ትምህርትን የማስቀጠያ አማራጮች

0
10

እንደ መንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መረጃ  በ2024 እ.አ.አ 251 ሚሊዮን ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ አልተገኙም:: ለትምህርት የሚደረገው ኢንቨስትመንት ከሚጠበቀው በታች ዝቅተኛ መሆንን ዩኔስኮ ይገልጻል:: ሴቭ ዘ ችልድረን ከትምህርት ውጪ ከሆኑት 251 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ለ103 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት መራቅ ቀዳሚው ምክንያት በትጥቅ የታገዘ ግጭት እንደሆነ አስቀምጧል::

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት በትጥቅ ግጭት እና በጦርነት ውስጥ ሆነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳጊዎች ከትምህርት በራቁበት በዚህ ወቅት ትምህርትን በምን አግባብ ማስቀጠል ይገባል? የሚለው ወቅታዊ ገዥ ጥያቄ ነው:: የሰው ኀይል ክምችት የሚገለጸው በአንድ ግለሰብ ውስጥ ያለው እውቀት፣ ክህሎት፣ ችሎታ እና ብቃት ድምር ውጤት እንደሆነ የምጣኔ ሐብት ትንተናዎች ያሳያሉ:: ነገር ግን በግጭት እና በጦርነት ምክንያት የሚስተጓጎል ትምህርት የሰው ኅይል ክምችትን በማሳጣት ሀገራት ዕድገታቸው ወደ ኋላ እንዲቀር ሊያደርግ እንደሚችልም ይታመናል::

ለዚህም ነው ጥናቶችን እና አዳዲስ ግኝቶችን በማጋራት የሚታወቀው ‘ኦፕን ፕራክሲስ’ (openpraxis.org) በጦርነት ወቅት ትምህርት መቀጠል እንዳለበት ጠቁሟል:: ለዚህም መፍትሔዎችን አመላክቷል፤ ጦርነት በተማሪዎች፣ መምህራን እና ወላጆች ላይ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ስብራት እና የትምህርት መሰረተ ልማት ውድመትን  ጥሎ ያልፋል የሚለው ጥናታዊ ጽሑፉ፣ በዚህ ወቅት ትምህርት ከርቀትም ቢሆን ማስቀጠል በመፍትሔነት ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁሟል:: ይህም የልጆችን የመማር መብት ከማስጠበቅም በላይ ከረጅም ጊዜ የሰብዓዊ ሀብት ክምችት ፈተና ለመውጣት ዋና መውጫ መንገድ እንደሚሆን አጽንኦት ሰጥቷል::

ትምህርትን በሬዲዮ ተደራሽ ማድረግ፡- በአካባቢያዊ ተደራሽነት እና በዋጋ ተመጣጣኝነት ብዙዎች ቤት የማይጠፋው ሬዲዮ በጦርነት፣ በግጭት እና ሌሎች ተፈጥሯዊ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት የተቋረጠን ትምህርት ለማስቀጠል ወሳኝ መንገድ እንደሆነ ጥናቱ ለይቷል:: ይህ ዘዴ በከፍተኛ አስጊ ሁኔታዎች ውስጥ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ መሆኑንም ጠቁሟል::

በሬዲዮ ከትምህርት በላይ የሆኑ መልዕክቶችን በቀላሉ በማስተላለፍ ለሰላም እና መረጋጋት ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም በጥናቱ ተጠቁሟል:: እንደ ጥናቱ በቀውስ ወቅት ብዙዎች ለከፋ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ይዳረጋሉ:: በመሆኑም ትምህርቱ በሚሰጥበት ወቅት በየመሀሉ የግጭትን አውዳሚነት፣ የሰላምን አስፈላጊነት፣ ከግጭት እንዴት መውጣት እንደሚገባ የሚያግዙ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ልጆች ከደረሰባቸው ስነ ልቦናዊ መረበሽ እንዲወጡ የሬዲዮ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተመላክቷል:: እነዚህ ይዘቶች ተማሪዎችን ከማረጋጋትም ባሻገር ማኅበረሰቡ የግጭትን አላስፈላጊነት እንዲረዳ በማድረግ ሰላም እና መረጋጋትን በአጭር ጊዜ እንዲመለስ የራሱ አበርክቶ እንደሚኖረውም በጥናቱ ተገልጿል::

