምር አገልግሎት’ የተሰኘው ተቋም ግጭት እና አለመረጋጋት ለአፍሪካ ትምህርት ትልቁ ፈተና መሆኑን ገልጿል:: ትምህርት ላይ የሚደርሰውን ጫና ዛሬ ላይ በዝምታ ማለፍ በነገ የሚገለጽ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርም ይዘረዝራል::
ግጭት በዓም አቀፍ ደረጃ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን ከትምህርት እንዲርቁ ያደርጋል:: አስተማማኝ ሰላም እስካልሰፈነ ድረስ በተቆራረጠ መንገድም ቢሆን የትምህርት ሥራ ቢቀጥል እንኳ ልጃገረዶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉትን ሕጻናት ያገለለ ይሆናል ይላል:: የልጅነት እና ያለ ዕድሜ ጋብቻ እንዲባባስ እና ጾታዊ ጥቃት እንዲስፋፋ ግጭት ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዳለው በአማኒ አፍሪካ ሚዲያና የምርምር አገልግሎት የሰፈረው ጽሑፍ ያስረዳል::
ግጭቶች በአጭር ጊዜ መቋጫ ካላገኙ በትምህርት ቤቶች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ይጨምራሉ:: ሕጻናትም ወዳልተገባ የግጭት አዙሪት ውስጥ እንዲሳቡ ያደርጋል:: ይህ ደግሞ ድህነት እንዲሰፋ እና እኩልነት እንዳይረጋገጥ ዳፋውን ጥሎ እንደሚያልፍም መረጃው አክሏል::
ከትምህርት ውጪ በመሆን ከዓመታት በኋላ ከሚገለጡ የዕድሜ ልክ ጉዳቶች መካከል የሥራ ዕድሎች መገደብ፣ ለድህነት ይበልጥ ተጋላጭ መሆን እና ማኅበራዊ መገለል ተጠቃሾች አድርጓል:: ለትምህርት ከለላ ሰጥቶ ተማሪዎች እንዲማሩ፣ መምህራን እንዲያስተምሩ፣ ባለድርሻ አካላትም በሚፈለገው ልክ የትምህርት ሥራውን እንዲደግፉ ከማድረግ ይልቅ ማስተጓጎል የነገው ሀገራዊ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ ምርታማነት እና ፈጠራ እንዲዳከም ከማድረግ ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ ጽሑፉ አስምሮበታል:: ይህም “እንማር?” የሚሉትን በመከልከል በአስተሳሰብ እና በአመለካከት የተዳከመ የሰው ኃይል በመኖሩ የሚመጣ ሥር የሰደደ የተጽዕኖ ውጤት እንደሆነ አመላክቷል::
እንደ አማካሪ ድርጅቱ የትምህርት ሥራ እንዲስተጓጎል ማድረግ ለሰላም በር ከመክፈት ይልቅ የግጭትን ዘላቂነት ያስቀጥላል:: ትምህርትን ያልተቀበለ አካል በዜጎች ሕይወት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችል አቅሙ ያነሰ ነው፤ ከዚህም የሚመጣው የድህነት እና የእኩልነት ማጣት ዑደት ሕዝቡን ወደ ተጨማሪ ግጭቶች የመሳብ ዕድሉን ከፍ ያደርጋል።
ግጭቶች በትምህርት መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ የትምህርት ተደራሽነት በሚፈለገው ልክ እንዳይሄድ የማድረግ አጋጣሚያቸው የሰፋ ነው:: መምህራን ባልተረጋጋ አካባቢ ለመሥራት ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ በግጭቱ ምክንያት መፈናቀል እና ለጉዳት መዳረግ የመምህራን እጥረት ግጭት ካበቃም በኋላ ፈተና ሆኖ ሊዘልቅ እንደሚችል ይታመናል:: ይህም የትምህርት ጥራት ፈተና ሆኖ ብቅ ማለቱ አይቀሬ እንደሚሆን መገንዘብ ይገባል::
ግጭት እና አለመረጋጋት ለትምህርት ሥራ የሚመደበው በጀት እንዲቀንስ ሊያደርግ እንደሚችልም ጽሁፉ አስፍሯል:: መንግሥታት በሀብት ውስንነት ምክንያት በግጭት ጊዜ እና ከግጭት በኋላ በትምህርት ላይ የሚያወጡትን ወጪ በመቀነሳቸው የተነሳ ሲሆን ይህም የትምህርት ሥርዓቱ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል::
በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በየዓመቱ ከትምህርት የሚርቁ ተማሪዎች ቁጥር እና በትምህርት ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ክልሉን ዋጋ እያስከፈለው እንደሚገኝ ጠቁመዋል:: በ2017 ዓ.ም ብቻ ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎች ቁጥር ከአፍሪካ የ15 ሀገራትን የሕዝብ ቁጥር መብለጡ ለችግሩ አሳሳቢነት ማሳያ አድርገው አንስተዋል::
በትምህርቱ ላይ እየደረሰ ያለው ችግር ተጽእኖ በክልሉ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ እና ዓለም የሚፈልጉትን ችግር ፈቺ የሰው ኅይል እንደሚያሳጣ ነው የገለጹት:: ሕጻናት ለዓመታት ከትምህርት ሲርቁ በዕድሜያቸው ልክ ማግኘት የሚገባቸውን ዕውቀት አያገኙም፤ የነበራቸው ተሰጥኦ ይመክናል፤ እነዚህ ሁሉ አሉታዊ ተጽእኖዎች እንደ ሕዝብ የሚነሳው የመልማት አቅም እና ፍላጎት እንዳይሳካ እንደሚያደርግ ነው ያስረዱት::
በአጠቃላይ በትምህርት ላይ ያጋጠመው ስብራት የትውልድ ቅብብሎሽን የሚያቋርጥ፣ የክልሉን የመልማት አቅም የሚያጓትት፣ የአገልግሎት አሰጣጡ ከመዘመን ወደ ኋላ የሚያስቀር፣ የክልሉን ሕዝብም ከማንኛውም ተሳትፎ የሚነጥል እንደሆነ ገልጸዋል:: በመሆኑም የ2018 የትምህርት ዘመን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከትምህርት ውጪ ሆኖ የቆየውን ተማሪ ሁሉ ወደ መማር የሚመልስ እንዲሆን የሚያደርግ ዕቅድ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል::
ሰባት ሚሊዮን 445 ሺህ 545 የትምህርት ዘመኑ የተማሪ ዕቅድ ነው:: ቢሮው የሩብ ዓመት አፈጻጸሙን በደብረ ብርሃን ከተማ በገመገመበት ወቅት 79 በመቶ ትምህርት ቤቶች ተከፍተዋል፤ 51 በመቶ ተማሪዎችም ተመዝግበዋል። ዕቅዱን ለማሳካት፣ የትውልድ ቅብብሎሹን ለማስቀጠል፣ እንደ ክልል የሚጠበቀውን ተወዳዳሪ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት እና የክልሉ ሕዝብ ለትምህርት ያለውን ከፍ ያለ ዋጋ ለማስቀጠል በርብርብ መሥራት ዋና ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ኃላፊዋ ጠቁመዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም