ኅብረት ሥራ ማህበራት ሰዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እንዲሁም በተናጠል መፍታት የማይችሏቸውን ችግሮች በጋራ የሚፈቱባቸው ተቋማት ናቸው:: ማህበራት አገልግሎት ሰጭ እና አምራች በመሆናቸው የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገትም ያፋጥናሉ:: ስያሜያቸውን ያገኙትም ከተግባራቸው እንደሆነ የአማራ ክልል ኀብረት ሥራ ማህበራት የሕግ ባለሙያ ወ/ሮ አልማዝ ካሳ ተናግረዋል::
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት የሚቋቋሙትን ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለማጠናከርም የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 985/2009 አንቀጽ 76 ንኡስ አንቀፅ (3) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ተቋቁሟል:: የአማራ ክልል በ2017 መመሪያውን አሻሽሎ ”የአማራ ክልል ኀብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ 220/2017 አዋጅ”ን አጽድቆ ወደ ተግባር ገብቷል::
በክልሉ በ2017 ዓ.ም የተሻሻለው አዋጅ የአገልግሎት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የኢንዱስትሪ፣ የእደጥበብ፣ የሸማቾች፣ የአሳ አስጋሪዎች… ተደራጅቶ አገልግሎት መስጠትን እና ማምረትን ያጠቃልላል::
ማህበራት የሚመሰረቱት የተለያዬ ዓላማን አንግበው ነው ያሉት ባለሙያዋ፤ ሰዎች በተናጠል መፍታት የማይችሉትን ችግር በጋራ ሆነው ለመፍታት፣ አባላት ያላቸውን ገንዘብ፣ ጉልበት እና ዕውቀት አቀናጅተው የተሻለ ውጤት ለማግኘት እንደሆነ ጠቁመዋል:: ለምሳሌ ሸማች ማህበራት ግብዓትን ለአባላት ለማከፋፈል፣ አምራች ሲሆኑ ደግሞ ምርታቸውን ለማህበራቸው ሲሸጡ ተመጣጣኝ ዋጋ ያገኛሉ::
ሌላው የማህበራት ዓላማ የብድር እና ቁጠባ አገልግሎት ለመስጠት ሲባል በተለይ የባንክ አገልግሎት በስፋት በሌለባቸው የገጠር አካባቢዎች እና በከተሞች የቤት ፕላን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማስያዝ መበደር ለማይችለው የመንግስት ሠራተኛ እና አርሶ አደሮች የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል ነው:: በጠቅላላው አባላት በግል ቢሠሩ የሚደርሰውን ኪሳራ በመቀነስ በጋራ መምራት እንዲሁም ሰዎችን ማስተማር እና ማሠልጠንን አዓማ አድርገው የሚያከናውኑት ተግባር መሆኑን ባለሙያዋ አብራርተዋል::
ማኀበራት የሚመሩባቸው መርሆዎች
የሕብረት ሥራ ማህበር አባላት በዘር ፣ በሃይማኖት እና በፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይፈጥሩ በፍቃደኝነት ላይ የሚመሰረት ተቋም ነው::
እያንዳንዱ አባል አንድ ድምጽ ብቻ ይኖረዋል፤ ይህ ማለት እንደ ድርጅት ብዙ እጣ የገዛ ሰው የመወሰን ሥልጣን የለውም፤ ሁሉም አባል እኩል አንድ ድምጽ ብቻ በመያዝ በጋራ ድምጹ አመራሩን ይመርጣል:: ኀብረት ሥራ ማህበራት ትርፍ ክፍፍል ያደርጋሉ፤ ካገኙት ትርፍ ላይ ወጫቸው ተሰልቶ ከወጭ የቀረው ትርፉ 30 ከመቶ ለመጠባበቂያ፤ 70 ከመቶው ለአባላት ይከፋፈላል::
የራስ ገዝ ባህሪያቸውን ሳይለቁ ከሌሎች አቻ ማህበራት ጋር ስምምነት ማድረግ ይችላሉ::
ለሠራተኞቻቸው ትምህርት እና ሥልጠና ይሠጣሉ፤ በዚህም ከሌሎች አቻ ማህበራት ጋር ኅብረት መፍጠር ይችላሉ::
ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘላቂ ልማት የሚያመጣ ሥራ ይሠራሉ፤ ለአባልም ሆነ አባል ላልሆነው የአካባቢው ሰው የውኃ ጉድጓድ፣ ትምህርት ቤት… ሠርተው ተጠቃሚ ያደርጋሉ::
አመሠራረት እና ሕጋዊ ሰውነት
