የባሕር በር አልባ ሀገር ማለት ከውቅያኖስ ወይም ከባሕር ጋር የተገናኘ ግዛት የሌላት ሀገር እንደሆነ ብሪታኒካ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል:: የባሕር አልባ መሆን ደግሞ ከፍተኛ የመርከብ ወጪን እና ከውቅያኖስ የሚመጡ የምግብ ሀብቶች ውስንነትን ያስከትላል::
መረጃው እንዳስነበበው በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓ እና በደቡብ አሜሪካ 44 የባሕር በር ወይም ወደብ የሌላቸው ሀገሮች አሉ:: እነዚህ ሀገራት በሌሎች ሀገሮች የተከበቡ ናቸው፡፡
በመሆኑም እጣ ፋንታቸው በጎረቤቶቻቸው መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን እና የውጭ ግኑኝነታቸውን ውስብስብ እንደሚያደርግ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
የባሕር በር እና ወደብ አልባነት ሀገራትን ክፉኛ ይጎዳል፡፡ ስኬታማ የልማት ጉዞ እንዳይኖራቸው ያርጋል፡፡ የባሕር በር ባለቤትነት ለዓለም አቀፍ ትስስር እና ንግድ ወሳኝ ሲሆን በተቃራኒው አለመኖሩ ደግሞ ሀገራትን ወደ ኋላ ያስቀራል፤ እኩል ከሌሎች ሀገራት ጋር እንዳይራመዱ ያደርጋል፡፡
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት አብዛኛዎቹ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፤ ሀገራቱ የባሕር በር ካላቸው ሀገራት ጋር ሲነፃፀሩ ለዓለም አቀፍ የሸቀጣሸቀጥ ትራንስፖርት ከፍተኛ ወጪ ያወጣሉ::
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደብ የለሽ ሀገር ማለት የባሕር በር የተደራሽነት እጦት ብቻ ሳይሆን አንዲት ሀገር ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማስፋት እኩል እድል የላትም ማለት ነው፡፡ የባሕር በር አለመኖር በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ እና በፖለቲካ ትልቅ ኪሳራን ያደርሳል፡፡ ከፍተኛ የመጓጓዣ ወጪን እና የማጓጓዣ እጥረትን ያስከትላል፡፡ እንዲሁም ከዓለም ገበያ ያርቃል፡፡ ለጎረቤት ሀገራት ጥገኛም ያደርጋል፡፡
በአውሮፓ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወደብ የሌላቸው ሀገሮችን (አንዶራ፣ ኦስትሪያ፣ ሊችተንስታይን፣ ሉክሰምበርግ፣ ሳን ማሪኖ፣ ስዊዘርላንድ እና ቫቲካን ሲቲ) በምናይበት ጊዜ የበለጸጉ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ወደብ አልባ መሆን ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ እንደየሀገራቱ ይለያያል ማለት ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ወደብ አልባ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው ከጅምሩም ያደገ እና የበለጸገ ቢሆንም የባሕር በር አለመኖሩ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ በተለይም ፖለቲካዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ከሉክሰምበርግ (የኔቶ መስራች አባል ሀገር) በስተቀር ሌሎቹ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ገለልተኝነትን ይመርጣሉ:: ምክንያቱም እነዚህ ወደብ አልባ ሀገራት ለአንዱ መወገናቸው ወይም መቃረናቸው የባሕር በር ተጠቃሚነታቸውን ሊያሳጣ ይችላልና ነው፡፡
ከ44ቱ የባሕር በር ከሌላቸው የዓለም ሀገራት 32ቱ በአፍሪካ፣ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት የባሕር በር አልባ ታዳጊ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ (LLDCs) ተመድበዋል፡፡ ዝቅተኛው የሰው ልጅ ልማት ኢንዴክስ ደረጃ ካላቸው ዐሥራ ሁለቱ ሀገራት ዘጠኙ የባሕር በር አልባ ናቸው::
16ቱ የባሕር በር የሌላቸው የአፍሪካ ሀገራት ቦትስዋና፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ሌሴቶ፣ ማላዊ፣ ኒጀር፣ ኢስዋቲኒ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኒዊዝላንድ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ዙምባብዌ እና ቡሩንዲ ናቸው፡፡
በቆዳ ስፋት የባሕር በር የሌላት የዓለማችን ትልቋ ሀገር ካዛኪስታን ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የሚኖርባት የባሕር በር አልባ ሀገር ናት፡፡ ትንሿ ደግሞ ቫቲካን ሲቲ ናት፡፡
የባሕር በር ያላቸው ሀገራት ስልጣኔን የተላበሱ፣ ቱሪዝም የተስፋፋባቸው፣ የተለያዩ ባሕል እና ቋንቋ የሚስተናገድባቸው፣ የኪነጥበብ ሥራዎች የተስፋፉባቸው እና ከማንኛውም ጥገኝነት የተላቀቁ ናቸው፡፡ ለአብነትም እነ ዳካር፣ ጅቡቲ፣ ደርባን፣ ፍሎረንስ፣ ሲንጋፖር፣ ሮተርዳም እና ሞምባሳ፣ ቬኒስ የመሳሰሉ የወደብ ከተሞችን (seaport cities) መጥቀስ ይቻላል፡፡
እንደ አንክሎስ (unclos.org) መረጃ እ.አ.አ በ1982 ዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ (United Nations Convention on the Law of the Sea/UNCLOS) ስምምነት የጸደቀ ሲሆን 157 የዓለም ሀገሮች ተስማምተው የፈረሙበት ነው፡፡ ሕጉም የዓለም ሀገሮች የባሕር ክልልን እና ወሰንን በምን መንገድ መጠቀም እንደሚኖርባቸው ዝርዝር መሠረታዊ መርሆዎችን ያስቀመጠ ነው፡፡ እ.አ.አ በ1994 ደግሞ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የጠረፍንና የዓለም አቀፍ ውኃ ክልልን ምንነትና አጠቃቀም እንዲሁም በባሕር ወሰኖች ላይ የሚነሱ ውዝግቦችን አፈታት ሂደቶችን በዝርዝር ያሰፈረ ነው፡፡
በሕጉ መሠረት ወደብ የሌላቸው መንግሥታት የንግድ እና የኢኮኖሚ ልማትን ለማሳለጥ በአጎራባች የባሕር ዳርቻ ግዛቶች የመሸጋገር መብት አላቸው:: በዚሁ ስምምነት አንቀጽ 125 ላይ እንደሰፈረው የባሕር ላይ የመግባት እና የመውጣት መብትን ያረጋግጣል፡፡ አንቀጽ 127 ደግሞ የወደብ እና የመጓጓዣ መሠረተ ልማትን ጨምሮ የመሸጋገሪያ ነፃነትን ይደነግጋል፡፡
ሕጉ የባሕር በር ያላቸው ሀገራት አላስፈላጊ ገደቦችን ወይም ከልክ ያለፈ ታሪፍን እንዳይጥሉም ይገድባል፡፡
በዚህ ሕግ የሀገሮች የባሕር ክልል ላይ የትኛውም ሀገር ለሰላማዊ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ መተላለፊያ ሊከለከል አይችልም:: ሆኖም ሕጉ ብዙ ጊዜ ተግባራዊ ሲደረግ አይታይም፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየሦስት ዓመቱ ወደብ የሌላቸው ሀገራት ጉባኤን ያካሂዳል፡፡ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር (Augest5-8/2025) በቱርከሜኒስታን ከተማ (አዋዛ) ጉባኤው የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያም ተወካዮቿን በመላክ ተሳታፊ ነበረች፡፡
የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ቀጥተኛ የባሕር መተላለፊያ ባለማግኜታቸው ለከፍተኛ የትራንዚት (የመሸጋገሪያ) እና የትራንስፖርት ወጪ እየተዳረጉ ነው፡፡ እንዲሁም መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ አለመሟላታቸው ጉዞውን አድካሚ እና ፈታኝ እንዳደረገባቸው በጉባኤው ተመላክቷል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጉባኤው ላይ እንደተናገሩት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የሚደርስባቸው ተጽዕኖ ከባድ ነው፡፡ የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት ተሳትፎ የሚገድብ የንግድ ሥርዓት መሻሻል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሀገራቱ በዓለም ገበያ ለመሳተፍ ከፍተኛ ጫና እንዳለባቸውና ይህም ኢፍትሐዊነት እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡ “በቅኝ ግዛት እና በሌሎች ምክንያቶች ሀገራት ከባሕር በር እንዲርቁ ተደርገዋል”፣ ያሉት ዋና ጸሐፊው የባሕር በር የሌላቸው የባሕር በር ካላቸው ሀገራት ለማደግ እና ለመበልጸግ የበለጠ ልፋት እና ጥረት እንደሚጠይቃቸውም አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባልተገባ ጫና የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት ጎራ መደመሯን፣ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት የባሕር በር በማጣቷ በብዙ መንገድ መጎዳቷም በልዑካኗ አማካኝነት ተገልጿል፡፡ የውጭ ምንዛሬም ለባሕር በር ኪራይ ፈሰስ እንድታደርግ ተገዳለች፡፡ ለዓለም ገበያ በሚፈለገው መጠን ቅርብ እንዳትሆን አድርጓታል፡፡ የትራንዚት ወጪ በመጨመሩ ለዓለም አቀፉ ንግድ ተወዳዳሪ እንዳትሆንም እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ይህም ለዋጋ ግሽበት ሀገሪቱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ምርቶች በሚፈለገው ልክ ተደራሽ እንዳይሆኑ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር 60 ኪሎሜትር ባልበለጠ ርቀት ላይ መገኘቷን ልብ ይሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የዛሬ 30 ዓመታት ኢትዮጵያ የሁለት ወደብ ባለቤት ነበረች፤ ታዲያ ባልተገባ ውሳኔ የባሕር በሯን እንድታጣ ተደርጓል፡፡ እ.አ.አ በ2030 ደግሞ የሀገሪቱ ሕዝብ 150 ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህን ያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በር አልባ ሆኖ መኖር አይቻልም፡፡ የባሕር በር ጥያቄ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፤ የሕልውና ጉዳይ ነው” ሲሉ ነው ለተወካዮች ምክርቤት በአጽንኦት የተናገሩት፡፡ “ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና ለዘላለም ትኖራለች ብሎ የሚያስብ ካለ የሞተ ነው” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስፋት የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


