ለስኳር በሽታ ተጋላጭነትን የሚቀንሰዉ

0
13

አትክልት፤ ፍራፍሬ እና ዓሳ የመሣሰሉትን “ሜዲትራኒያን” የምግብ ዓይነቶችን በመመገብ፣ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር ያጣመረ የአኗኗር ዘይቤን መከተል የስኳር በሽታ ተጋላጭነትን 31 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል::

በስፔን የናቭራ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ከሌሎች አገራት አቻ ምሁራን ጋር በመተባበር ባደረጉት ጥናት እና ክትትል የኃይል ሰጪ መጠናቸው ያነሰ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ቅጠላ ቅጠል እና ዓሣን መመገብ 31 በመቶ በስኳር በሽታ የመጠቃት አጋጣሚን እንደሚቀንስ አረጋግጠዋል:: አብዛኛዎቹ ሰዎች ጤናማ ምግብ፣ ወይም ችግሮችን በማያስከትሉ “ርካሽ” የሚመሰሉ ምግቦችን እንደማያዘወትሩ ነው ያሰመሩበት -ተመራማሪዎቹ:: ይህ በመሆኑ ደግሞ የጤና ችግር በሚያስከትሉ የምግብ ዓይነቶች ላይ በመመርኮዝ ለጤና እክል ይዳርጋሉ ነው ያሉት::

የናቭራ ዩኒቨርስቲ 200 ከሚሆኑ ከ22 ዩኒቨርስቲ እና የጤና ተቋማት ከተውጣጡ ተመራማሪዎች ጋር በጥምረት ሰፊ እና ጥልቅ ምርምሮችን አድርገዋል::

በምርምሩ በአጠቃላይ 4746 እድሜያቸው ከ55 እስከ 75 ዓመት የሆናቸው የናሙና ተሣታፊዎች ተካተዋል:: የናሙና ተሣታፊዎቹ ቀደም ብሎ ምንም ዓይነት የስኳር ህመም የሌለባቸው ሆነው በሁለት ቡድኖች ተከፍለዋል:: አንደኛው ቡድን ጣፋጭ ወይም ኃይል ሰጪ መጠኑ የተቀነሰ ምግብን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር እንዲያዛወትሩ ተደርጓል:: ሌላኛው ሁለተኛው ቡድን ደግሞ የኃይል ሰጪ ወይም የጣፋጭ መጠኑ ያልተቀነሰ ምግብ ያለ አካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያዘወትሩ አድርገዋል- ተመራማሪዎቹ::

ተመራማሪዎቹ በናሙና ምርምሩ ክትትል ያደረጉባቸው ለስድስት ዓመታት ሲሆን ውጤቱን በመቀመር ግኝታቸውን ይፋ አድርገዋል:: በመሆኑም ከጠቅላላ የጥናትና ምርምር ተሣታፊዎች የኃይል ሰጪ ይዘቱ የተቀነሰ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ዓሣ የመሳሰሉትን አጣምረው የተመገቡቱ 31 በመቶ የስኳር በሽታ ተጋላጭነታቸው መቀነሱን ነው ያረጋገጡት – ተመራማሪዎቹ::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here