በተሻሻለው የአማራ ክልል አዋጅ 220 /2017 አንቀፅ (6) መሠረት በየደረጃው በዞን፣ በክልል እና በፌደራል ደረጃ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን እውቅና ይሰጣቸዋል:: ማሟላት የሚገባቸው ነጥቦች ደግሞ በአንድ በተወሰነ አካባቢ የሚኖሩ በተመሳሳይ ችግር እና በተመሳሳይ ሙያ የተሠማሩ ወገኖች ማህበር ሊመሰርቱ ይችላሉ:: ይህም ሲባል የኀብረት ሥራ ማህበራት መርሆዎች በዘር እና በፓለቲካ እንደማይከፋፈል አስቀምጧል፤ የመሥሪያ ክልል /አካባቢ/ ግን ገደብ እንዳለው ባለሙያዋ ጠቁመዋል::
መሰረታዊ ኀብረት ሥራ ማህበራት ሲመሰርቱ ቃለ ጉባኤ ይይዛሉ፣ መተዳደሪያ ደንብ ያረቃሉ፣ አባላት ተገኝተው ፊርማቸውን በማስቀመጥ ይመዘገባሉ::ይሄንን ለኀብረት ሥራ ኮሚሽኑ በማቅረብ ምዝገባ ይፈጽማሉ:: የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ካሟሉ በአንድ ቀን ተኩል ውስጥ እውቅና ይሠጣሉ::
በክልሉ መመሪያ መሠረት አንድ ሰው አባል ለመሆን ከ14 ዓመት ጀምሮ እንደሚቻል ሲያስቀምጥ የፌደራሉ ግን 18 ዓመት ይላል:: 14 ዓመት ለሕግ ትርጉም ስለሚዳርግ ብዙ ጊዜ የሚሠራበት እና መታወቂያም መያዝ የሚቻለው 18 ዓመት እና ከዛ በላይ ስለሆነ የሚሠራበትም 18 ዓመት እንደሆነ ነው ባለሙያዋ ያብራሩት::
በሌላ በኩል በመመሪያ የሚቋቋሙ ማህበራት ይኖራሉ፤ ለምሳሌ የቤት ሥራ ማህበር መነሻ ቁጥር ከ10 እስከ 24 ሰዎች እንደ መነሻ መስፈርት ተቀምጧል:: ዩኒየን የሚመሰርቱ ከሆነ ደግሞ አባል የሚሆኑት በሕግ እውቅና የተሠጣቸው መሠረታዊ የኀብረት ሥራ ማህበራት ናቸው:: ፌደሬሽን ሲሆን ደግሞ ተመሳሳይ ዩኒየኖች ናቸው:: በየደረጃው የተቋቋሙ ኅብረት ሥራ ማህበራት ዋና ዓላማቸው ለአባላት በቂ እና ተመጣጣኝ አገልግሎት ለመሥጠት እንጂ ከፍተኛ ትርፍን ማግኘት አለመሆኑን ባለሙያዋ ጠቁመዋል::
ማኅበራት ከአባላት ምርት ሲገዙ ለዘር፣ ለማዳበሪያ እና ሌሎች የተለያዩ ግብዓቶችን ለመግዛት ያወጣውን ወጭ ታሳቢ አድርገው በወቅታዊ የገበያው ዋጋ መሠረት እንደሆነም ባለሙያዋ አስገንዝበዋል:: አመራር አካላት ለሦስት ዓመታት ሲመረጡ በየዓመቱ ለኮሚሽኑ የሒሳብ ምርመራ/ኦዲት ሪፓርት ያቀርባሉ:: እንቅስቃሴውን ሠራተኛ በመቅጠር ሂሳቡን በየጊዜው በማሠራት ለሂሳብ ምርመራ ምቹ ማድረግ እንደ ሚገባም ነው ባለሙያዋ የሚገልፁት:: የሒሳብ ምርመራውንም የኀብረት ሥራ ኮሚሽኑ ብቻ እንደሚያደርጉ ወ/ሮ አልማዝ ተናግረዋል::
የፌደራል አዋጅ ቁጥር 220/2007 አንቀፅ 26 ንኡስ አንቀፅ (6) እንዲሁም አንቀፅ 28 ንኡስ አንቀጽ (4) አሠራር የተመረጠው ቦርድ ለሦስት ዓመት ሲመረጥ በአሠራሩ ላይ ክፍተት ከተገኘ፣ የገንዘብ ጉድለት ከተከሰተ በፍትሐብሔር እንዲሁም በወንጀል ተጠይቀው የጎደለውን ይመልሳሉ:: አስፈላጊ ከሆነ በእስርም እንደሚቀጡ ተጠቁሟል:: ጥፋቱን የፈፀመው ተቀጣሪ ሠራተኛ ከሆነ ከሥራው ይሰናበታል፣ በፍትሐብሔር እንዲሁም በወንጀል ተጠያቂ ይሆናል:: ህብረተሰቡ በራሱ ፍቃድ ወዶ እና ፈቅዶ የሚመሠርታቸው እነዚህን ማህበራት መጠቀም፣ መደገፍ እና ካጠፉ መጠየቅ እንደሚገባው ነው የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ አልማዝ ያሳሰቡት::
የሕግ አንቀጽ
የኀብረት ሥራ ማህበራት እሴቶች
- ራስን በራስ መርዳት፣
- የግል ኃላፊነትን መወጣት
- የዴሞክራሲ ባህልን ማስፋፋት
- እኩልነት፣ፍትሐዊነት እና ወንድማማችነት ናቸው፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት አባላት የሥነ ምግባር እሴቶች
- ታማኝነት
- ግልጸኝነት
- ተጠያቂነት
- አሳታፊነት
- ማህበራዊ ኃላፊነት እና ለሌሎች ማሰብ ናቸው፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


