የዛሬ ሃምሳ አመት ገደማ ከፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችው ኬፕ ቨርድ እንደ ሀገር በራሷ ለመቆም ስትንገዳገድ እኛ ኢትዮጵያውያን ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቀኝ ግዛት ነጻ መውጣት ብርታትና ወኔ ከመሆን ባለፈ የአፍሪካ ዋንጫን መስርተን ከተሳትፎ ባለፈ ውድድሩን በማሸነፍ ሌላ ታሪክ ሰርተን አልፈናል።ልዩነቱ እኛ በመሰረትነው እግር ኳስ ለመሳተፍ እንኳ ከብዶን አንዴ ሰላሳ አንድ አመታት ሌላ ጊዜ ስምንት አመታት ብዙ ጊዜ ደግሞ ተመልካች ሆነን በመድረኩ ስንጓዝ በቅርብ አመታት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የመጣችው ኬፕቨርድ በአስደናቂ ብቃትና በአጭር ጊዜያት ታላላቅ ሀገራት ተመኝተው ያልተሳካላቸውን የአለም ዋንጫ ተሳትፎ ያላገኙትን ትንሿ ሀገር ግን ዘና ኮራ ብላ ለተሳትፎ መብቃቷ ነው።
ከግማሽ ሚሊዮን ያልበለጠ የህዝብ ቁጥር ያላት ኬፕቨርድ ለእግር ኳሷ እድገት እንደምክንያት የሚነሳው በርካታ ተጫዋቾቿ ከፖርቱጋል የዘር ሀረግ የሚመዘዙ በመሆናቸው ነው የሚል ማስረጃ ደጋግሞ ይነሳል።ይህን ሀሳብ እኔ በተቃርኖው እመለከተዋለሁ።ምክንያቴ ደግሞ ኬፕ ቨርድ ለፖርቱጋል እግር ኳስ ውጤታማነት ባለውለታ ናት ብየ ነው የማስበው።ለምሳሌ የዘር ሀረጋቸው ከትንሿ አፍሪካዊት ሀገር ኬፕቨርድ ሆኖ በፖርቱጋል እግር ኳስ አሻራ ካላቸው ከስምንት በላይ ተጫዋቾች መካከል ሉዊስ ናኒ አንዱ ነው።ኬፕ ቨርድ ለአለም ዋንጫ ማለፏን እንዳረጋገጠች ናኒ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፏል።የሆነው ሆኖ ኬፕ ቨርድ ለአለም ዋንጫ ለመብቃት ስምንት አመታት ብቻ ወይም የሁለት አለም ዋንጫ ብቻ እድሜ ፈጅቶባታል።ሩሲያ ባዘጋጀችው የ2018ቱ የአለም ዋንጫ ለመድረስ ጥረት አድርጋ ያልተሳካላት ኬፕ ቨርድ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በትጋት በመስራት የማይቻል የሚመስለውን የአለም ዋንጫ ተሳትፎን እውን አድርጋለች። የኬፕ ቨርድ ለአለም ዋንጫ መብቃት የህዝብ ብዛት ከቁጥር የበለጠ አለመሆኑን አሳይቷል።በዚህ ረገድ የአለማችን በህዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆኑት ህንድ እና ቻይና በጋራ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ህዝብ ይዘው አልተሳካላቸውም።
በአፍሪካ ቀዳሚ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትመደበው ኢትዮጵያ ሰንደቋን ከፍ አድርገው በታላቁ መድረክ ጮቤ የሚያስረግጧት 11 ተጫዋቾች ለማግኘት ተቸግራለች። በአፍሪካ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ከፋይ ሊግ ያላት ሀገራችን ወይ ሊጉ ጥራት የለው ወይ ብሔራዊ ቡድኗ ለአለም ዋንጫ አይደለም ለአፍሪካ መድረክ አይበቃ ዝም ብሎ ባለበት መርገጥ ጠያቂም ተጠያቂም ያጣ ሆኗል። ለመሆኑ ኬፕ ቨርድ ምን ሰርታ ነው ለአለም ዋንጫ የበቃችው?
