የጋዛ  ውድመት እና  የሠላም ስምምነት

0
15

ታሪካዊ ነው ተብሎ የተሞካሸው እና በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊት አውራሪነት የተፈረመው የጋዛ ሰላም ስምምነት በተለይ ለፍልስጤማዊያን ልዩ የደስታ ስሜትን ፈጥሯል፤ አብዛኛዎቹ የጋዛ አካባቢዎች ከሁለት ዓመታት ግጭት በኋላ የፍርስራሽ እና የድንጋይ ክምር ቢሆኑም ፍልስጤማዊያን የተኩስ አቁሙን በደስታ ሲያከብሩ ታይተዋል::

ስምምነቱን ተከትሎ እስራኤላዊያን ታጋቾች በሃማስ በኩል፣ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውን 250 ፍልስጤማዊያንን ጨምሮ ሁለት ሺህ የሚጠጉ እስረኞች ደግሞ በእስራኤል በኩል ተለቀዋል።

ቢቢሲ እንደዘገበው በአሜሪካው ፕሬዚዳንት የቀረበው የሰላም ዕቅድ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ማግኘት በመቻሉ ታጋቾቹ ተለቀዋል። ሃማስ በሕይወት ያሉ 20 እስራኤላዊ ታጋቾችን መልቀቁን ተከትሎ ትራምፕ በእስራኤል ምክር ቤት በመገኘት ባደረጉት ንግግር   “ቀኑ ለመካከለኛው ምሥራቅ ታሪካዊ ነው!” ብለዋል።

በእስራኤል እና በሃማስ  መካከል ሰላም እንዲወርድ ላደረጉ የዓረብ ሀገራት  ምስጋና ያቀረቡት ትራምፕ “በጋራ መሥራት ታላቅ ድል አስገኝቷል” ሲሉ የተደምጠዋል::

እስራኤል እና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ከተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎች ወጥቷል። የሰላሙ ዕቅድ በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ይሁንታ ካገኘ በኋላ ፍልስጤማዊያን ከተሰደዱበት ቦታ ወደ ፈራረሰው መኖሪያቸው መመለስ ጀምረዋል።

ትራምፕ በግብጽ ሻርም ኤል-ሻይክ ከ20 በላይ ከሚሆኑ የሀገራት መሪዎች ጋር በመሰባሰብ በቀጣዩ የጋዛ የሰላም ዕቅድ ላይም ተወያይተዋል:: አሜሪካ፣ ቱርክ፣ ግብጽ እና ኳታር   የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊነትን የሚከታተሉ ሀገራት ሆነዋል።

አልጀዚራ እንደዘገበው የእስራኤል እና የሃማስ ግጭት ከተጀመረ  ሁለት ዓመት ሆኖታል። እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት የጀመረችው እ.አ.አ ጥቅምት 07 ቀን 2023 በደቡብ እስራኤል ላይ የሃማስ ታጣቂዎች ላደረሱት ጥቃት ምላሽ ነበር::  በወቅቱም  ከእስራኤል በኩል አንድ ሺህ 139 ሰዎች ሲገደሉ 240 ያህሉ በምርኮ ወደ ጋዛ ተወስደው ነበር።

የእስራኤል የሁለት ዓመታት ጥቃት በትንሹ የ67 ሺህ ፍልስጤማዊያንን ሕይወት ቀጥፏል። ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አስከሬናቸው ሳይወጣ በፍርስራሹ ውስጥ ቀርቷል።  ከሟቾች መካከል ቢያንስ 20 ሺህ ሕጻናት ናቸው:: ይህም ማለት ላለፉት 24 ወራት በየሰዓቱ አንድ ሕጻን ይገደል ነበር። በእስራኤል በኩል ወታደሮቿን ጨምሮ ከሁለት ሺህ በላይ ዜጎቿ ሕይዎታቸው አልፏል::

በተያያዘም በጋዛ ከ169 ሺህ በላይ ሕዝብ የመቁሰል አደጋ አጋጥሞታል፤ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በጋዛ ውስጥ ከሦስት ሺህ እስከ አራት ሺህ የሚደርሱ ሕጻናት አንድ ወይም ከዚያ በላይ አካላቸውን አጥተዋል ብሏል። ድርጅቱ እንዳስታወቀው ባለፉት ሁለት ዓመታት 34 ሆስፒታሎችን ጨምሮ ቢያንስ 125 የጤና ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል፤ ይህም ታማሚዎች አስፈላጊ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙ አድርጓል።  በሆስፒታሎች ላይ በደረሱት ጥቃቶች እና በጋዛ ላይ በቀጠለው የቦምብ ድብደባ ቢያንስ አንድ ሺህ 722 የጤና እና የእርዳታ ሠራተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በአራተኛው የጄኔቫ ስምምነት ከአንቀጽ 18 እስከ 22 ባለው መሠረት ሆስፒታሎች የጥቃት ዒላማ ሊሆኑ እንደማይገባ ቢገለጽም በአሁኑ ጊዜ በሚደረጉ ጦርነቶች የጤና ተቋማት እየወደሙ ናቸው።

