የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ያደርጋታል ተባለ

0
13

የኮሪደር ልማቱ ባሕር ዳር ከተማን ከአፍሪካም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚያርጋት ተጠቆመ፤ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ እና ሌሎች ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ አባላት በባሕር ዳር ከተማ እየተከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር እና የሐይቅ ዳር ልማት ጎብኚተዋል:: ከባሕርዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋርም የልምድ ልውውጥ አድርገዋል::

ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በፊት ዝም ብለው ታጥረው የተቀመጡ በቆሻሻ የተሞሉ ስፍራዎችን በማጽዳት ለመዝናኛ እና ለማንበቢያ በሚመች መልኩ መሥራቱ እና ማስዋቡ የሚበረታታ ነው ያሉት የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ በቢሾፍቱም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል::

የባሕር ዳር መንገዶች መስፋታቸው እና ቀደም ሲል የማይገናኙ መንገዶቿን እንዲገናኙ መደረጉ እንዲሁም የጣና ሐይቅን  ከሚሠራው ልማት ጋር አጣጥመው የሚገነቡ አንዳንድ ለማመን የሚከብዱ (የሚያስደንቁ) ብለው በጠሯቸው ባለ አምስት ኮከብ ሪዞርቶች ከተማዋን   በክልሉ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ፣ ብሎም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ እንደሆነ ነው የጠቆሙት:: በኮሪደር ልማቱ የከተማ አስተዳደሩ እና ሕዝቡ ምን ያህል እንደሚተሳሰቡ ያመላከተ ነው ሲሉም ተናግረዋል::

በቢሾፍቱ እንደ ጣና ሐይቅ ትላልቅ ባይሆኑም ሰባት ሐይቆች እንደሚገኙ የጠቆሙት ከንቲባው  ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በሐይቅ ልማት ዙሪያ ስለሚከናወኑ ልማቶች ልምድ መለዋወጣቸውን ተናግረዋል::

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ ወደ ባሕር ዳር ከተማ ከአምስት ዓመት በፊት መጥተው እንደነበር በመግለጽ አሁን ላይ  በኮሪደር እና በሐይቅ ዳር ልማቱ እየተለወጠች መሆኗን ተናግረዋል:: ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ልማት ላይ መሆኗን አረጋግጠናል:: የሚሠራው ልማት ለሀገር እና ለሕዝብ ነው፤ በመሆኑም በባለቤትነት ካልያዝነው እና ካልመራነው እንዲሁም ካልተንከባከብነው ዘላቂ አይሆንም:: ሕዝቡ የተሠራውን ልማት የራሱ ማድረግ አለበት:: ልማት የጋራ ነው፤ ትውልድ ተሻጋሪ  በመሆኑ የከተማው ማሕበረሰብ የሚሠሩ ልማቶችን በባለቤትነት መንፈስ እንዲጠብቅ አደራ” ብለዋል::

የተሻለች ከተማ ለመፍጠር ሥራዎችን እየሠራን ነው” ያሉት የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው እንደገለጹት ከተማዋ የተፈጥሮ ሀብቷን በሚያጎላ መልኩ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት ተመራጭ ከተማ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው:: ለውጡም ከቢሮ  እድሳት እንደተጀመረ ገልጸዋል:: በመቀጠልም የባሕር ዳር ከተማን የስማርት  ፕሮጀክት ጽ/ቤትን ማቋቋም  እና የዚህ ጽ/ቤት አካል የሆነውን የኮሪደር ልማቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here