የአፍሪካውያንን ችግሮች በአፍሪካውያን…

0
13

የጣና የምክክር መድረክ (ጣና ፎረም) የተመሠረተው ሚያዝያ 2004 ዓ.ም ነበር፤ በዓባይ ወንዝ የተጋመደው አፍሪካዊ ግንኙነት በመንግሥታት መካከልም ተጠናክሮ ይቀጥል  ዘንድ፡፡ የአፍሪካውያን መድረክ የሆነው የምክክር መድረኩ መሰባሰቢያውን ብዙ የአፍሪካ ሀገራትን በሚያዋስነው ዓባይ እንዲሁም የዓባይ ወንዝ እና ጣና ሐይቅ ህብር በሚፈጥሩባት ባሕር ዳር ከተማ አድርጓል፡፡  በተለያዩ ውኃማ አካላት የታየው ሕብር በአፍሪካዉያንም ዘንድ ጎልብቶ ኃያሏን አህጉር አፍሪካን ለመገንባት አፍሪካውያን ጉባኤተኞች በየዓመቱ በባሕር ዳር እየተገኙ ይመክራሉ፡፡

የምክክር መድረኩ ከምስረታው ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም በ”ፎረም”ነቱ ሲቀጥል፣ ከ2008 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ጣና ፋውንዴሽን በሚል ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ጉባኤዉ ፖሊሲዎችን እና በጉባኤው የሚነሱ ሀሳቦችን ለማስፈፀም የገንዘብ አቅም እንዲኖረው ለማስቻል የስያሜ ለውጥ ተደርጎበት እንደነበርም ታሪካዊ ሂደቱ ያሳያል፤ ከዚያ በኋላም ወደ “ፎረም”ነቱ ተመልሷል፡፡

ጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት መለያ እስኪመስሉ ድረስ በተደጋጋሚ የሚስተዋሉትን ግጭቶች፣ ስደት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ድህነት… ገርሰሶ ሰላም የሰፈነባት፣ ዕድገቷ የተረጋገጠ እና ተወዳዳሪ አህጉርን መፍጠርን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡

ጉባኤው ይህን የገዘፈ ዓላማ ያነገበ ይሁን እንጂ፣ ምክረ ሃሳብ ከማቅረብ ባለፈ የወሳኝነት ሚና  የለውም፡፡ ለዚህም በአህጉሪቱ የሚከሰቱ የሰላም፣ የደህንነት፣ የአካባቢያዊ ትስስር… እጦትን በማጥናት፣ ክርክሮችን በማዘጋጀት እና የሚደረስባቸውንም መደምደሚዎችም ለውሳኔ ሰጪ አካላት እና ለአፍሪካ መሪዎች ያቀርባል፡፡

የምክክር መድረኩ (ፎረሙ) በእስካሁን ጉዞው በሽብርተኝነት፣ በአፍሪካ የንግድ ትስስር፣ በአፍሪካ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ የፋይናንስ አቅም ማጎልበት በሚቻልባቸው እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

በጸጥታ ችግሮች እና በሌሎችም ምክያቶች ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ጉባኤውን ያላካሄደው የምክክር መድረኩ ዘንድሮ 11ኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡

“አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት ውስጥ” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው የምክክር መድረክ የተለያዩ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ የአፍሪካን ጉዳይ ጉዳያቸው ያደረጉ የፖለቲካ አካላት ተገኝተውበታል፡፡

የምክክር መድረኩ በአህጉራዊ ጉዳዮች  በጋራ በመምከር የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እና ባሕርዳር ከተማችንን  የቱሪዝም ከተማነቷን ይበልጥ የሚያስመሰክር ሁነት ነው፡፡

የጣና የምክክር ጉባኤ በኢትዮጵያ መካሄድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ እና በአፍሪካ አንድነት ዙሪያ እንዳሳየችው  ተነሳሽነት በጋራ ጉዳዮች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአህጉሩ  ጐልታ እንድትታይ ሊያደርግ የሚችል፣ ለቱሪዝም እና ልማት በር  የሚከፍት ነው፡፡ ጉባኤው በየዓመቱ በአማራ ክልል መካሄዱ ለምርምር ዕድል እንደሚፈጥርም ይታመናል፡፡ አፍሪካ በተለዋዋጩ ዓለም የሚመጡ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የምትችልበትን መፍትሄ ለማፍለቅ የሚጫወተው ሚናም ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ከዚህም ባሻገር አፍሪካ ከቀሪው ዓለም ጋር እኩል ለመራመድ በጋራ የምትመክርበት፣ የአህጉሯን የሰላም እና ብልጽግና መንገድ የምትተልምበት፣ ያሏትን ጸጋዎች አቀናጅታ በማልማት ለመጠቀም የሚያስችሉ  መፍትሄዎች ጭምር የሚንሸራሸሩበት መድረክ ነው፡፡  አፍሪካ ከፍተኛ ትኩስ ጉልበት የሚገኝባት፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የእሴት፣ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ናት፡፡ እነዚህን ጸጋዎች አቀናጅቶ ለማልማት ጉባኤው  ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

መድረኩ ግልጽ ውይይቶች የሚበረታቱበት፣ ሀሳብ በነጻነት የሚያንሸራሸርበት ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ለአፍሪካ አፍሪካዊ መፍትሄዎች እንዲበረታቱ ዕድል ይሰጣል፡፡

ጉባኤው  የሚመክርባቸው እና ድምዳሜ ላይ የሚደርስባቸው የሰላም፣ የጸጥታ እንዲሁም የልማት ጉዳዮች በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ለሚሠሩ ሥራዎች ትልቅ ግብዓት ይሆናል፡፡ ከትብብር ይልቅ ፉክክር በበዛበት ዓለም ውስጥ አፍሪካውያን በጋራ ጉዳዮች እየመከሩ በጋራ መሥራታቸው፣  የአፍሪካን ችግሮችን በአፍሪካውያን በጋራ የመፍታት ጥረታቸው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here