አብዮት የሚያስፈልገዉ ውድድር

0
6

የኢትዮጵያ ስም በዓለም አደባባይ ሲነሳ ከአድዋ ድል በተጨማሪ አብሮ የሚነሳው የማይናወጠው የአትሌቲክስ ገናናነቷ ነው። በዓለም አቀፍ ታላላቅ መድረኮች ያሸበረቁ  እና ክብረወሰኖችን የሰባበሩ ጀግና አትሌቶች የወለደች ምድር ናት-ኢትዮጵያ። በሻምበል አበበ ቢቂላ የድል ችቦ የተቀጣጠለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ  በኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በቀነኒሳ በቀለ፣ በጥሩነሽ ዲባባ  እና  ስፍር ቁጥር በሌላቸው ልጆቿ ኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ሯጮች ሀገር መሆኗን በተደጋጋሚ አስመስክራለች። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዘርፉ አሳሳቢ ችግር መታየት ጀምሯል። ኢትዮጵያውያን ለዓመታት የለመዱት የድል ዜና በተለይም በዋና ዋናዎቹ የዓለም መድረኮች ላይ መደብዘዝ ከጀመረ ቆይቷል።

ለችግሩ ማሳያ ከሆኑት  መካከል በቅርቡ የተካሄደው  የቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ተጠቃሽ ነው። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት እና ከሚጠበቅባት የሜዳሊያ ብዛት እና ጥራት አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገቧ አይዘነጋም። ቀደም ባሉት ዘመናት በበርካታ የረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ መድረኩን ሙሉ በሙሉ በበላይነት የሚቆጣጠሩት ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ በጎረቤት ሀገር ኬኒያ የበላይነቱ ተወስዶባቸዋል::

ይህ ክስተት ጊዜያዊ የብቃት መውረድ ነው? ወይስ ስር የሰደደ ሥርዓታዊ ችግር ምልክት ነው? የሚለውን ብዙዎች እንዲጠይቁ ያስገድዳል። ለዘርፉ  ውድቀት አንዱ ምክንያት በሀገር ውስጥ ያለው የአትሌቲክስ ውድድር ሥርዓት ዛሬም ኋላቀር መሆኑን  በተንታ የአትሌቲክስ ማዕከል አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ታምራት ታደሰ ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉበት ቆይታ ተናግረዋል::

ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ እና ጠንካራ ልምምድ ብቻውን በቂ በማይሆንበት በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚወዳደሩበት የሀገር ውስጥ መድረክ አሁንም ድረስ ባህላዊ እና ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የታጋዘ አለመሆኑ ይነገራል:: ይህ ታዲያ ሀገራችንን  ለውድቀት እየዳረጋት መሆኑን የአትሌቲክስ አሰልጣኙ አቶ ታምራት ይናገራል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስን ከባህላዊ አሠራር ወደ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ማሸጋገር ስሟ በገዘፈበት በዓለም ታላላቅ መድረኮች የጠፋውን ውጤት ለመመለስ እና ለቀጣይ ትውልድ የማይናወጥ መሠረት ለመጣል ያስችላልም ብሏል ባለሙያው።

የ2025 የቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤት እንደሚያሳየን ጥንካሬ እና ጽናት ብቻ ውድድሮችን ለማሸነፍ ዋስትና እናደማይሆን ነው። ዛሬ ላይ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚወሰኑት በሽርፍራፊ ሴኮንዶች፣ በሚሊሜትር ልዩነቶች እና ብልሀት በተሞላበት ስልታዊ አሯሯጥ ነው። በሀገራችን አብዛኞቹ የአትሌቲክስ ውድድሮች የሰዓት አያያዝ አሁንም ድረስ በእጅ በሚያዝ የሩጫ ሰዓት (Stopwatch) ላይ የተመሠረተ መሆኑን አሰልጣኙ ያስረዳል። ይህም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በሴኮንድ እና በማይክሮ ሴኮንዶች ለሚወሰን ትንቅንቅ የሚያስፈልገውን ሥነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ዝግጁነት አትሌቶች ሊያዳብሩ አይችልም።

በተመሳሳይ በዝላይ እና በውርወራ ውድድሮች ላይም የሚሠራበት የመለኪያ ቴፕ አጠቃቀም ለአትሌቱ ትክክለኛ ብቃቱ ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ መረጃ እንደማይሰጥም የዘርፉ አሰልጣኝ ይናገራል። ይህ ችግር በአትሌቶች መካከል ፍትሐዊ ውድድር እንዳይኖር ከማድረጉም ባሻገር አትሌቶች በራሳቸው ብቃት ላይ ያላቸውን እምነት ይሸረሽረዋል። ይህ ደግሞ ቀጥተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድረው በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በሚኖራቸው የራስ መተማመን ላይ ነው ተብሏል።

ዘመናዊ ውድድር ማለት የተመልካቹን ስሜት የሚይዝ  በአስደናቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የታጀበ እና ለአትሌቱም ሆነ ለተመልካቹ አስደሳች ስሜት የሚፈጥር መሆን እንዳለበት የኦሎምፒክ ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል። በሀገራችን ስታዲየሞች ውስጥ ያለው ድባብ ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው። ግዙፍ የውጤት ማሳያ ሰሌዳዎች የሉም፤ የድምፅ ሥርዓት ጥራትም ዝቅተኛ  ነው:: ይህ ደግሞ አትሌቶች በከፍተኛ ጫና እና በተመልካች ግፊት ውስጥ የመወዳደር ልምድን እንዳያዳብሩ ያደርጋቸዋል።

