አባ ቆስቁስ

0
14

ዲፕሎማት፣ ደራሲ እና ፈላስፋ ነበሩ። በአድዋ እና በማይጨው ጦርነት ውጊያ አውድማ ላይ  ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በማማከርም ትልቅ ውለታ ውለዋል፤ ራሳቸውም ጦራቸውን መርተው ተዋግተዋል፤ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ (አባ ቆስቁስ)። ቼኮስሎቫኪያዊው ተጓዥ እና የታሪክ ተመራማሪ አዶልፍ ፓርለሳክ አማካሪያቸው ነበር:: የሀበሻ ጀብዱ በተሰኘው መጽሐፉ ስለእኚህ ታላቅ ሰው በሰፊው ተርኳል:: በወቅቱ ከዐፄ ኃይለሥላሴ ቀጥሎ ትልቁ ስልጣን የእሳቸው እደነበረም ገልጿል:: ዕውቀትን ፈላጊ፣ ብቁ ዳኛ፣ ጀግና የጦር መሪ፣ ደራሲ እና ጥሩ አባት እና ባል እንደነበሩም አሳይቷል::

ራስ ካሳ በወሎ ክፍለሀገር በላስታ ምድር ሙጃ 1873 ዓ.ም ነበር የተወለዱት። ታላቅ ስብዕናን የተላበሱ የሹም ልጅ ሹም፣ በቤተክህነት ሥርዓት ያደጉ እና የተማሩ የሀገረ-መንግሥት ዕውቀትን ገና በጧቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደኪሮስ እግር ስር የተማሩ ናቸው። ከዐፄ ምኒልክ አጎት ራስ ዳርጌ በኋላም በዐፄ ምኒልክ ቤት ገብተው ዕውቀትን ከባህሩ የጨለፉ ናቸው። ልዑል ራስ ካሳ አስተዋይና ብልሃተኛ መሪ ሲሆኑ መንፈሳዊውን ዓለም ከዓለማዊው ጋር አጣምረው መጓዛቸው አጀብ ሳያሰኝ አልቀረም።

ልዑሉ የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅት ከዱበር እስከ መተማ ያለውን ግዛት አስተዳድረዋል። እንኳን ሰው እግር ይጋጫል እና የጠቅላይ ግዛቱ ነዋሪዎች ፍርድ እንዳይጓደልባቸው እና በዳይና ተበዳይ ቂም ቋጥሮ እርስ በእርሱ እንዳይጫረስ መዝገብ ይዘው ዳኝነት የተቀመጡ ናቸው።

ምዕራባዊያን ቀኝ ገዢ ሀገራት አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሲከፋፈሉ በፋሺስት ጣሊያን መዳፍ ገብታ የመመተር እጣ የደረሳት ኢትዮጵያ ነበረች። በወቅቱ ማለትም 1888 ዓ.ም “ወረኢሉ ከተህ ባላገኝህ ማሪያምን አልምርህም ” የሚለው የዐፄ ምኒልክ አዋጅ ከጫፍ ጫፍ ሲያስተጋባ የጦር ነጋሪቱን ጎስመው የሀገሪቱን የከፍተኛው ጦር ይዘው የዘመቱት እኒሁ ራስ ካሳ ኃይሉ ስለመሆናቸው የታሪክ መዛግብቶች ይመስክራሉ።

ታሪክን በትክክል ሰንዶ የማስቀመጥ ልምዳችን ደካማ በመሆኑ ብዙ ማህደሮችን ለማጣቀስ አስቸጋሪ ቢሆንም በወቅቱ ገና በ15 ዓመታቸው በወርሃ መስከረም 1888 ዓ.ም በአድዋ ጦርነት ላይ በተንቤን ጦር ግንባር ዘምተው በልዑል ራስ ስዩም ሥር ሆነው የተዋጉ ብላቴና ነበሩ። ራስ ካሳ ኃይሉ ዋና አዛዥ በመሆን በዚህ ጦርነት ሲዘምቱ በኮሎኔል አዲቫ የተጻፈው ቀይ አምበሳ ከ45 ሺ እስከ 50 ሺህ የሚደርስ የጦር ሰራዊት ይዘው መዝመታቸውን ያነሳል።