በችግር ወቅት ትምህርትን በሬዲዮ አማካኝነት አስቀጥለው ውጤታማ ከሆኑ ሀገራት መካከል ጥናቱ ቀዳሚ ያደረጋት አፍጋኒስታንን ነው:: ብዙ ሰዎች ሬዲዮ የሚያደምጡበትን ጊዜ የለየው የሀገሪቱ ተሞክሮ፣ ይህም በሥራ ምክንያት ወይም በደህንነት ስጋት ትምህርት መከታተል የማይችል ተማሪ እንዳይኖር ታሳቢ ያደረገ ነው:: በተጨማሪም የትምህርት ሥርጭቱ በቀን ሁለት ጊዜ እንዲተላለፍ ይደረጋል:: ይህም በመጀመሪያው መከታተል ያልቻለ በሁለተኛው እንዲከታተል ከማገዙም ባለፈ ይዘቱ በተደጋጋሚ መሰጠቱ የተሻለ ዕውቀት እንዲያገኙ ጉልህ አበርክቶ ስለመጫወቱ ጥናቱ አመላክቷል:: ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያም የሬዲዮ ትምህርትን ተማሪዎች ወዳልተፈለገ አላማ እንዳይገቡ የማረጋጊያ ስልት አድርገው እንደተጠቀሙበትም ጥናቱ ለይቷል::

የመስመር ላይ ትምህርት፡- በግጭት እና በሌሎች ምቹ ባልሆኑ ችግሮች ምክንያት የተቋረጠውን ትምህርት በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች ማስቀጠል ከእረጅም ጊዜ በኋላ ሊያጋጥም ከሚችል የተማረ የሰው ኅይል ክምችት እጥረት ለመዳን ሌላኛው መፍትሄ ሆኖ በጥናቱ ተለይቷል:: ዩቱዩብ፣ ፌስ ቡክ፣ ቴሌግራም፣ ዙም እና ሌሎችን የበይነ መረብ አማራጮችን በመጠቀም የሚሰጠው አገልግሎቱ ትልቁ ውስንነቱ የቴክኖሎጂ እና የኅይል  መሠረተ ልማት መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል:: አገልግሎቱ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እና የኅል መሠረተ ልማት ባለባቸው አካባቢዎች ቢሰጥም ሕጻናት ከድባቴ ወጥተው በቅርቡ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ተስፋ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ግን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ጥናቱ አስፍሯል::

ኢንተርኔት የማይጠቀሙ ወይም የኢንተርኔት ፍጆታቸው ዝቅተኛ የሆኑ መተግበሪያዎችን በማፍለቅ የቴክኖሎጂ እና የኅይል መሠረተ ልማት ውስንነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችንም በእኩል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ጥናቱ አረጋግጧል::

ማኅበረሰብ ተኮር ትምህርት፡-

ተማሪዎች ከአንድ ዓመት በላይ ከትምህርት ውጪ በሚሆኑበት ጊዜ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ይወድቃሉ:: የዕድሜ መግፋት፣ የትምህርት መረሳት እና እንደ አዲስ መጀመር ከተወዳዳሪነት ውጪ ማስወጣት፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ወደ ግጭት መግባት ተጽእኖዎቹ ናቸው:: ታዲያ ተማሪዎችም ሆኑ በአካባቢው የሚኖሩ መምህራን ከሕዝብ ጋር በመነጋገር ማኅበረሰብ ተኮር ትምህርትን በመፍትሄነት ተግባራዊ በማድረግ ልጆችን ከስነ ልቦናዊ ጉዳት መታደግ እንደሚገባ ጥናቱ አስቀምጧል::