ደሴቲቱ ኬፕ ቨርድ በምድሯ ተፈጥረው ነገር ግን ለፖርቱጋል የሚጫወቱትን ተጫዋቾች ለእናት ሀገራቸው ተመልሰው እንዲጫወቱ ብሎም ብሔራዊ ስሜት እንዲያድርባቸው ልዩ ልዩ ተግባራትን ሰርታለች። ከሊግ እርከን እስከ ብሔራዊ ቡድን ባለው አደረጃጀት የኬፕ ቨርድና ፖርቱጋላውያን አሰልጣኞች ስብጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ በመግባባት ይሰራሉ። በኬፕ ቨርድ ተወልደው ለፖርቱጋል የተጫወቱ ታላላቅ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ወደ እናት ሀገራቸው ቶሎ ቶሎ እየሄዱ ልምድ ያካፍላሉ፤ ይደግፋሉ፤ ይገመግማሉ፤ ያዩትን ክፍተት እንዲሞላ ሀሳብ ያቀርባሉ። ከዚያ ባለፈ ኬፕ ቨርድ ውስጥ የተመሰረቱት ፕሮጀክቶችና አካዳሚዎች የጥራት ደረጃቸው በአውሮፓ ልኬት ላይ መሆናቸው የእግር ኳሱ እድገት በፍጥነትና የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል አድርጎታል።
የእኛስ? ከፕሮጀክት እስከ ክለቦቻችን አደረጃጀት ድረስ ከዘመኑ የራቁ ናቸው።ስራችን በተግባር ሲመዘን ሀገርን ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን ለግል ጥቅም ወይም ለግለሰብ ፍላጎት ሲባል የሚሰራ በመሆኑ በየአመቱ የእግር ኳሳችን እድገት የኋሊዮሽ ሆኗል። በጣም የሚያበሳጨው ደግሞ እግር ኳሳችን የገንዘብ ችግር ስላለበት ነው እንዳይባል በየአመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ ይደረጋል ውጤቱ ባዶ ነው። በአፍሪካ ሶስተኛውን ውድ ከፋይ ሊግ ይዘን ሜዳ ሳይኖረን ከፍተኛ ደሞዝ እየከፈልን ቀዳሚ ጀማሪነታችን ጠፍቶ የሌሎች አድናቂ ሆነን ጉዟችን ባለበት ቀጥሏል።
እግር ኳሳችን የሚመሩት አካላት በምርጫ ከመፈራረቅ በዘለለ ወደ ስልጣን ለመምጣት ከሚያደርጉት ዱላ ቀረሽ የፋክክር ትንቅንቅ በዘለለ በቆይታቸው ጥለውት የሚያልፉት አሻራ ብዙም ባለመሆኑ የኬፕ ቨርድን አይደለም ከጎረቤቶቻችን እንኳ የሚቀራረብ የእግር ኳስ እድገትና አደረጃጀት የለውም።በአንድ ወቅት አንድ የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለማይሰራበት እንጅ በአፍሪካ የኢትዮጵያን የሚያህል የእግር ኳስ አቅም ያለው ሀገር አላየሁም ሲሉ ተናግረዋል።ይሄ የአሰልጣኙ ንግግር በራሱ ብቻ ቁጭት ፈጥሮብን ሊያነሳሳን ይገባ ነበር።እግር ኳሱ የሚመለከታቸውን ታላላቅ ሙህራንን ከማቅረብ ይልቅ አትንኩኝ ብሎ ብቻውን የሚጓዝ በመሆኑ አለም ከሚሄድበት ሳይንሳዊ አሰለጣጠን ይልቅ ተፎካካሪ የማያደርግና ለውጥ በማይፈልጉ ሰዎች የታጠረ እግር ኳስ ማስቀጠላችን ዛሬ ዋሊያው በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጅራት ሆኖ ማጠናቀቅ ልማዱ አድርጎታል።
የ2029 አፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ለካፍ ጥያቄ ያቀረበችው ኢትዮጵያ በቀሪ አራት አመታት ውስጥ ምን ተሰርቶ ነው ጠንካራ ብ/ቡድን ይዘን የምንቀርበው።ያ መድረክ ደግሞ ለ2030 አለም ዋንጫ የሚያመጣው ጸጋ እንደሚኖር መገመት ቀላል ቢሆንም ዛሬ በበቂ ሁኔታ ያልተሰራባቸው ታዳጊዎች ነገ ከየት መጥተው ጠንካራ ብ/ቡድን እንደሚፈጠር በጣም አሳሳቢ ነው።
ለማንኛውም ከፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች የሃምሳ አመት የእድሜ ባለጸጋዋ ኬፕ ቨርድ ከምንም ተነስታ ለዚህ ሁሉ ስኬት አልበቃችም፤ በጠንካራ ስራ እና መቅደም ያለበትን በማስቀደም ነው። ከኬፕ ቨርድ በላይ እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ እድገት እና ጉዞ በየአመቱ ባለበት ከመጓዝ ተላቆ ከወንበርና ከጥቅማቸው ይልቅ የሀገር ውጤት መጥፋት በሚያሳስባቸው ሰዎች ሊመራ ይገባል።የሚመለከተው አካልም ቢሆን በየአመቱ ይህ ሁሉ በጀት እየፈሰሰ ስንት ሆስፒታል ስንት ትምህርት ቤት የሚገነባ ቢሊዮን ገንዘብ እየፈሰሰ ለምን ውጤቱ የቁልቁለት ሆነ? ብሎ መጠየቅ ይገባዋል!!!።
(መልሰው ጥበቡ)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም