አፍሪካውያንን ያገናኘው – ጣና ፎረም

0
17

መነሻውን ከአማራ ክልል ሰከላ ወረዳ ያደርጋል፤ የተለያዩ ወንዞችን እየጠቀለለ እና ኅይሉን እያጎለበት ወደ ጣና ሃይቅ ይገባል፡፡ ፍሰቱ ግን ጣና ሃይቅ ላይ የሚቆም አይደለም፤  ቁልቁል በመንደርደር ከ11 በላይ የአፍሪካ ሀገራትን በፍሰቱ ያረሰርሳል፤ ለለምለሚቷ አፍሪካም አቅም ሆኖ የመጨረሻ መዳረሻውን ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ያቆማል፡፡

በዓባይ ወንዝ የተጋመደው አፍሪካዊ ግንኙነት በመንግሥታት መካከልም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጣና ፎረም ሚያዚያ 2004 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡ የአፍሪካውያን መድረክ የሆነው ፎረሙ መሰባሰቢያውን ብዙ የአፍሪካ ሀገራትን በሚያዋስነው ዓባይ እንዲሁም የዓባይ ወንዝ እና ጣና ሃይቅ ህብር በሚፈጥሩባት ባሕር ዳር አድርጓል፡፡  በተለያዩ ውኃማ አካላት የታየው ሕብር በአፍሪካውያንም ዘንድ ጎልብቶ ኀያሏን አህጉር ለመገንባት አፍሪካውያን ጉባይተኞች በየዓመቱ በባሕር ዳር እየተገኙ ይመክራሉ፡፡

ጉባኤው ከምስረታው ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም በፎረምነቱ ሲቀጥል፤ ከ2008 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ጣና ፋውንዴሽን በሚል ቀጥሎ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ ጉባኤው ከመድረክነት አልፎ ፖሊሲዎችን እና በጉባኤው የሚነሱ ሀሳቦችን ለማስፈፀም የገንዘብ አቅም እንዲኖረው ለማስቻል የስያሜ ለውጥ ተደርጎበት እንደነበርም ታሪካዊ ሂደቱ ያሳያል፡፡ ከዚያ በኋላም ወደ ፎረምነቱ ተመልሷል፡፡

ፎረሙ የአፍሪካ ሀገራት መልክ እስኪመስሉ ድረስ በተደጋጋሚ የሚስተዋሉትን ግጭት፣ ስደት፣ ሞት፣ መፈናቀል እና ድህነት ገርሰሶ ሰላም የሰፈነባት፣ ዕድገቷ የተረጋገጠ እና ተወዳዳሪ አህጉርን መፍጠርን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ ፎረሙ የምክረ ሀሳብ ጉባዔ ሲሆን የወሳኝነት ሚና ግን  የለውም፡፡ ለዚህም በአህጉሪቱ የሚከሰቱ የሰላም፣ የደህንነት እና የአካባቢያዊ ትስስር እጦትን በማጥናት፣ ክርክሮችን በማዘጋጀት እና የሚደረስባቸውንም መደምደሚያዎች ለውሳኔ ሰጪ አካላት እና ለአፍሪካ መሪዎች ያቀርባል፡፡

ፎረሙ በእስካሁን ጉዞው በሽብርተኝነት፣ በአፍሪካ የንግድ ትስስር፣ በአፍሪካ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ የፋይናንስ አቅም ማጎልበት በሚቻልባቸው እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡ በጸጥታ ችግሮች እና በሌሎችም ምክያቶች ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ጉባኤውን ያላካሄደው ፎረሙ ዘንድሮ 11ኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ አፍሪካውያን ስለ አህጉራዊ ጉዳዮቻቸው ከጥቅምት 14 እስከ 16/2018 ዓ.ም   በመክሩበት ጉባኤ መገናኛቸውን ለፎረሙ መነሻ በሆነው ጣና ሃይቅ መገኛ፣ ዘንባባን መለያዋ ባደረገችው፣ በኮሪደር ልማት ውበቷ ይበልጥ እየተገለጠች በመጣችው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በ2015 እ.ኤ.አ የትምህርት ከተማነት ዕውቅና በሰጣት ባሕርዳር ከተማ መክፈቻውን አድርገዋል፡፡

“አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት ውስጥ” በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄደው መድረክ የሁለት ቀናት የማጠቃለያ ቆይታውን በአዲስ አበባ ከተማ አድርጓል፡፡ በመድረኩም የተለያዩ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒሥትሮች፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ የአፍሪካን ጉዳይ ርዕሰ ጉዳያቸው ያደረጉ የፖለቲካ አካላት እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጣና ፎረም አህጉራዊ አጀንዳዎችን በጋራ በመምከር ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ  ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እና ባሕር ዳር ከተማን  የቱሪዝም ከተማነቷን ይበልጥ የሚያስመሰክር ሁነት መሆኑንም ያስታወቁት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ናቸው፡፡ ከንቲባው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ ከተማዋ የጣና ፎረምን ጨምሮ ትልልቅ ሁነቶችን ያለምንም የጸጥታ ችግር እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ የጣና ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ እና በአፍሪካ አንድነት ዙሪያ እንዳሳየችው በጐ ተነሳሽነት ሁሉ የሚታይ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ይህም በቀጣናው እና በአህጉሩ ኢትዮጵያ ጐልታ እንድትታይ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት በር ይከፍታል፡፡

