የውል እርሻ ለምርታማነት የላቀ ሚና አለው

0
21

የውል እርሻ ለምርታማነት እንዲሁም ለአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት የላቀ ሚና እንዳለው ተገለጸ፤ የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር “በግብርና ውል አርሻ” አሠራር ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በውል እርሻ  እየተሳተፉ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል መለሰ ሙሐባው አንዱ ናቸው። አምራቹ ለአራት ዓመታት ያህል በውል እርሻ መሬት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸውልናል። በዚህም ለእርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በወቅቱ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በሄክታር የሚገኘው ምርትም እንዲያድግ አድርጓል፤ ከምርት በኋላ ደግሞ በወቅቱ ምርቱን ማስረከብ እንዲችሉ ዕድል እንደፈጠረላቸው ነው የገለጹት። በ2017/18 የምርት ዘመንም 20 ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ቦሎቄ እና ማሾ በውል እርሻ መሬት እያመረቱ ነው።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) የግብርና የውል እርሻ በኢትዮጵያ የቆየ አሠራር እንደሆነ ገልጸዋል፤ ይሁን እንጂ በሕግ ማዕቀፍ ባለመታገዙ በአሠራር ሂደቱ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል ብለዋል። ችግሩን ለመፍታትም ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የውል እርሻ አዋጅን በማጽደቅ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት አዋጁ የአርሶ አደሮችን ምርታማነት እንዲያሳድጉ አድርጓል፤ አስመጪ እና ላኪዎች የሚፈልጉትን ምርት በጥራት እና በተፈለገው ጊዜ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል።  ለኢንዱስትሪዎችም ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ እያገዘ ነው።

የውል እርሻ ከሰብል እና ከሰብል ልማት (ሆርቲ ካልቸር) ባለፈ የተፈጥሮ እና የእንስሳት ሃብቶችን እንደሚያካትትም ገልጸዋል። አሠራሩን እስከ ታች ድረስ ማስተዋወቅ ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) የግብርናው ዘርፍ በባሕላዊ አሠራርም ቢሆን ከሀገራዊ ጥቅል ምርት 32 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ ባሕላዊውን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል። እየሠራቸው ከሚገኙ ሥራዎች ውስጥም በውል እርሻ አሠራር ምርታማነትን ማሳደግ አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የሚያመርቱትን ምርት ከመካፈል ወጥተው እሴት ጨምረው ለገበያ  እንዲያቀርቡ ማድረግ የቀጣይ ትኩረት መሆኑንም ተናግረዋል። የውል እርሻ አሠራርን የማስፋት ተግባርም ሌላኛው የቀጣይ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here