በአብዛኛው የሀገራችን ኪነ ጥበብ ብዙዎችን ብትጠቅምም ለሠሪዎቿ ግን ውለታ አትከፍልም:: ለዚህ ብዙ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ቢቻልም እንኳን ጥበብ ዋጋ እንድታወጣ የሚያደርጋት ስርዓት አለመዘርጋቱ ነው:: የቀደሞ ኪነ ጥበበኞች ዝና እና ስሜትን ተከትለው ሠርተዋል:: በውጤቱ ደግሞ በርካታ ሥራዎች ቢኖሯቸውም ደሀዎች እና የሰው እጅ ላይ የወደቁ ሆነዋል:: ገንዘብ መሥራት ላይ ትኩረት አልነበራቸውም።
የኔው አካሉ ደግሞ ከ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ በዜማ እና ግጥም ሥራዎቹ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አሻራ ያበረከተ የጥበብ ሰው ነው:: ሙዚቃ እሱ እንደዋለላት ውለታ አልከፈለችውም:: እንኳንስ ውለታ የላቡን እንኳን አልሰጠችውም::
የግጥም እና ዜማ ደራሲዎች እንደ ጥሩ ምግብ አብሳይ ባለሙያ ሴት ናቸው:: በጓዳ ከሰው ተነጥለው አስበው፣ አርግዘው፣ አምጠው፣ ወልደው ጥሩ አድርገው ያዳበሩትን ግጥም ወይም ዜማ ለድምጻዊያን ይሰጣሉ:: ዝነኞች ሆነው የሚታወቁበት ድምጻዊያን ናቸው:: የማን ዘፈን ነው ይባላል እንጂ የማን ዜማ ነው የሚል የለም::
የጓዳዋ ምግብ አብሳይ የሠራሽው ምግብ ይጣፍጣል የሚላት የለም:: አሳላፊዋ (እመቤቷ) ናት የምትወደስበት:: ግጥም እና ዜማ ላይም ደራሲዎቹ ይረሳሉ:: ዘፋኙ አደባባይ ላይ ይውላል፤ ከሰው ጋር ይገናኛል:: ከሥራ ዕድሎች እና ዓለም ጋር ይተዋወቃል:: የኔው አካሉ ባንድ ወቅት “ዘፋኝ እንጂ የሚታወቀው ደራሲ አይታወቅም” ሲል ተናግሮ ነበር::ዜማ ደራሲው ኪ ቦርድ ይዞ ሲደበድብ ውሎ ያድራል:: የዜማ ደራሲ አበበ መለሰ በአንድ ወቅት “የፀሐይ ብርሃን አይተን አናውቅም ነበር” ሲል መናገሩን አስታውሳለሁ:: ጉምቱው ግጥም እና ዜማ ደራሲ አበበ መለሰ ኩላሊቱን በታመመ ጊዜ ገንዘብ ከሕዝብ ተሰብስቦለት፤ ታክሟል::
የዛሬው የጥበብ ሰው ትኩረቴ የኔው አካሉ ነውና ወደ እሱ ልመለስ:: ዳንግላ ከተማ ነው የተወለደው:: ለወላጆቹ የመጨረሻ ልጅ ነው:: 11ዱም እህት እና ወንድሞቹ ሞተዋል:: ይህን በማሰብ የራሱን ብቸኝነት ታሪክ በሙዚቃ ለመግለጽ ፍቅርን ተጠቀመ።
በደርግ ዘመን ኬኔዲ መንገሻ እስከ 16 ዓመቱ ድረስ የኖረው አያቱ ባሻ መንገሻ ወልደ ሚካኤል ጋር ነበር:: ይህን ያደረገውም አባቱ አቶ አጥናፉ መንገሻ ዘመኑ ክፉ ነው ብለው እንደ ወላጅ በስርዓት ለማሳደግ የሚያደርጉበትን ቁጥጥር በመሸሽ ነበር:: ከአያቱ ጋር ጋር ሆኖ ከፍተኛ ኪነትን ተቀላቀለ:: ቀጥሎም የሙዚቃ ክበቦችን ተቀላቀለ:: አቶ ሳህለ ብርሃን የሶል ኩኩ ሙዚቃ ባለቤት ነበሩ:: እሳቸው ኬኒዲን ፈልገው አገኙት:: የኔው አካሉ እና ኬኔዲ በሶል ኩኩ ሙዚቃ ቤት አማካይነት ተጣመሩ።
በዚህ ሁኔታ ኬኔዲ የመጀመሪያውን አልበም ሰራ:: አባቱ እና አያቱ አንድ ነኝ ብሎ ሲዘፍን በደስታ አንብተዋል ይባላል:: ኬኔዲ በሙዚቃ ምክንያት ከወላጅ አባቱ ተነጥሎ አያቱ ጋር መኖሩ፣ በኋላም ሙዚቃ ውስጥ መቀጠሉ ቅሬታን ፈጥሯል:: ቤተሰቦቹ ብዙም ደስተኞች አልነበሩም:: አንድ ነኝ የሚለው የየኔው አካሉ ድርሰት የበለጠ ዝነኛ ሆነ:: ከራሱ ከዘፋኙ ታሪክ ጋር የሚገናኝ ነው የሚል ግምት በሙዚቃ አድማጮች ዘንድ ተሰማ:: ዳግም እህት እና ወንድም ነበረው፡፡
ምናልባት ኬኔዲ የተፈጠረበትን ስሜት ለማያያዝ ካልሞከረ በቀር እውነተኛው ታሪክ ግን የኔው አካሉ በሞት የተለዩትን እህት እና ወንድሞቹን ለማስታወስ የተጠቀመበት ነበር።
“አንድ ነኝ አጋር ዘመድ የለኝ
ትክሻ ሚሆነኝ አለሁህ የሚለኝ
አልጸናም ሆዴም አይጠብቅልኝ
ፍቅሬም ተለየችኝ ሁለት ያጣ ሆንሁኝ”
ብሎ በኀዘን ስሜት አንጎራጎረ::ሕዝቡ ከኬኔዲ ከወላጆቹ ተለይቶ መኖር ጋር አገናኘው:: በኋላም ሐምሌ 25 ቀን 1985 ዓ.ም ኬኔዲ በ29 ዓመቱ ድንገት መለየቱ በሕዝብ ልብ ውስጥ የትካዜ ስሜትን ፈጠረ::ኬኔዲ ደግ፣ በሄደበት የሚውል፣ ለነገ የማይል፣ በራሱ ሕግ የሚኖር ወጣት ነበር።
የኔው አካሉ ከ3 ሺህ በላይ ዜማዎችን መሥራቱን በተለያዩ ቃለመጠይቆች ተናግሯል::
በልጅነቱ የኔው በጎጃም ክፍለ ሀገር የፖሊስ ክበብ ሙዚቃ ይሠራ ነበር:: በኋላም ግሽ አባይ ኪነት ገብቶ ነበር:: ተወዛዋዥም ነበር:: በአዲስ አበባ የፖሊስ ኦርኬስትራን ተቀላቅሎም ሰርቷል:: በኋላ በግሉ የዜማ እና ግጥም ስራዎችን በመስራት ተወዳጅነትን አግኝቷል:: በኋላ ወደ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቶ ተምሯል:: የኔው አካሉ ከበርካታ ድምጻዊያን ጋር ሰርቷል።
ጋሻው አዳል፣ አስናቀ ገብረየስ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ሐመልማል አባተ፣ ተፈራ ነጋሽ፣ ተስፋዬ ወርቅነህ፣ ይሁኔ በላይ፣ ጌቴ አንለይ፣ ፋሲል ደሞዝ፣ ማን አልሞሽ ዲቦ፣ አሸብር በላይ፣ ታደሰ ዓለሙ፣ አያሌው መስፍን፣ መስፍን አበበ፣ ካሳሁን ታዬ፣ ገነት ማስረሻ፣ ሰርጉ ዓለም ተገኝ፣ ተሾመ ወልዴ፣ በእውቀቱ ሰው መሆን፣ ደረጄ ደገፋው፣ ዚነት ሙሀባ፣ ማርታ አሻጋሪ፣ ዳምጠው አየለ፣ መሰሉ ፋንታሁን፣ አክሊሉ ስዩም፣ ሀብተሚካኤል ደምሴ፣ ግዛቸው ተሾመ፣ ብጽዓት ስዩም፣ ቻላቸው አሸናፊ፣ እና ሌሎች መቶ የሚደርሱ ድምጻዊያን ጋር ሠርቷል:: ከሙሉቀን መለሰ ጋር ብሰራ ኖሮ ብሎ በጣም ይቆጫል::
የኔው አካሉ የመሥራቱን ያህል አይደለም:: እንደ ልፋቱ እና ድካሙ ጉልበቱ የኢኮኖሚ ፍሬ አላፈራም:: መኖሪ ቤት አልሠራም:: ምቹ መስሪያ ቦታ የለውም:: ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ነው:: ምቹ ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ከዚህ የበለጠ መሥራት ይችል ነበር:: ነገር ግን የፈጠራ አቅሙ ምቾቶ በማጣት ተገድቧል:: በሕይወት ለመቆየት በሚቸገርበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል:: የቅርብም የሩቅም፤ የሀገር ውስጥ እና ውጪ ሰዎች እየደገፉት ለመኖር ተገዷል::
የዜማ ሥራ ክፉ ምጥ ነው:: ረጂም ጊዜ መቀመጥን የሚጠይቅም ነው:: “48 ሰዓት ሁሉ የማልነሳበት ሰዓት አለ:: አንዱ ሲመጣ አንዱ ሲተካ፣ አንዱ ሲመጣ አንዱ ሲተካ፣ እዛው ላይ ሁሉ ሰው ላለ ማስቀየም ስትል በዛው ላይ ታድራለህ እና ያለ እድሜ የሚያስረጅ ስራ ነው::
በቃ ምግብ አይታይህ:: ምን ሌላ ነገር አይታይም:: ስራ ላይ ከገባሁ አልጀምረውም እንጂ ከጀመርኩኝ ወጣ ማለት የለም::ዘፋኝ እየተቀያየረ እና በዚህ ላይ ስታይሉን ስታጠና፣ ምን አይነት ዜማ ነው የምሰራለት ለሱ ስትል በጣም… ረቀቅ ያለ ነው ወደ እኛ ህይወት ስንመጣ” ሲል ምን ያህል በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ረጂም ሠዓታትን በዜማ ሥራ እንደሚያሳልፍ ተናግሯል::
የኪነ ጥበብ ሰው ስሜት አሳዳጅ ነው:: ገንዘብን ለማሰብ ይቸገራል መሰለኝ:: በተለይ ባለፈው ዘመን የነበሩ የጥበብ ሰዎች ለራሳቸው ሀብት እና ለልጆቻቸው ጥሪት አላጠራቀሙም:: ለጥበብ ራሳቸውን አሳልፈው በባርነት ይሰጣሉ:: ያች ጥበብ ደግሞ ባሪያ እንጂ ንጉሥ ልታደርጋቸው አትፈቅድም:: ጥበብ ፈጣሪዋን አታከብርም:: የሚተውነውን ታከብራለች:: የኔው ከሚፈጥሩት ተርታ ነው:: ማፍለቅ፣ ማሰብ፣ መብሰልስ፣ መመሰጥ ነው የተሰጠው:: በዚያም የሚጠበቅበትን ሠርቷል::
አሁን የመጡ የጥበብ ሰዎች ጥበብን ይጠቀሙባታል:: ንጉሥ ይሆኑባታል እንጂ እነሱን ባሪያ አድርጋ አትነግስባቸው:: ኪነ ጥበብን በዋጋ ይተምኗታል:: አንድ ነገር ላይ ግትር ብለው አይቀመጡም:: ይህ በመሆኑ ብዙ አማራጮችን ያሳድዳሉ:: ሕይወታቸው ብዙ ምርጫ አለው::
ሙዚቃን የነፍስ ጥሪየ ብለው ልሙት አይሉም:: ካላዋጣቸው ዘወር ይላሉ:: እየቸገራቸው አይሠሩም:: አምስት ፊልም የሰራች ሴት 50 ዓመት ዜማ ከሰራው ሰው ባላይ ሀብታም ናት፤ ዝነኛ ናት:: የተሻለ ሕይወት ትኖራለች:: ግን የጥበብ ስራ ፍሬው የት ነው የሚለው ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ጥራት እና ኪነ ጥበባዊ ፈጠራ በገንዘብ ሲተመን አደጋ ነው:: ሁሉ ነገር ወደ ገበያ መቅረቡ ስጋት ነው:: ግን አንዳንዶቹ እንደ የኔው አካሉ ዓይነት ሰዎች የጥበብን የእዳ ቀንበር ተሸክመው ነፍስ ያለው ሥራን መስጠታቸው አይካድም::
1400 የሙዚቃ ግጥም የጻፈው ጸጋየ ደቦጭም ባለፈው ጊዜ ለሰዎች እርዳታ እጁን ዘርግቶ ነበር:: 3 ሺህ ዜማ የሰራው የኔው አካሉም ከዚህ የተለየ እጣ አልገጠመውም:: በተለይም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ እድሜያቸውን ያሳለፉ ቀደምት ኪነ ጥበበኞች ኑሯቸው አሳዛኝ ነው:: ዝና ሰማይ ሁብት ምድር ሆኖ በጣም ይቸገራሉ:: ብዙዎች ዝናቸው አሳፍሯቸው በቤታቸው ከመቸገር ጋር ይኖራሉ:: የክብር ዘበኛው ሙዚቃ አቀናባሪ ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ አሟሟት የከፋ ነበር:: የዜማ ጎተራው ተዘራ ኃይለ ሚካኤል ችግር አስከፊ ነበር:: ኧረ ብዙው የኪነ ጥበብ ሰው አስቸጋሪ ሕይወት ነው የሚያሳልፈው:: ምኒልክ ወስናቸው እና ጥላሁን ገሰሰን በታመሙበት ወቅት ያሳከሟቸው ሼህ ሙሀመድ አሊ አላሙዲን ናቸው::
“የ40 ቀን እድል ልበልህ:: እኔን እንደሚመስለኝ ከሆነ ሳንቲም ምናምን የሚባል ነገር ለኛ አይታየንም:: የኛ መከፋት ለአንዳንድ ሰው እንጀራ ይሆናል ልበል? በጣም አስቸጋሪ ነው” ይላል የኔው አካሉ ስለ ድህነቱ ሲናገር::
ኪነ ጥበብ ለዝና እና ለስሜት የምትፈጠርበት እና የምትከወንበት ዘመን አብቅቷል:: አሁን ጊዜው የገበያ ነው:: ገበያ ደግሞ ስርዓት ይፈልጋል:: ቀድሞ ለዝና የሚያንጎራጉርን በመንግሥት ቤት የሚዘፍን ጥበበኛ በደመወዝ ማስተዳደር ይቻል ነበር:: ቀጥሎ የንግድ ሙዚቃ ቤቶች መጡ:: ካሴት ከድምጻዊያን እየገዙ እነሱ ሀብት ፈጥረዋል:: ኪነጥበበኛው ግን አልተለወጠም:: ቀጥሎ ሲዲ መጣ::
ከዚያ ደግሞ ሙዚቃ አየር ላይ ቆመች:: አሁን ዩቱዩብ የሚባል ቴክኖሎጂ መጥቶ እውቀት እና መረዳት ያላቸው ጥበበኞች ብቻ እየተጠቀሙበት ነው:: አሁን የሚቀርቡ ግጥም እና ዜማዎችን መመልክት የፈጠራ ድርቅ የገባ መሆኑን ያሳያል:: ርግጥ ጎበዝ ሰዎች አሉ:: ጥሩ ይሠራሉ:: ግን በውጤት ሲታይ የድሮ ዜማዎችን መገልበጥ እና መቅዳት ነው የተጀመረው:: ሙዚቃ አሁን እናት እና አባት የሌለው ልጅ ሆናለች:: ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሙዚቃ ገበያ ስርዓት መዘርጋት አለበት:: የኔው አካሉ አንድ ነኝ እንዳለው አሁን ሙዚቃ ብቻዋን ናት:: የኔውም ብቻውን ነው:: ለሙዚቃ ካልደረስንላት ሌሎች የኔው አካሉን ማፍራታችን አይቀርም::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