የልዑሉ ዋና የጦር አማካሪ ሆኖ የዘመተው አዶልፍ ፓርለሳክ የሀበሻ ጀብዱ መጽሐፍ ከ150 ሺህ በላይ የጦር ሰራዊት ይዘው መዝመታቸውን የሚያትት ሲሆን በሌላ በኩል ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ቀዩ አምበሳን በሚደግፍ መልኩ ከ45 እስከ 50 ሺህ የጦር ሠራዊት ይዘው መዝመታቸው ላይ ይስማማሉ።

በሁለተኛው የማይጨው ጦርነት ወቅት ራስ ካሳ ኃይሉ ሀገራቸውን ከጠላት መንጋጋ ለማስጣል ሲሉ በጦር ዋና አዛዥነት ከቀዳማዊ ዐፄ ኀይለሥላሴ ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው በመሆን መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም የጦር ሠራዊቱን ብቻ ሳይሆን ሦስት ወንድ ልጆቻቸውን ማለትም ደጃች ወንድወሰን ካሳ፣ ደጃች አበራ ካሳ፣ ደጃች አስፋወሰን ካሳን ጨምረው ነበር የዘመቱት። በዚህ የአምስቱ ዓመት ጦርነት ፓልዋሪና ቀጨም መልፋ በተባለ ቦታ የካቲት 11 ቀን 1928 ከጠላት ጋር ውጊያ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ትጥቁ በሌለበት የጣሊያንን የ40 ዓመት የበቀል ጦር ዝግጅት ባደረገበት ራስ ካሳ ባላቸው ዕውቀት ተጠቅመው ጦሩን ለመከላከል ችለዋል። ይሁን እንጂ በጦር ሚኒስትሩ እና በጦሩ ዋና አዛዥ መካከል በተፈጠረ ችግር እና አለመግባባት የተነሳ በአምባራዶ ጦርነት ላይ ሚንስትሩ ራስ ሙሉጌታና ልጃቸው እያፈገፈጉ ሳለ ህይወታቸው አልፏል። በዚህ ጦርነት ከኢትዮጵያ ከ275 ሺህ በላይ ተዋጊ ሲገደል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ጦረኛ ቆስሎሏል። ከፋሽስቱ ጣሊያን በኩል 208 ሺህ ወታደር ሙትና ቁስለኛ ሆኗል።

ራስ ካሳ ከጣሊያን ጀት በሚዘንበው የእሳት ነበልባል ወታደሮቻቸውን ላለማስፈጀት በተጠቀሙት ታክቲክ ከጦር ድብደባው ተርፈው ከዐፄ ኃይለሥላሴ ጦር ጋር መደባለቅ ችለዋል። ይሁን እንጂ ደጃዝማቾቹ ልጆቻቸው በአዲስአበባ በመሸገውና 3000 ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ሀኔታ በጨፈጨፈው ፋሽስት ላይ ጥቃት ያደረሱ ሲሆን ሁለቱ ወንድማማቾች ደጃዝማች አስፋወሰን እና ደጃዝማች አበራ በጣሊያን የጦር ሰራዊት ተይዘው ሲገደሉ ወንድማቸው ደጃዝማች ወንደሰን ካሳ ወደላስታ ሸሽቶ ከፋሽስቱ እየታገለ ባለበት ወቅት በላሊበላ ጥራሪ በተሰኘ ወንዝ ላይ እንደተሰዋ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። የዐፄ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያና የህይወቴ እርምጃ በተሰኘው ቁጥር 1 መጽሐፋቸው ላይ በ1928ቱ የኢትዮ-ጣሊያን ጦርነት ራስ ካሳ በአቢያዳና በአርባወያኔ ድል ማስመዝገባቸውን መስክረውላቸዋል።

ልዑል ራስ ካሳ በእስከ መጨረሻ ሚጣቅ ሚካኤል የሚባል ቦታ እንደሄዱ በኀዳር 7 ቀን 1949 በድንገት ሳይታሰብ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ለቀብራቸው ሥነ ስርዓት ከላስታ እጅግ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ሰው ወደ ሸዋ እንደሄደ ይነገራል። የቀብር ሥነስርዓቱ ሕዝብ በብዛት በተሰበሰበበት በታላቅ ክብር በፊልድ ማርሻል ማዕረግ ተፈጽሞ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቀበሩ። ልዑል ራስ ካሳ ክብራቸውን የሚጠብቁ፣ የረጉ፣ ሰጥ ያሉ፣ ምክር አዋቂ፣ የአገር ባህልና አስተዳደር ጠንቅቀው የተረዱ ስለነበሩ አስተያየታቸው ሁሉ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው ነበር። ቦረናና ሳይንትን ጨምሮ፣ ሰላሌን፣ ላስታን በከፊል ራያን፣ በጌምድርን ወዘተ በተለያየ ጊዜ በገዥነትና በጠቅላይ ገዥነት አስተዳድረዋል።

