በደቡብ ምስራቅ አውሮፓ ክሮሺያ ውስጥ የሚገኝ ጥንታዊ እና በስፋቱ ከቀዳሚዎቹ ረድፍ ተጠቃሽ ነው- የፕሊቪስ ኃይቆች ብሔራዊ ፓርክ፡፡ ስፋቱ 297 ኪሎሜትር ስኩዌር ወይም 73,350 ሄክታር ተለክቷል፡፡ በፓርኩ ቀጣና የሚገኙት ኃይቆች ከጠቅላላ ስፋቱ ሁለት በመቶ ይሸፍናሉ፡፡
ለፓርኩ አስደናቂነትን ያላበሱ 16 የስፋት መጠናቸው የተለያዩ አንዱ ከሌላው ከፍ ካለ ቀጣና ወደ ዝቅተኛው የሚወርድ ፏፏቴ ያላቸው ኃይቆች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ፓርኩ በ1949 እ.አ.አ በሀገሪቱ የመጀመሪያ ፓርክ መሆኑ ቢታወጅም በዓለም አቀፍ የአካባቢ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በቅርስነት የተመዘገበው በ1979 እ.አ.አ ነው፡፡
ፓርኩ ለጐብኚዎች ዓመቱን ሙሉ ክፍት ሲሆን ወደ ፓርኩ የሚያመሩ ሰባት መንገዶች እና ውስጥ ለውስጥ ተዘዋውሮ መመልከቻ በጣውላ የተዘጋጁ መረማመጃዎች አሉት፡፡
በፓርኩ 1400 የእፅዋት ፣ 160 የዓዕዋፍ እና 300 የቢራ ቢሮ ዝርያዎች መኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ በአካል ከገዘፉ የዱር እንስሳት 50 የሚሆኑ ቡናማ ድቦች እና ሦስት የተኩላ መንጋዎችን አስጠልሏል፡፡
በቀጣናው የሚገኙ የድቦች ግልገሎች ቁጥራቸው እንዳይቀንስ በ “ጂፒኤስ” ክትትል እንደሚደረግባቸውም ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡
ለፕሊቪስ ብሔራዊ ፓርክ መፈጠር የኖራ ዓለት የሚበዛበት አቀበት ከአቀበቱ፣ የሚነሱ ምንጮች እና ቁልቁል የሚፈሱ ፏፏቴዎች ዋነኛ መሰረቶች ናቸው፡፡
በፓርኩ ውስጥ ምንም አይነት ማረፊያ ስለሌለ ሌሊት ማዳሪያ እንዲሁም እሳት ማቀጣጠል በጥብቅ የተከለከለ ነው፤ አይመከርምም፡፡
የፕሊቪስ ኃይቆች ብሔራዊ ፓርክ ሰባት ነጥብ 24 የሳቢነት ደረጃ አግኝቶ በዓለም ላይ ካሉ ውብ ብሔራዊ ፓርኮች በአምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ድረገፆች አስነብበዋል፡፡
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ክሮሺ ያ ዶት ኤች አር፣ ኢንሳይት ቫኬሽን ድረገጽ እና ኤንፒ- ፕሊቪካ- ጀዚራ ድረገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


