የሀሰት ዜና   የልፋት ውጤትን ሲያስቀር መና

0
10

በፖላንድ ፖድካርፒሲ ግዛት የደብሮይካ ቀጣና ኗሪ በያዝነው ዓመት ያመረተውን ሁለት ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የድንች ምርት  ገዥ አጥቷል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ በነፃ እንደሚሰጥ በተሰራጨ የሀሰት መልእክት በአካባቢው ኗሪዎች በአንድ ቀን አዳር መወሰዱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት አስነብቧል::

በማህበራዊ ሚዲያ የተለጠፈውን የሀሰት መልእክት የተከታተሉ፣ ከተከታተሉት የሰሙ የአካባቢው ኗሪዎች የቻሉ በተሽከርካሪ ያልቻሉ በሸክም አግዘው ወስደውበታል::

አምራቹ  አቶፒዮትር ግሪታ እሁድ በቤተሰብ ጉዳይ በአጐራባች ቀጣና ውሎ ሰኞ አመሻሽ ምርቱን በጊዚያዊነት ወደ ከመረበት ቦታ ይደርሳል … “ያየሁትን ማመን አልቻልኩም፤ በ68 ዓመት ዕድሜዬ ይህን የመሰለ ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም፤ በድረጊቱ የተሳተፉ አንዳንዶች መጥተው አነጋግረውኛል፤ በሰላም ችግሩን ብንፈታ ጥሩ ነው አሊያ ግን ጉዳዩን ወደ ህግ አቀርባለሁ::” የሚል መልእክት አስተላልፏል::

አምራቹ እንዳሉት ከፊሎቹ በኬሻ ተሽክመው፣ ከፊሎቹ በተሽከርካሪ ጭነው እየተመላለሱ መውሰዳቸውን ለማወቅ ችለዋል::

ይህ ሲሆን በቀጣናው ከሚኖሩ ሰዎች አንድም የማን ነው? ለምንድን ነው የምትወስዱት? ብሎ የጠየቀ እና ድርጊቱን ለማስቆም የሞከረ አለመኖሩ እንዳሳዘናቸውም ነው ያሰመሩበት::

ባለንብረቱ ከደብሮይካ ድንቹ ከሚገኝበት ቀጣና ጥቂት ራቅ ብሎ የቤተሰብ ግብዥ ስነስርዓት ላይ እንደነበሩ እና በማግስቱ ምርታቸውን ባኖሩበት ሲደርሱ ሙሉ በሙሉ መወሰዱን ተመልክተው ጉዳዩን ለህግ ሊያቀርቡ ነው መባሉ ታዛቢዎችን ግራ አጋብቷል፤ ጥርጣሬም አስነስቷል::

አንዳንድ ታዛቢዎችም የድንች ዋጋ ከሚጠበቀው በታች በመውረዱ ግለሰቡ “ከመድን ካሳ ለማግኘት አውቀው፣ ሆን ብለው የፈጠሩት መላ ነው” የሚል አስተያየት መሰንዘራቸውን በማጠቃለያነት አስነብቧል- ድረ ገጹ::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here