አልፈርድ ፓርላሳክ በመጽሐፉ በአስቀመጣቸው ታሪኮች የኢትዮጵያ ጦር በሁለተኛው የኢትዮ ጣሊያን ጦርነት ጊዜያዊ ሽንፈት እንደደረሰበት መረዳት ይቻላል:: ለአብነት ፓርላሳክ እንዲህ ሲል ይተርካል፡- “በየቀኑ የተለያዩ ሹሞች ጦራቸውን እየያዙ ወደ ራስ ካሳ ይመጣሉ፤…የራስ ካሳ ጦር በየቀኑ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱ፣ ወንዝ ስንሻገር ወይም ጠባብ መንገድ ላይ ስንደርስ ትርምስ ይፈጠር ጀመር፤ ሹማምንቱም የእኔ ጦር መጀመሪያ ይለፍ በሚል ሰጣ ገባ ውስጥ ይገባሉ:: ወደ ራስ ካሳ ኃይሉ እልፍኝ ሄጄ እንዲህ አይነት ችግሮች ዳግም እዳይፈጠሩ ዘዴ እንዳለኝ እና ለዚህም የሠራዊቱን ቁጥር ያውቁ እንደሆነ ጠየኳቸው:: በሀሳቡ ተደሰቱ ቁጥሩን ግን እንደማያውቁ ነገሩኝ:: “ይሄንማ ቀኝአዝማች አበበ ነው የሚያውቀው፤ እሱን ጠይቀው አሉኝ”::

ቀኝ አዝማች አበበ በድንኳናቸው ተቀምጠው ከሁለት ሹማምንት ጋር ጠጅ እየጠጡ ይጫወታሉ:: ምን እንደሚያወሩ ባይሰማም ሳቃቸው ከሩቅ ይሰማል:: አሽከራቸው በፍጥነት ዋንጫ አምጥቶ ጠጅ ቀዳልኝ:: የተቀዳልኝን ጨልጬ የመጣሁበትን ላስረዳ ስዘጋጅ አሽከሩ በፍጥነት መጥቶ ዋንጫውን በጠጅ ሞላው:: የመጣሁበትን ጉዳይ ገልጬ የሠራዊቱን ቁጥር በትክክል እንዲነግሩኝ ቀኝ አዝማች አበበን አጥብቄ ጠየኩ:: ቀኝ አዝማች አበበ ጥያቄዬን ወደ ጎን ትተው ከወር በኋላ አስመራ ስንገባ እውነተኛውን የጣሊያን ቪኖ እንደሚጋብዙኝ ደጋግመው ቃል ገቡልኝ::

ሦስተኛ ዋንጫዬን እንደያዝኩ በድጋሚ ጥያቄዬን አምርሬ አቀረብኩ:: አሁን ቀኝ አዝማች አበበ በመገረም እያዩኝ “የወታደሮቹን ቁጥር ነው ያልከኝ? እሱንማ እግዜሩ ነው የሚያውቀው፤ እዚህ ማንም አያውቀው” አሉኝ:: ለካስ እንኳን አጠቃላዩን ሹሙ በሙሉ ያመጣውን ጦር ይቅርና ራሳቸው ያመጡትን የሠራዊት ቁጥር በግምትም ቢሆን አያውቁትም:: እናም አለማወቃቸውን ለመሸፈን ያክል “ጌታዬ መድፈኛ ጦርም እኮ አለን” አሉኝ:: በጣም ገረመኝ፤ አንድ ሳምንት ከጦሩ ጋር ስጓዝ እንኳን መድፍ ላይ መድፍ የመሰለ ብረት እንኳ አላየሁም እና እንደመሳቅ ሲቃጣኝ:: ቀኝ አዝማች አበበ ተቆጥተው “ተመልከት ጌታው!” በማለት  ከድንኳኗ ጀርባ በጨርቅ የተሸፈነ ነገር አሳዩኝ፤ መድፍ የመሰለ ነገር እና ብዙ ቁርጥራጭ ብረቶች ተደርድረዋል::