ግጭቶች ሰዎች ወደ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዳይሄዱ ሲያደርጉ፣ ጊዜያዊ መማሪያ ቦታዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ይፈጠራሉ፤ ትምህርትን ለማስቀጠልም ይውላሉ:: እነዚህም ቦታዎች ትምህርቱን ወደ ሕዝቡ በማምጣት በትምህርት፣ ሰላም እና ልማት ትልቅ ለውጥ ለማምጣት አጋዥ እንደሚሆኑ ይታመናል:: ደቡብ ሱዳን በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች የማኅበረሰብ ተኮር ትምህርት ቤትን በመፍጠር የተቋረጠው ትምህርት ልጆችን ወዳልተፈለገ ዓላማ እንዳይመራቸው ለማድረግ ሥራ ላይ ውሏል::

በሲኖ-ጃፓን ጦርነት ወቅት በርካታ የቻይና ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዳይቋረጥ ሲሉ ትምህርትን በመጠለያዎች እና ዋሻዎች ውስጥ ማስቀጠል የቻሉበት መንገድም ተጠቃሽ ነው::

የተለያየ የክፍል ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች አንድ ላይ ማስተማር፡- ይህ ማለት አንድ ብቃት ያለው መምህር በአንድ የትምህርት ክፍል ውስጥ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ እና የተለያየ የክፍል ደረጃ ያላቸውን ተማሪዎች በአንድ ላይ ማስተማር ነው። ይህ ዘዴ በተለይም በአንድ ክፍል ተመዝግቦ መማር የነበረበት የተማሪ ቁጥር በሚጠበቀው ልክ ሳይሆን የሚተገበር የመፍትሔ አማራጭ ነው:: ይህ ዘዴ በግጭት ወይም በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ አካባቢዎች ብዙ ትምህርት ቤቶችን ወይም ብዙ መምህራንን መቅጠር የማይችሉበት ሁኔታ ባሉት ውስን መምህራን እና የመማሪያ ክፍሎች ትምህርቱን ለማስቀጠል ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል:: በተጨማሪም ይህ ዘዴ በአካባቢው ያሉ ልጆች ሳይለያዩ በአንድ ክፍል ውስጥ በአንድነት እንዲማሩ ስለሚያስችል በማኅበረሰቡ ውስጥ ትስስር እና መደበኛ ግንኙነት እንዲሰምር አጋዥነቱ ከፍተኛ ነው:: በ1990 ዓ.ም የቬትናም መንግሥት በጦርነት ምክንያት ተነጥለው የሚኖሩ የጎሳ ቡድኖችን ልጆች የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት ይህንን ዘዴ ተጠቅሟል። ይህም በቂ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ትምህርት ለማግኘት በተስፋ ሲጠባበቁ ለነበሩ ተማሪዎች ትልቅ አማራጭ ሆኖ ታይቷል::

ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቀደመ ቀያቸው እስኪመለሱ ጊዜ ድረስ ተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት፣ ራስን በራስ የማስተማር፣ ልዩ መሰጠትን ለይቶ ተሰጥኦን የማዳበር እና ሌሎችም ስትራቴጂዎች በጦርነት እና ግጭት ወቅት ትምህርትን ለማስቀጠል ወሳኝ መፍትሔዎች ሆነው በጥናቱ ተለይተዋል:: የእኛዋ ሀገር ኢትዮጵያን ጨምሮ በግጭት አዙሪት ውስጥ የሚገኙ ሀገራት የዜጎቻቸውን የመማር ዕድል በማስቀጠል ከጊዜ በኋላ ከሚፈጠር የተማረ የሰው ኅይል መቀነስ ለመውጣት አዋጭ መፍትሄዎችን ለይተው ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል::

ግዕዝ በአማርኛ

ሌለየ- ለየ

መሀረ – አስተማረ

መሐረ – ይቅር አለ

መዘረ – ጠላ ጠመቀ

ሠዐለ  – ሥዕል ሣለ

ሠረቀ – ወጣ (ፀሐይ)

ሰአለ – ለመነ

ምንጭ፡- ጥንታዊ ግዕዝ በዘመናዊ አቀራረብ

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here