የተማረ ዜጋ ለማፍራት በጋራ እንቁም!

0
9

ኢትዮጵያዊያን ለትምህርት ያላቸውን ልዩ ክብር ለመግለጽ “የተማረ  ሰው  ይግደለኝ”   ሲሉ  ይሰማሉ::   የተማረ ሰው ምክንያታዊ ፣   የሞራል እና የማሰብ ችሎታው ከፍተኛ  እንደሆነ ጽኑ እምነት አላቸው::

ኢትዮጵያዊያን ለትምህርት ከፍተኛ ክብርና ዋጋ ይሰጣሉ:: ምክንያቱም ትምህርት ሀገርን ለመገንባትም ሆነ ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ኑሮ፣ ሕይወትና ጤና እንዲሁም ምጣኔ ሃብትን ለማሻሻል  የሚረዳ የለውጥ አይነተኛ መሳሪያ በመሆኑ ነው::

ሰዎች የተደላደለ ኑሮ ለመኖር፣ ምቹ እና ዘላቄታዊ የአኗኗር ዘይቤያቸውን ለማረጋገጥ  የሚችሉት በመማር እና ዕውቀት በመቅሰም  ነው:: ትምህርት በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ገቢ ለማግገኘት፣ ጤናን ለመጠበቅ፣ ምርታማ ለመሆን … ዋናው መውጫ መንገድ ነው::

ሁሉም ሰው በምቾት መኖር፣  በቂ እና ቋሚ የሃብት ምንጭ፣ የተደላደለ እና ከስጋት ነጻ የሆነ ኑሮ ይፈልጋል:: ይህን ፍላጎቱን ለማሳካት ይቻል ዘንድ ደግሞ ዋና መሳሪያው ትምህርት ነው::

ከዚህ አንጻር ለትምህርት ትኩረት በመስጠት የተማረ ዜጋ ማፍራት ቀዳሚ  ተግባር ሆኖ እናገኘዋለን::ይሁን  እንጂ  ዛሬ  ላይ  ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን በማስተማር ለነገ ብሩህ ህይወታቸው መንገድ በመጥረግ ለሃገራችንም ሆነ ማህበረሰባችን ብቁ ሃኪም፣ በስነምግባር የታነጸ ዳኛ እና ጠበቃ፣ ታታሪ መንገድ ቀያሽ ፣ ትውልድ ቀራጭ መምህር፣ ካፒቴን … የማፍራት ሂደት በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት  መሰናክል ገጥሞታል::

ዘርፈ ብዙ የሙያ ባለቤቶችን ካላፈራን ሃገራችን ባልተማሩ ዜጎች የተከበበች፣ መዳረሻዋ የማይታወቅና በዓለም ዘንድ የተናቀች እና የተዋረደች  ልትሆን ትችላለች:: ይህን በማሰብ ሃገራችን  ከዚህ አይነት ችግር እና ዝቅታ  እንዳትወድቅ ከወዲሁ አሁን ያለውን ነባራዊ ችግር በመፍታት  ሁሉም ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ማገዝ የሁላችንም ሥራ ሊሆን ይገባዋል::

ወደ ትምህርት ቤት ባልሄዱ ልጆች ላይ የሚመጣው ዘርፈ ብዙ ችግር በእነሱ ላይ ብቻ የሚደርስ እና እነርሱን ብቻ የሚጎዳ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ችግሩ በቀጣይ መላ ህብረተሰቡን፣ ቤተሰብን እና ሃገሪቱ ላይ የሚደርስ  መሆኑን ተረድተን ለራሳችን  እና ለሃገራችን ስንል ለመፍትሄው በጋራ መሥራት አለብን::

ምክንያቱም የተማሩ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ለማህበረሰብ፣ ለአካባቢ እና ለሃገራቸው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ያገለግላሉ፤ የሥራ እድል ይፈጥራሉ፤ ይመራመራሉ፤ ሃገራቸውንም በዓለም ዘንድ የተሻለች፣ የበለጸገች እና የተከበረች ለማድረግ በርካታ ሥራወችን ያከናውናሉ:: የተማረ የሰው ኀይል የበዛባት ሃገር ሕዝብም አኗኗራቸው ምቹ፣ ገቢያቸው የላቀ፣ የተከበሩ እና በነጻነትና በድፍረት በየትኛዉም ዓለም የመንቀሳቀስ መብታቸው ያልተገደበ ሆኖ እናያቸዋለን::

የተማረ ማህበረሰብ በስነ ምግባር የታነጸ፣ ለስልጣኔ ቅርብ የሆነ፣ የሞራል ልዕልና ያለው፣ የዘመነ፣ ለሰዎች ክብር የሚሰጥ፣  ሀገሩንና ወገኑን የሚወድ፣ በባህሉ የሚኮራ፣ ባህሉንና እምነቱን ጠባቂ፣ የሌሎችን ማንነት የሚቀበል እና የሚያከብር ስለሆነ ከሁሉም ጋር ለመኖርም ሆነ ለመግባባት አይቸግረውም::

ታዲያ  እነዚህንና ሌሎች በርካታ ጸጋዎችን የሚያጎናጽፈውን ትምህርት ልጆቻችን እንዲማሩ  ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ  ጥቅሙና ክብሩ ለራስ ነው:: ስለሆነም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሂደው እንዲማሩ እናግዛቸው፤ ዳፋው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ  እኛው  ራስ ላይ አይወርድምና::

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here