አሁን ሳቄን አፈን አደረኩ፤ ቀኝ አዝማችን ላስከፋቸው አልፈለኩም፤ ብረቶቹን ሳይ ሙዚየም መቀመጥ የነበረባቸው እና ከ40 ዓመታት በፊት በአድዋ ጦርነት በዐፄ ምኒልክ ሠራዊት ከጣሊያኖች የተማረኩ አሮጌ መድፎች እና ቁርጥራጮች ናቸው…እና ይሄው ነው አልኳቸው፤ “ለጊዜው ሁለት መድፍ ብቻ ቢኖረንም ከጣሊያኖች እንማርካልን” አሉኝ በወኔ::… በኋላ የጦሩን ቁጥር በግምት ሠርቼ አቀረብኩ:: ከራስ ካሳ ውጪ የቁጥሩ አስፈላጊነት እቁብ የሰጠው የለም:: ራስ ካሳ ግን መረጃዋን በጥንቃቄ አስቀመጧት:: በዚህ ሁኔታ ነው የእኛ ጦር እጅግ የተደራጀውን እና እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያን ጦር የሚገጥመው”…::

ከላይ ያየነው የፓርላሳክ ትረካ ራስ ካሳ ከሌሎች ሹማምንቶች የተለየ መረዳት እና አዲስ ነገር የመቀበል እና የማወቅ ጉጉት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው:: ሁሉም ሹማምንት እና የጦር መሪዎች እንደ ራስ ካሳ አዲስ ነገር የመቀበል እና የመመርመር ልማድ ቢያዳብሩ ኖሮ ጦርነቱ በኢትዮጵያዊያን የበላይነት ይደመደም እንደነበር ፓርላሳክ በተዘዋዋሪም ቢሆን ገልጿል::

ሳምንቱ በታሪክ

ቀ.ኃ.ሥ ነገሡ

ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ቀዳማዊ ተብለው የነገሡበት ሳምንት ነው።

በኢትዮጵያ፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በድንገተኛ ሞት ከአለፉ በኋላ አልጋ ወራሹ ንጉሥ ተፈሪ መኮንን ተተክተው በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የንጉሠ ነገሥትነት ዘውድ ጭነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተባሉ።

በንግሥ  በዓሉ  ዋዜማ  ጥቅምት 22  ቀን የትልቁ ንጉሠ-ነገሥት የዳግማዊ  ዐፄ  ምኒልክ  ሐውልት  በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን አጠገብ ፤ ለዘውድ በዓል የመጡት እንግዶች በተገኙበት ሥርዓት፣ የሐውልቱን መጋረጃ የመግለጥ ክብር ለብሪታንያ ንጉሥ ወኪል ለ(ዱክ ኦፍ ግሎስተር) ተሰጥቶ ሐውልቱ ተመረቀ።

ለንግሥ ስርዓቱ ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ ሀገር ልኡካን ከየሀገራቸው ጋዜጠኞች ጋር ከጥቅምት 8 ቀን ጀምሮ በየተራ ወደ አዲስ አበባ ገብተው ስለነበር ሥርዓቱ በዓለም ዜና ማሰራጫ በየሀገሩ ታይቶ ነበር። በተለይም በብሪታንያ ቅኝ ግዛት በጃማይካ አንዳንድ ድሀ ጥቁር ሕዝቦች ስለ ማዕረጋቸው ተረድተው የተመለሰ መሢህ ነው ብለው ይሰብኩ ጀመር። እንደዚህ የሚሉት ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ፊተኛው ስማቸው «ራስ ተፈሪ» ትዝታ ራሳቸውን ራሰተፈሪያውያን ብለዋል።

ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውድ እንደጫኑ የሀገሪቱን የመጀመሪያ ሕገ-መንግሥት እንዲዘጋጅ  አዝዘው በዘውዱ አንደኛ ዓመት በዓል ጥቅምት 23 ቀን 1924 ዓ.ም. በአዲሱ ምክር ቤት (ፓርላማ) ለሕዝብ ቀረበ። ከዚህም በላይ ብዙ የቴክኖሎጂ ሥራዎች እና መሻሻያዎች ወደ ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር አስገቡ።

አንዋር ሳዳት

ጥቅምት 17 ቀን 1971 ዓ.ም – ሦስተኛው የግብጽ ፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ሜናኽም ቤጊን የዓመቱ የኖቤል የሠላም ሽልማት ተሸላሚዎች መሆናቸው ይፋ ሆነ።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here