ሌላው የጋዛን ሕዝብ ከጦርነቱ ባልተናነሰ ሕይዎታቸውን ስቃይ ውስጥ የጨመረው ረሃብ ነው:: 154 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 459 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሞተዋል። እ.አ.አ ነሐሴ 22 ቀን 2025 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ ዓለም አቀፍ የረሃብ ክትትል (አይ ፒ ሲ) መሠረት በመካከለኛው ምሥራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ዕውቅና የተሰጠው  ረሃብ የተከሰተው በጋዛ ነው።

እንደ አይ ፒ ሲ ዘገባ በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ግዛት የተከሰተው ረሃብ   ወደ ዴይር ኤል-ባላህ እና ካን ዮኒስ ግዛቶች እንደሚሰፋ ስጋት ፈጥሯል። ከጠቅላላው የጋዛ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው (641 ሺህ ሕዝብ) አስከፊ የረሃብ ሁኔታዎች ይገጥማቸዋል ተብሎ ይጠበቃል::

በሐምሌ ወር ብቻ ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት በከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሕይወታቸው አልፏል:: ከአራት ሕጻናት መካከል አንዱ  በከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ይሰቃያል::  ከአምስት ሕጻናት አንዱ የሚወለደው ያለጊዜው ወይም ከክብደት በታች መሆኑም የሟች ሕጻናት ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀፍ ውጭ ሲንቀሳቀስ የነበረው በእስራኤል እና በአሜሪካ የሚደገፈው የእርዳታ ማሰራጨት ሥራ ረሃቡን አባብሶት እንደነበር መረጃው አመላክቷል:: የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር እንደገለጸው ከጣቢያዎች ምግብ ለመሰብሰብ ሲሞክሩ የነበሩ ከሁለት ሺህ 600 በላይ ሰዎች ተገድለዋል:: ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል::

የጋዛ የውኋ እና የፍሳሽ ማስወገጃ መሠረተ ልማት 89 በመቶ ተጎድቷል:: የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ 89 በመቶው የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና መረብ ተጎድቷል ወይም ወድሟል፤ ይህም ከ96 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች የውኃ ዋስትና እንዳይኖራቸው አድርጓል።

በተጨማሪም በጋዛ የሚገኙ ሁሉም ቤቶች በሚባል ደረጃ ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በነሐሴ ወር ይፋ ባደረገው መረጃ 92 በመቶ የመኖሪያ ሕንፃዎች እና 88 በመቶ የንግድ ተቋማት ወድመዋል።

62 በመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎች የንብረት ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ሕጋዊ ሰነዶች ስለሌላቸው መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ትግል በተግዳሮቶች የተሞላ ይሆናል። በርካታ ቤተሰቦች የመልሶ ግንባታው ሂደት ቢጀመርም ቤታቸውን ወይም መሬታቸውን ማስመለስ ስለማይችሉ ለዘለቄታው ይፈናቀላሉ::

የዓለም ባንክ በየካቲት ወር(2025) ይፋ ባደረገው ግምገማ መሠረት በጋዛ የእስራኤል የቦምብ ድብደባ ያደረሰው ቀጥተኛ ጉዳት 55 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

የጋዛ የትምህርት ሥርዓትም በጦርነቱ ምክንያት  ተሽመድምዷል:: 658 ሺህ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት እና 87 ሺህ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይማሩባቸው የነበሩ ተቋማት በመውደማቸው  የመማር ዕድልን አጥተዋል። ቢያንስ 780 በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ ሠራተኞችም ተገድለዋል:: 63 የዩኒቨርሲቲ ሕንፃዎችን ጨምሮ ከሁለት ሺህ 300 በላይ የትምህርት ተቋማት ወድመዋል። አሁንም የተረፉት  ለተፈናቃዮች መጠለያ እየሆኑ ነው።

እ.አ.አ ከጥቅምት 07 ቀን 2023 ጀምሮ በጋዛ 300 የሚጠጉ ጋዜጠኞች እና ሌሎች የሚዲያ ሠራተኞች ተገድለዋል፤ ከነዚህም መካከል 10 የሚሆኑት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች መሆናቸውን መረጃዎች አመላክተዋል::

የጀርመኑ ዶቼቨሌ እንደዘገበው በአጠቃላይ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶች 60 ሚሊዮን ቶን ወደ ሚገመት ፍርስራሽነት ተቀይረዋል:: ይሁንና  የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለ 20 ነጥብ የተኩስ አቁም ዕቅዳቸው ውስጥ ጋዛ እንዴት እንደምትገነባ ዝርዝር መረጃ አላካተቱም:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 70 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ቢገምትም ገንዘቡ ከየት እንደሚገኝ እና ማን እንደሚያስተዳድረው የተቀመጠ ነገር የለም::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዛን ማን ያስተዳድር፣ ሃማስ ማናቸውንም የጦር መሳሪያዎች እና መሠረተ ልማቶች ማስረከብ ወይም ማውደም አለበት፤ የእስራኤል ወታደሮች ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ ለቀው መውጣት አለባቸው፤ የሚሉት  ለሰላም ስምምነቱ መጽናት ስጋቶች ሆነዋል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here