በዓለም የኢኮኖሚ ፖለቲካ ውስጥ የዓባይ ወይም በዓለም አቀፍ ስያሜው የናይል ወንዝ ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ዓባይን ከ11 በላይ የአፍሪካ ሀገራት ይጋሩታል፡፡ ፎረሙ በየዓመቱ በምንጩ መገኛ በሆነው አማራ ክልል መካሄዱ ለምርምር እና ቱሪዝም ተጨማሪ ዕድልን ይፈጥራሉ የሚሉ አካላትም አልታጡም፡፡

ጉባኤው አፍሪካ ለሚገጥሟት ችግሮች በሀሳብ ፍጭት መፍትሔዎችን ማፈላለግ ዓላማው ባደረገው እና 11ኛ መድረኩን በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደበት ወቅት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ንግግራቸውን ጣና ፎረም አፍሪካ በተለዋዋጭው ዓለም የሚመጡ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የምትችልበትን መፍትሔ ለማፍለቅ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አፍሪካ ከቀሪው ዓለም ጋር እኩል ለመራመድ በጋራ የምትመክርበት፣ የአህጉሯን የሰላም እና ብልጽግና መንገድ የምትተልምበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አፉሪካ ያሏትን ጸጋዎች ለመጠቀም የሚያስችሉ መፍትሔዎች ጭምር የሚንሸራሸሩበት መድረክ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ ትኩስ ጉልበት የሚገኝባት፤ የታሪክ፣ የባሕል፣ የእሴት፣ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መሆኗን ለጸጋዋ ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡ እነዚህን ጸጋዎች አቀናጅቶ ለማልማት የፎረሙ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው የጣና ፎረም በየዓመቱ በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ መድረኩ ግልጽ ውይይቶች የሚበረታቱበት፣ ሐሳብ በነጻነት የሚያንሸራሸርበት መሆኑ ለአፍሪካ አፍሪካዊ መፍትሔዎች እንዲበረታቱ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

ፎረሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ ቢቆይም ሁሌም በየዓመቱ በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ መክፈቻውን በባሕር ዳር አድርጎ ሁለቱን ቀናት በአዲስ አበባ መክሯል፡፡ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ምሁራን እና መሪዎች እንዲሁም የሌሎች ሀገራት የሚሳተፉበት ፎረም ለኢትዮጵያ  እና ለአፍሪካ ምን ፋይዳ እንደሚኖረው አምባሳደር ነብያት አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ቁልፍ ሚና የምትጫወት ሀገር ናት፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአፍሪካ ሕብረት ሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት አባል መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ጥቅሟ ተነስታ  ለአህጉራዊ ሰላም እና መረጋጋት የራሷን አቋም እንድታራምድ ዕድል የሚሰጣት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ አፍሪካ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም የሚኖራትን አቋም የሚወስን መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከአነሳሱ ጀምሮ የአፍሪካን ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች አጀንዳ ያደረገው ፎረሙ፤ አፍሪካዊ መፍትሔዎችን እና  የሰላም ሐሳቦችንም በማፍለቅ ለተረጋጋች አህጉር መፈጠር የበኩሉን ሚና የሚወጣ  መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከትብብር ይልቅ ፉክክር በበዛበት ዓለም ውስጥ እንደ አህጉር በጋራ ማራመድ የሚገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አቋሞች ምን መምሰል እንዳለባቸው ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡  ፎረሙ የሚመክርባቸው እና ድምዳሜ ላይ የሚደርስባቸው የሰላም እና ጸጥታ አጀንዳዎች እንዲሁም ሌሎችም ጉዳዮች በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሮ አዲስ አበባ የተቋጨው ፎረም አፍሪካ በኢኮኖሚ እንዴት ራሷን መቻል አለባት? ምን ዓይነት እርምጃዎች ያስፈልጋሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በዚህም በአፍሪካ ያሉ ወጣቶችን እና ሴቶችን ጨምሮ አካታች ሥርዓት መዘርጋት ለነገ የሚባሉ ጉዳዮች እንዳልሆኑ ምክክር ተካሂዶበታል።

የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እና የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ በፎረሙ መዝጊያ ላይ እንዳሉት 11ኛው የጣና ከፍተኛ የሰላም እና ጸጥታ ፎረም ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል። የፎረሙ መሪ ሀሳብ አፍሪካ በተለዋዋጩ ዓለም ሥርዓት እንደ አህጉር ልንነጋገርበት የሚገባ ወቅቱን የጠበቀ ጽንሰ ሀሳብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ጆይሴ ባንዳ ”በአሁኑ ወቅት ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር፣ የተፈጥሮ ሀብትን በፍትሐዊነት እና ዘላቂነት ተደራሽ ማድረግ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። ዓለም በፍጥነት እየተለወጠች መሆኑን አስታውሰው፤ አፍሪካም እየተለወጠ ላለው የዓለም ሥርዓት የሚመጥን እንቅስቃሴ ማድረግ አለባት፤ ለዚህ ደግሞ በጣና ፎረም የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ከአፍሪካ ሀገራት በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቃል” በማለት አስገንዝበዋል፡፡

አፍሪካ ለማሳካት ያስቀመጠቻቸው ውጥኖች ያለ ወጣቶች ተሳትፎ እውን ሊሆን እንደማይችል አመልክተው፤ በአፍሪካ በሁሉም መስክ የሚከናወኑ ተግባራት ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

 

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here