ትክክለኛ የውጤት ምዝገባን ለማረጋገጥ የፎቶ-ፊኒሽ ካሜራዎች እና ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የሚሠራ የሰዓት አያያዝ ሥርዓት (Fully Automatic Timing System) መዘርጋት ከዘመኑ ጋር እኩል ለመጓዝ ያስፈልጋል ተብሏል:: ለሜዳ ተግባራት በተለይም ለዝላይ እና ውርወራ ውድድሮች የኤሌክትሮኒክስ ርቀት መለኪያ መሣሪያዎችን (EDM) መጠቀም ያስፈልጋል ብሏል ባለሙያው:: በተጨማሪም የንፋስ ፍጥነት መለኪያ (Anemometer) ለአጭር ርቀት ሩጫዎች እና ለዝላይ ውድድሮች የሚመዘገቡ ክብረ ወሰኖች ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖራቸው ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ታምራት ይጠቅሳል።

በዓለም አቀፍ መድረክ በ80 ሺህ ተመልካች ፊት የሚወዳደር አትሌት በሀገሩ ውስጥ ተመሳሳይ ባይሆንም እንኳ ተቀራራቢ የሆነ የውድድር ስሜትን እና ጫናን ተላምዶ መሄድ እንደሚኖርበት በተንታ የአትሌቲክስ ማዕከል አሰልጣኝ የሆነው አቶ ታምራት ያምናል። በዘርፉ አሁን ያለው የውድድር  ስርዓት ጥንካሬ (Competitive Toughness) ዓለም ከደረሰበት የውድድር ስርዓት የተራራቀ እንደሆነም አሰልጣኙ ይናገራል:: እናም በአትሌቲክስ ስፖርት የኢትዮጵያ ውጤት ማሽቆልቆል የእነዚህ ሁሉ  ጉድለቶች ጥርቅም መሆኑን ባለሙያው አልሸሸገም ።

ችግሩን ለማስተካከልም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቤት ሥራውን መስራት እንዳለበት ባለሙያው ይናገራል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የተደረገውን የቶኪዮ  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትልቅ የማንቂያ ደወል መሆኑን አቶ ታምራት ታደሰ ያስታውሳል:: የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ካለው ኋላቀር አሠራር ወጥቶ በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ዘመናዊ አሠራሮች ላይ ማተኮር ይገበዋልም ነው ያለው:: ታዲያ ይህን ለማከናወን ግልጽ፣ ተጨባጭ እና የጊዜ ገደብ የተቆረጠለት የረጅም  እና የአጭር ጊዜ ዕቅድ ማዘጋጀት ለነገ የማይባል ተግባር ነው።  ዕቅዱን ለማሳካትም ፌዴሬሽኑ በቂ በጀት መመደብ እና አጠቃቀሙ ግልጽ እና ተጠያቂነትን ያሰፈነ መሆኑን  ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል- አቶ ታምራት።

አሰልጣኞች እና ዳኞች ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ውጤት የሚወሰንባቸውን ጥቃቅን የሕግ እና የቴክኒክ ጉዳዮችን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል። ታዲያ ለዳኞች፣ ለቴክኒክ ባለሙያዎች እና ለውድድር አዘጋጆች ተከታታይ እና ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ ነው። ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ  (World Athletics) እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የልምድ ልውውጥ እና የሥልጠና መርሀግብሮችን በማዘጋጀት የባለሙያዎችን አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግም ሌላው የፌዴሬሸኑ ተግባር መሆን እንዳለበት የአትሌቲክስ አሰልጣኙ ያስረዳል።

የመሮጫ መሞች፣ የአትሌቶችን ፍጥነት የሚለኩ እና ከጉዳት የሚከላከሉም መሆን ይኖርባቸዋል። ለሜዳ ተግባራት ስፖርቶችም ደረጃቸውን የጠበቁ እና ለአትሌቶች ምቹ መሆን አለባቸው። ከዚህ ባለፈ መወዳደሪያ ስፍራዎች  ለተመልካቾች ምቹ መቀመጫ፣ ንጹሕ መጸዳጃ ቤቶች እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን ያሟሉ መሆን አለባቸው። ለአትሌቶች ደግሞ ዘመናዊ የልብስ መቀየሪያ፣ የመታጠቢያ እና የማገገሚያ ክፍሎች ሊኖሯቸው ይገባል።

የአትሌቲክስን ወድድር ወደ ዘመናዊ ለመቀየር ከፌዴሬሽኑ ባለፈ የሌሎች የባለድርሻ አካላት እገዛን ይጠይቃል። በተለይም ግዙፍ ድርጅቶች በገንዘብ እና በቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አቶ ታምራት ይናገራል:: አሊያ ግን የምንኮራበትን ታሪክ በትዝታነት ብቻ እንድናስታውሰው ከመዳረግ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here