የብቁ ወጣት መርሐ ግብር ተጀመረ

0
15

በተባሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና በማስተርካርድ ፋውንዴሽን የሚደገፍ በአማራ ልማት ማሕበር (አልማ) ተፈጻሚ የሚሆን ብቁ ወጣት የሚል መርሐ ግብር ተጀምሯል:: መርሐ ግብሩ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን የወደፊት ዕድል ለማሳደግ የሚያስችል ነው ተብሏል::

በዩኒሴፍ የአማራ ክልል ተወካይ አስተባባሪ ዶ/ር አምባነሽ ነጮ በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት መርሐ ግብሩ በግጭት በተጎዱት በአማራ፣ ትግራይ እና የአፋር ክልሎች ላይ የሚተገበር ይሆናል:: 59 በመቶ የሚሆነው ድርሻም ለአማራ ክልል የተመደበ ሲሆን 23 ወረዳዎች ላይ ለሦስት ዓመታት ተፈጻሚ የሚሆን ነው::

በሦስት ዓመቱ መርሐ ግብርም 67 ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው የተባለው:: ለአካል ጉዳተኞች እና ሴቶች ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጥም ነው የተገለጸው:: ለወጣቶቹ ስለ አዕምሮ ጤና እና ራሳቸውን በትምሕርት እና በሥራ ለማሰማራት የሚያስችል የአመለካከት ሥልጠና በመስጠት 25 ሺህ ለሚሆኑት የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው ተመላክቷል:: ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 የሆኑትን ደግሞ ወደ ትምሕርት ገበታ ለመመለስ ታስቧል::

ይህንን ሥራ ለማከናወንም ዐሥራ ሦስት ተቋማት ተሳታፊ ይሆናሉ:: የአማራ ልማት ማሕበር (አልማ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ መላኩ ፈንታ ማሕበሩ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እንደሚሠራ ጠቁመዋል፤ የብቁ ወጣት መርሐ ግብርም ከረጂ ድርጅቶች ጋር በትብብር ከሚሠሩ የማሕበሩ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል::

የልማት ማሕበሩ የራስን ችግር በራስ አቅም ለመፍታት የሚንቀሳቀስ ተቋም እንደሆነም ገልጸዋል።

‘’በትምህርት የተቀየረ እና ጤንነቱ የተጠበቀ ማኅበረሰብ ለሀገር ልማት ግንባታ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው’’ም ብለዋል። ለዚህም ማሕበሩ በትምህርት እና ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል::

በትብብር የማኅበረሰብ ችግርን ለመፍታት ከማኅበረሰቡ፣ ከመንግሥት እና ከረጂ ተቋማት ጋር እንደሚሠሩም አንስተዋል።

የብቁ ወጣት መርሐ ግብር ከረጂ ድርጅቶች ጋር ከሚሠሩ ተግባራት መካከል አንዱ ነውም ብለዋል:: ፕሮጀክቱን በሙሉ ተነሳሽነት እና ፍላጎት ለመተግበር ዝግጅት እንዳላቸውም ነው የገለጹት::

 

(ፍሬሕይወት አዘዘው)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here